ሁለት
ምስክሮች ይቀራሉ
Free All Political Prisoners !!! |
የእነ ጉርሜሳ አያኖ መዝገብ ለጥር 15/2009 የተቀጠረው አቃቤ ህግ ይቀሩኛል ያላቸውን 5 ምስክሮች ለመስማት ነበር፡፡ ከአምስቱ ምስክሮች ሶስቱ በዛሬው እለት የምስክርነት ቃላቸውን ለመስጠት መቅረባቸውን አቃቤ ህግ አሳውቋል፡፡ ሁለቱ ምስክሮች በተመሳሳይ ጭብጥ በ18ኛ ተከሳሽ ላይ ፤ አንዱ ምስክር ደግሞ በ5ኛ ተከሳሽ ላይ እንደሚመሰክሩለት ተናግሯል፡፡
በቅድሚያ የመሰከረው አብረሃም ሃይሌ የተባለው ምስክር ሲሆን፤ 18ኛ ተከሳሽ በሆነው መገርሳ አስፋው ላይ የሚመሰክር የአቃቢ ህግ የደረጃ ምስክር ነው፡፡ ምስክሩ መጋቢት 10 ቀን 2008 የፌደራል ወንጀል ምርመራ ዘርፍ ተገኝቶ ተከሳሽ የተከሳሽነት ቃሉን ሲሰጥ ያየውን እና የታዘበውን እንደሚመሰክር ጭብጥ አሲዟል፡፡ በግል ስራ ላይ የተሰማራ እንደሆነ የገለጸው ይኸው መስክር ተከሳሹን ከችሎት ለይቶ ማሳየት እንደሚችል ቢናገርም በችሎቱ ውስጥ ከነበሩት ተከሳሾች ውስጥ በተመሳሳይ መዝገብ የሚገኘውን አሸብር ደሳለኝን፤ 18ኛ ተከሳሽ መገርሳ ነው በማለት አሳይቷል፡፡ ምስክሩ ለስራ ጉዳይ ማእከላዊ አካባቢ የሚገኝ ካፍቴሪያ ውስጥ ከሌላ ጓደኛው ጋር ቁጭ ብለው እያሉ የፓሊስ አባላት ታዛቢ እንዲሆኑ ሲጠይቋቸው ተስማምተው ወደ ማእከላዊ እንዳመሩ ገልጿል፡፡ ተከሳሽ መርማሪው የሚጠይቀውን ነገር በዝርዝር ሲመልስለት፤ መርማሪውም ተከሳሹ የሚሰጠውን ምላሽ በወረቀት ሲመዘግብ እንደነበረ እንደሚያስታውስ ተናግሯል፡፡ የአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ ተማሪ እንደነበረ፣ በማስተር ፕላኑ ምክንያት የኦሮሞ ህዝብ እየተገደለ ስለሆነ ኦነግን ለመቀላቀል ሲል ሞያሌ ላይ እንደተያዘ ተከሳሹ መገርሳ አስፋው ለመርማሪው ሲናገር መስማቱን ምስክሩ ተናግሯል፡፡ መርማሪው ከተከሳሽ የተቀበለው ቃል 7 ገፅ አካባቢ እንደሚሆን እና ከተከሳሽ ጋርም ከተማመኑ በኋላ ተከሳሹ ወረቀቶቹ ላይ ሲፈርም መመልከቱም እንዲሁም እሱና ሌላኛው ታዛቢ ጓደኛው የተለየ ወረቀት ላይ መፈረማቸውን ገልጿል፡፡
በ18ኛ ተከሳሽ ላይ የሚመሰክረው ሁለተኛ የአቃቤ ህግ ምስክር አቶ መስፍን ብርሃኔ፤ በተመሳሳይ ጭብጥ ላይ የሚመሰክር በመሆኑ እና ተመሳሳይ ምስክርነት ስለሚሆን ሳይመሰክር እንዲሰናበት አቃቤ ህግ በመጠየቁ ምስክሩ በችሎት ቀርቦ ሳይመሰክር ተመልሷል፡፡
ቀጣዩ ምስክር 5ኛ ተከሳሽ በሆነው አብደታ ነጋሳ ላይ የቀረበ ምስክር ነው፡፡ ጥር 17 ቀን 2008 የ5ኛ ተከሳሽ የግል ላፕቶፕ ሲከፈት በውስጡ የተገኙ ሰነዶች ፕሪንት ሲደረጉ መመልከቱን እና የታዘበውን የሚመሰክርለት እንደሆነ በጭብጥነት አሲዟል፡ ምስክሩ አቶ እንዳለ በርሄ ይባላል፡፡ ምስክሩ የሚመሰክርበትን ተከሳሽን ያየው ከአመት በፊት ከ15-20 ደቂቃ ያክል ጊዜ በመሆኑ ተከሳሽን ከችሎት ለይቶ ማሳየት እንደማይችል ተናግሯል፡፡ ጥር 17/2008 ቀን ፍቅርአለም የተባለ ጓደኛው ለስራ ጉዳይ ወደ ማእከላዊ ወንጀል ምርመራ ዘርፍ በሚሄድበት ወቅት አብሮት መሄዱን ገልፆ መርማሪ ፖሊስ ጓደኛውን ታዛቢ እንዲሆኑ ሲጠይቃቸው እነሱም ተስማምተው መታዘባቸውን ገልፀዋል፡፡ በእለቱ ምርመራ ክፍል ውስጥ መርማሪው ላፕቶፕ ይዞ እንደመጣና ተከሳሹም የራሱ መሆኑን አምኖ እና የሚስጥር ኮዱን እንዲያስገባ እና ላፕቶፑን እንደከፈተው ተናግሯል፡፡ ላፕቶፑ ላይ የፕሪንተር ኬብል ከተሰካ በኋላ 4ገፅ ወረቀት (3 ገፅ ኦሮምኛ እና 1 ገፅ አማርኛ) ፕሪንት መደረጉን እንዲሁም የኦነግን ባንዲራ ያደረጉ ሰዎች ያሉበት የቅስቀሳ ዘፈን ከላፕቶፑ ወጥቶ በሲዲ ተደርጎ ማየቱን ገልጿል፡፡ በ3ቱ ገፅ ላይ የተፃፈውን ኦሮምኛ ፅሁፍ ይዘት ምን እንደሆነ እንደማያቅ የተናገረው ምስክሩ፤ 1ዱ ገፅ አማርኛ ፅሁፍ ላይ “የመሬት ወረራ ይቁም!”፣ “ለሞቱት ሰዎች ተጠያቂ መንግስት ነው!” እና “ኢህአዴግ አሸባሪ ነው!” የሚሉ ፅሁፎች እንዳሉባቸው እንደሚያስታውስ ተናግሯል፡፡ ወረቀቶቹ ፕሪንት ከተደረጉ በኋላም ተከሳሹ ከፈረመባቸው በኋላ ምስክሩ ከተከሳሽ ላፕቶፕ ፕሪንት ሲደረግ ያየውን ሰነድ ከሌሎች ማስረጃ ሰነዶች ጋር ተደባልቆ ተሰጥቶት ለይቶ አሳይቷል፡፡ ኦሮምኛ ቋንቋ እንደማይችል የተናገረው መስካሪው፤ ከላፕቶፑ ወደ ሲዲው የተቀዳው ቪድዮ ዘፈን መሆኑን እንዴት ማወቅ እንደቻለ ተጠይቆ ቪዲዮው ላይ የሙዚቃ ድምፅ ስላለው እንደሆነ ተናግሯል፡፡ ተከሳሽ በወቅቱ የተረጋጋ ሁኔታ ውስጥ እንደነበረ እና በሚታዘቡበት ወቅት ሻይ ተጋብዘው ሲጠጡ እንደነበረ ገልፇአል፡፡
የቀረቡት የአቃቤ ህግ ምስክሮች ከተደመጡ በኋላ ቀሪ ሁለት ምስክሮችን በተመለከተ ተጨማሪ ጊዜ እንዲሰጠው እና ምስክሮቹን ማሰማት እንዲችል አቃቤ ህጉ ጠይቋል፡፡ ምስክሮቹን ማቅረብ ያልተቻለው ቀድሞ ይኖሩበት ከነበረው አድራሻ ቀይረው ሌላ አካባቢ በመሄዳቸው እና የቀየሩት ቦታም ስለታወቀ አዲስ ከቀየሩት አካባቢ ፈልጎ ለማግኘት ጊዜ እንዳልበቃ አቃቤ ህግ ተናግሯል፡፡
ምስክሮቹ አድራሻ መቀየራቸውን እና ሊያገኟቸው እንዳልቻሉ ከዚህ በፊትም በምክንያትነት ሲቀርብ የነበረ ነገር መሆኑን እና ከነበሩበት አካባቢ አድራሻ መቀየራቸውን የሚገልፅ ደብዳቤ ከቀበሌ እንዲያመጡ (አቃቤ ህግና ፓሊስ) ታዘው ማቅረብ እንዳልቻሉ አስታውሰው አቃቢ ህጉ ያቀረበው ምክንያት አሳማኝ እና ፍትሃዊ አይደለም ሲሉ የተከሳሽ ጠበቆች አቃቤ ህግ የጠየቀውን ተጨማሪ ጊዜ በጥብቅ ተቃውመዋል፡፡ በተጨማሪም አቃቤ ህግ ምስክሮችን ለማቅረብ እና ለማሰማት በቂ ጊዜ ተሰጠቶት እንደነበረ ገልፀው በህገመንግስቱ አንቀፅ 37 የተደነገገውን ፍትህ የማግኘት መብት እንዲሁም በስነስረአት ህጉ አንቀፅ 94 የተገለፀውን የምስክር አቀራረብ ሂደት እንደሚፃረር በማስረዳት በተሰሙት ምስክሮች ብይን እንዲሰጥ የተከሳሽ ጠበቆች ጠይቀዋል፡፡
ጠበቆቹ ካነሱት ሃሳብ የተለየ የሚናገሩት እንዳላቸው በማሳወቅ የኦፌኮ ም/ፕሬዝዳንት እና 4ኛ ተከሳሽ የሆኑት አቶ በቀለ ገርባ የሚከተለውን ተናግረዋል፡፡ “አቃቤ ህግ የሚያነሳቸው ሃሳቦች ታማኝነት የሌላቸው እንደሆኑ እናምናለን፡፡ ከዚህ በፊትም ምስክር መሰማት ከመጀመሩ በፊት ምስክሮቹ በዝግ ችሎት እንዲሰሙ አቃቤ ህግ ሲጠይቅ ያቀረበው ምክንያት “ምስክሮቹ ከተከሳሾቹ ጋር በድርጊት የተሳተፉ ስለሆነ” የሚል ነበር፡፡ እስካሁን እንዳየነው ምስክሮች ተሰምተው ወደ ማለቃቸው ነው፡፡ ከአንድ ምስክር በስተቀር በድርጊት ተሳተፍኩ ያለ አልሰማንም፡፡ እሱም በሩቁ ነው አየሁ ያለው፡፡ የዛሬውም መከራከሪያ ጊዜ አልነበረኝም የሚለው ምክንያት አሳማኝ አይደለም፡፡ ስለሆነም የምስክር ማስረጃዎቹ እንደሌሉ ተቆጥሮ እንዲወሰድልን ነው የምጠይቀው፡፡”
አቃቤ ህግ በበኩሉ ምስክሮችን ለማምጣት እና ለማሰማት የተቻላቸውን ጥረት እያደረጉ እንደሆነ ገልፆ፤ ምስክሮች አዲስ የቀየሩበት ቦታ በመታወቁ ቀድሞ ከሚኖሩበት ቦታ እንደማይገኙ የሚገልፅ ማስረጃ ማቅረብ አቅቷቸው ሳይሆን ማስረጃውን ከማቅረብ ምስክሮቹን ማቅረብ እንደሚሻል በማመን ምስክሮቹን የመፈለግ ስራ ቅድሚያ ሰጥተው እየሰሩ እንዳለ ተናግሯል፡: