Search This Blog

Friday, January 31, 2014

የኢትዮጵያ ሕዝብ አርበኞች ግንባር ሰራዊት መተማ አካባቢ ጥቃት ፈፀመ

የኢትዮጵያ ህዝብ አርበኞች ግንባር የአገራችን ኢትዮጵያን ዳር ድንባር ለሱዳን ለማስረከብ ሽር ጉድ እያለ የሚገኘውን የወያኔን አገዛዝ ጸረ-አገርና ጸረ-ህዝብ እንቅስቃሴ በመቃወም በመተማ አካባቢ ልዩ ስሙ ዘባጭ ባህር በተባለ ቦታ ከወያኔው 24ኛ ክፍለ- ጦር ጋር በጥር 21- 2006 ዓ.ም ከቀኑ 6 ሠዓት ላይ ባደረገው ውጊያ 14(አስራ አራት) ገድሎ 12(አስራ ሁለት) አቁስሏል።
በመተማና አካባቢው በተደጋጋሚ በአርበኛው ጥቃት እየተፈፀመበት የሚገኘው የወያኔው ቅጥረኛ ሠራዊት ህይወቱን ለማትረፍ እግሩ ወደመራው እየፈረጠጠ መሆኑ ሲታወቅ በደረሰበትም ጉዳት ማካካሻ ይሆነው ዘንድ ሰላማዊውን ነዋሪ በእናንተ ምሽግነት ነው እየተመታን ያለነው በሚል እንግልት እያደረሱበት መሆኑ ታውቋል።
በተያያዘ ዜና በጭልጋ ወረዳ ጫቁ የተባለ አካባቢ ነዋሪዎች ከብት፣በግና ፍየል በአካባቢው የወያኔ ታጣቂዎች እየታረደ እየተበላባቸው መሆኑ ታውቋል።
በዚሁ አካባቢና አጎራባች ወረዳዎች የወያኔው ተላላኪዎች ተደጋጋሚ ንብረትን የመዝረፍ ሂደት የተቆጣው ነዋሪ ለምንድን ነው ንብረታችንን የምትዘረፉት ምን አደረግናችሁ ብለው ሲጠይቁ እናንተ የኢትዮጵያ ሕዝብ አርበኞች ግንባር ደጋፊዎች ፣መንገድ መሪዎች እንዲሁም ስንቅ አቀባዮች ናችሁ የሚል ምክንያት የሰጧቸው መሆኑ ታውቋል።

የአማራው ክልል መሪ በአማራው ህዝብ ላይ ተሳለቁ

    የአማራ ክልል ም/ ፕሬዚዳንት እና የብአዴን ጽ/ቤት ሃላፊ የሆኑት አቶ አለምነው መኮንን “የአማራው ህዝብ ሰንፋጭ የሆነ ትምክተኝነት የተጠናወተው በመሆኑ በቤንሻንጉልና በሌሎችም ቦታዎች ለመሰደዱ ምክንያት ሆኖታል” በማለት፣ ለብአዴን ነባርና አዳዲስ ካድሬዎች ተናግረዋል።
ካድሬዎቹ “የአማራው ህዝብ ለምን ይሰደዳል? ለምን በእየክልሉ ጥቃት ይደርስበታል? አማራውን ከጥቃት ለመከላከል ለምን ሙከራ አይደረግም በማለት ጥያቄ ያቀረቡ ሲሆን፣ ም/ል ፕሬዚዳንቱ የአማራው ህዝብ በቅድሚያ እንዳይሰደድ ለማድረግ ስራ እየተሰራ ነው፣ ነገር ግን ከተሰደደ በሁዋላም ቢሆንም ሰንፋጭ የሆነውን ትምክህተኝነቱን በመተው ከሌላው ጋር ለመኖር መልመድ አለበት ብለዋል።
አማራው “በባዶ እግሩ እየሄደ የሚናገረው ንግግር ግን መርዝ ነው” ያሉት ምክትል አስተዳዳሪውና የብአዴን የጽህፈት ቤት ሃላፊው፣ ይሄ መርዝ ንግግሩ አንድ የሚያደርግ አይደለም ሲሉ አክለዋል።
ከኢትዮጵያውያን ጋር አብሮ ለመኖር አማራው  የትምክህት ለሃጩን ማራገፍ አለበት ያሉት አቶ አለምነው፣ ይሄ ለሃጭ ሳይራገፍ በጋራ መኖር አይቻልም ሲሉ ድምድመዋል።
ማንኛውም ስም ያወጣ ሙትቻ ፓርቲ ሁሉ መንገሻው አማራ ክልል ነው ያሉት ምክትል ፕሬዚዳንቱ፣ ምክንያቱንም ሲገልጹ ትምክህትን እንደ ምግብ ስለሚመገበው ነው ብለዋል። ያንን ምግብ እየተመገበ እንደሚያቅራራም ገልጸዋል።
አንዳንድ የብአዴን አባላት የምክትል ፕሬዚዳንቱ ንግግር እጅግ እንዳበሳጫቸው ለኢሳት ተናግረዋል።
የብአዴን ካድሬዎች አንቀጽ 39 ለምን አይወጣም በማለት ላነሱት ጥያቄ፣ እኝሁ ፕሬዚዳንት ሲመልሱ አንቀጽ 39 ባይኖር ኖሮ ኢትዮጵያ  ደቡብ ሱዳን እንደሆነቸው ትሆን ነበር በማለት መልሰዋል ። አንቀጽ 39 በህዝቦች ዘንድ መተማመን መፍጠሩን፣ አቶ መለስ ዜናዊ በሞቱበት ጊዜ በገሃድ መታየቱን ም/ፕሬዚዳንቱ ገልጸዋል

ማንነት (ፕ/ር መስፍን ወ/ማርያም )



በ1996 ዓ.ም. የክህደት ቁልቁለት በሚል ጽሑፌ ውስጥ ‹‹ማንነት ምንድን ነው፤ በሚል ንዑስ ርእስ ስር ከገጽ 98 ጀምሮ በተቻለኝ መጠን አፍታትቻለሁ፤ የሪፖርተር ጋዜጠኛ ይህንን ለማንበብ ጊዜ አላገኘም፤ ወይም የተገለጠለት ዱሽ ቅንጫቢ በቅቶት ይሆናል፤ የምጠቅሰውም ለሱ ሳይሆን ለሌሎች ነው፡፡

Prof. Mesfin Woldemariam : is an Ethiopian Human Rights activist and philosopher
በቅርቡ በፌስቡክ ላይ አንድ አውቀቱ ይሁን ጤንነቱ፣ ወይም ኪሱ የተቃወሰበት ሰው በትግርኛ ስለማንነት ጽፎ ነበር፤ ከዚህ በፊትም ጽፎ አስተሳሰቡ ሁሌም የተወላገደ በመሆኑ አልፌው ነበር፤ አሁን ደግሞ ሲጽፍና በአንዳንድ የሱ ቢጤዎች አበጀህ! አበጀህ! ሲባል ሳይ አደገኛነቱን ተገነዘብሁ፤ አንዱን ጎባጣ ሀሳብ ቶሎ ካላስተካከሉት ብዙ ጎባጦችን ያፈራል፤ የተጣራና ቀና የሆነ ሀሳብን ለመግለጽ በጣም ያስቸግራል፤ ማሰብ መጨነቅን፣ ማበጠርን፣ ማጣራትን ይጠይቃል፤ አፍ እንዳመጣ መልቀቅ ቀላል ነው፤ በተለይ የሚዳኝ ከሌለ!
በመጀመሪያ ሀሳብን ለመግለጽ የተመረጠው ቋንቋ ጠበብ ያለና የተፈለጉ አድናቂዎች ዘንድ ለመድረስ ብቻ ከተፈለገ ሀሳቡም እንደቋንቋው ለተወሰኑ ሰዎች የተመጠነ ይሆናል፤ በዚህ ዓይነት የቀረበው ቅንጣቢ ሀሳብ በሌላ ቋንቋ ሊተረጎም አይቻልም፤ ደንቆሮነትን ማጋለጥ ይሆናል፤ ለምሳሌ በትግርኛ ‹‹ኢትዮጵያዊ ዝበሃል መንነት የለን፤›› የሚለውን ‹‹ኢትዮጵያዊ የሚባል ማንነት የለም፤›› በማለት፣ በእንግሊዝኛ ደግሞ ‹‹There is no identity called Ethiopian.›› ተብሎ ሊተረጎም ነው፤ እንግዲህ ይህ አወቀች፤ አወቀች ሲሏት መጽሐፉን አጠበች እንደተባለችው ሴትዮ፣ ወይም ደግሞ አላዋቂ ሳሚ እንትን ይለቀልቃል! የሚባል ነው፤ ‹‹ኢትዮጵያዊ ዝበሃል መንነት የለን፤›› ብሎ በትግርኛ የጻፈው ሰው የአለማወቁ አዘቅት ዓለምን በሙሉ የሚያናጋ መሆኑን አልተገነዘበም፤ (አሜሪካን፣ እንግሊዝ፣ ፈረንሳይ፣ ኢጣልያን … የሚባል ማንነት የለም ሊለን ነው፤) የመንደር ማንነትን በሁለት እጆቹ ይዞ፣ አእምሮውን በመንደር ማንነት ጨቅጭቆ በየፓስፖርቱ ላይ የማንነት መግለጫ ተብሎ የተሰየመውንና በዓለም አቀፍ ደረጃ የታወቀውን ማንነት ካደው፡፡
በፍጹም ያልገባውን የፈረንሳዩን ፈላስፋ፣ የሩሶን ሀሳብ አበለሻሽቶ ከቆሻሻ መጣያ ውስጥ ያገኘው ቡትቶ ሊያደርገው ይከጅላል! ከጥራዝ-ነጠቅም አጉል ጥራዝ-ነጠቅ! ትግራይን የመገንጠል ዓላማ ያለው ሰው በእውነትና በግልጽ ዓላማውን ቢያራምድ በበኩሌ አልደግፈውም እንጂ አልቃወምም፤ መብቱ ነው፤ ነገር ግን በሰንካላ አስተሳሰብና በተንኮል ወጣቶችን ለመመረዝ የሚፈልገውን ሰው አጥብቄ እቃወማለሁ፤ ትግራይን እንደኤርትራ ካስገነጠለ በኋላ እንደኤርትራ ለትግራይም የኢትዮጵያዊነት ማንነትንን ማገድ ይቻላል፤ ከዚያ በፊት ግን ተንኮል ይቅር፡፡
ኢትዮጵያዊነትን ለማጥፋት የሚደረገው ሙከራ አዲስ ኤደለም፤ ኢጣልያኖች በሰፊው ዘርተውት የሄዱት ጉዳይ ስለሆነ የአባቶቻቸውን ውርስ የሚከተሉ ዛሬም ይኖራሉ፤ ኢትዮጵያዊነትን ለማጥፋት ብዙ ገንዘብና ሌላም የሚከፍሉ ብዙ የተለያዩ ድርጅቶች መኖራቸው የታወቀ ነው፤ ዱሮ የኢጣልያ ወኪሎች ተጠቅመውበታል፤ ዛሬ ደግሞ ሌሎችም ተጨምረው ያንኑ ተልእኮ የሚያራምዱ አሉ፤ በየዋህነት እንደበፊቱ እንዳናስተናግዳቸው እንጠንቀቅ!

Friday, January 24, 2014

የሁለት አመት ህዝባዊ ንቅናቄ ዛሬም ተደገመ! (ድምፃችን ይሰማ)

የትግላችን ማረፊያ ድል ብቻ መሆኑን ዛሬም አውጀናል!         

አርብ ጥር 16/2006
የዛሬዋ እለት ለህዝበ ሙስሊሙ ካለፉት ስድስት ወራት ለየት ያለ ክስተትን አስተናግዳ ያለፈች ጁሙዓ ነች፡፡ ህዝበ ሙስሊሙ ላለፉት ስድስት ወራት ለመንግስት በጥሞና የማሰቢያ ጊዜ ለመስጠት ከማንኛውም የአደባባይ የተቃውሞ ስነ ስርአቶች ተቆጥቦ ቆይቶ ነበር፡፡ መንግስት የእፎይታ ጊዜውን በአግባቡ ሊጠቀም ያለመፍቀዱ እንዳለ ሆኖ የሰላማዊ ትግሉን ሁለተኛ አመት ለማሰብም ‹‹730 ቀናት ለሃይማኖት ነጻነት›› በሚል ለሁለት ሳምንታት የሚቆይ ዘመቻ ታውጇል፡፡ የዛሬዋ ጁሙአ የዘመቻው ኦፊሴላዊ መክፈቻ ነበረች – ደማቅ መክፈቻ! ህዝበ ሙስሊሙ በበርካታ የአገሪቱ ከተሞች በሚገኙና የትግሉን መንፈስ አማክለው በቆዩ መስጊዶች በከፍተኛ ቁጥር ተሰባስቦ በመስገድ ለትግሉ ቀጣይ እርከን ሙሉ ዝግጁነቱን በከፍተኛ ወኔ አሳይቷል፡፡
በአዲስ አበባ አንዋር መስጂድ ከጁምአው አስቀድሞ መምጣት የጀመረው ከፍተኛ ቁጥር ያለው ህዝብ አንዋርና አካባቢውን ለመሙላት ቅጽበትም አልወሰደበትም፡፡ የህዝቡ ቁጥር እንዲታይ ያልፈለጉት ፖሊሶች እንደተለመደው መኪኖችን ለህዝቡ በማስቆምና መስገጃውን እንዲያነጥፍ በመፍቀድ ፋንታ ለመከልከልና ግርግር ለመፍጠር የሞከሩ ሲሆን ለማረጋጋት የሞከሩ ወጣቶችንም ለማሰር ሙከራ አድርገው ሳይሳካላቸው ቀርቷል፡፡ መዲና ህንጻ ላይ የኢቲቪ ካሜራዎች ተደግነው ህዝቡን ሲቀርጹ የነበሩ ሲሆን ህዝቡም በመሸማቀቅ ፋንታ እነሱኑ መልሶ ሲቀርጻቸው ማየት በእርግጥም አስገራሚ ነበር፡፡ ከጁምአው ስግደት በኋላ ደማቅ የዱአ ስነስርአት ተደርጎ ሰው የተበተነ ሲሆን በመምጫና መመለሻ ሰአቶችም በድልና ነስር ኒያ የአንድ ብር ሰደቃ ለችግረኞች ተሰጥቷል፡፡ በሺዎች ፊት ላይ ይታይ የነበረው ደስታና የማይሸነፍ ወኔ በእጅጉ ማራኪ እንደነበር ሁላችንም እዚያው የመሰከርነው የትግላችን ደማቅ ትእይንት ነበር፡፡
የክልል ከተሞችም እንዲሁ በከፍተኛ ድምቀት መርሀ ግብሩን አከናውነዋል፡፡ ለአዲስ አበባ አጎራባች በሆነችው አዳማ ከተማ አቡበክር መስጂድ በህዝበ ሙስሊሙ አሸብርቆ መዋሉና የዱዓና የሰደቃ ፕሮግራሙም ባማረ ሁኔታ መጠናቀቁን ማወቅ ተችሏል፡፡ በተመሳሳይ በጂማ ፈትህ መስጂድ ደማቅ ሆነ የዱአና የሰደቃ ፕሮግራም የተካሄደ ሲሆን በቀደሙ ደማቅ ተቃውሞዎቻቸው የሚታወቁት ሻሸመኔና መቱ ከተማም በደማቅ ሁኔታ ለትግሉ ያላቸውን አጋርነት ገልጸው አልፈዋል፡፡
ካሁን ቀደም የመንግስት የሀይል እርምጃ ሰለባ የነበረችው አጋሮ ከተማም በአል አዝሀር መስጂድ ላይ በከፍተኛ ቁጥር ለጁምአ በተገኘው ህዝበ ሙስሊም ዱአና ሰደቃ ደምቃ ውላለች፡፡ በዚያው በኦሮሚያ ክልል በደሌ ከተማ የሚገኘው መስጂደ ራህማ ላይም ተመሳሳይ ደማቅ ፕሮግራም ተካሂዶ የዋለ መሆኑ ተዘግቧል፡፡

Thursday, January 23, 2014

ከቃሊቲና ቂሊንጦ እስር ቤቶች በላይ የሚያንጸባርቁ ክዋክብቶች

ዳዊት ከበደ ወየሳ (አትላንታ)
(ይህ ጽሁፍ የርዕዮት አለሙ የልደት በአል በአዲስ አበባ በተከበረበት ወቅት; ከውጭ አገር ንግግር እንዳደርግ በተጋበዝኩበት ወቅት… የስራ ባልደረቦቼን እስክንድር, ውብሸት እና ርዕዮትን በማሰብ የተዘጋጀ ነው)
ይህ ሳምንት የታላቁ ማርቲን ሉተር ኪንግ የልደት በአል በመላ አሜሪካ የሚከበርበት ነው:: በአሜሪካ ከክርስቶስ ልደት ቀጥሎ ስራ እና ትምህርት ቤት ተዘግቶ ልደቱ የሚከበርለት አንድ ሰው ቢኖር ማርቲን ሉተር ኪንግ ብቻ መሆኑን ልብ ይበሉ:: የማርቲን ሉተር ኪንግ የልደት በአል በሚከበርበት ወቅት በህይወት ዘመኑ ለጥቁር ህዝብ ነጻነት ያደረገው አስተዋፅኦ ይታወሳል:: በህይወት በነበረበት ወቅት ለሰው ልጅ እኩልነት ተሟግቷል; የነጻነት ቀንዲልን ለኩሷል:: ሆኖም እኩልነት እና ነጻነትን ሳያጣጥም በበርሚንግሃም እስር ቤት ተጥሎ ፍዳውን እንዲቆጥር ተፈርዶበት ነበር:: በመጨረሻም የሰውን ልጅ ክብር እና ነጻነት በማይደግፉ ሰዎች ህይወቱ ማለፉ ይታወቃል – መልካም ስራዎቹ ግን አላለፉም::
ዛሬም በአገራችን ስለፍትህ, ስለነጻነት የሰበኩና የደሰኮሩ; የጻፉና የመሰከሩ… ለሃቅ ቆመው፣ ግፍ የተሰራባቸው፣ ከአገር የተሰደዱና የወጡ፤ በግፍ ሰንሰለት ለጨለማ እስር የተዳረጉ ወገኖቻችን ብዙ ናቸው:: እስክንድር፣ ውብሸት፣ ርእዮት፣ አንዷለም እና ሌሎች ኢትዮጵያውያን ራሳቸውን በሰብአዊነት መሰረት ላይ ስላነጹ እና ሃሳባቸውን በነጻነት ስለገለጹ መጨረሻቸው እስር እና እንግልት ሆኗል::
እንደ እውነቱ ከሆነ ሃሳብን በነጻነት መግለጽ… ብሎም የህዝብ ልሳን ሆኖ ለህዝብ የቤዛነት ዋጋ መክፈል የሚያስከብር እንጂ የሚያሳስር አልነበረም:: በመሆኑም ለነጻ ፕሬስ መክፈል የሚገባቸውን ዋጋ ከመጠን አሳልፈው የከፈሉት፤ ርዕዮት አለሙ፣ እስክንድር ነጋ እና ውብሸት ታዬ… ሶስቱም ከአገራቸው አልፈው በአለም አቀፍ ደረጃ እውቅና አግኝተዋል:: በአለም አቀፍ ደረጃም በልዩ ልዩ አለም አቀፍ የጋዜጠኞች ማህበራትና ተቅውውማት ለሽልማት ታጭተው አሸናፊ ሆነዋል::
የ’ነዚህ የስራ ባልደረቦቼ ብዕር… ህዝብን ሳይሆን የተወሰኑ ወገኖችን አሸብሮ ሊሆን ይችላል:: እነርዕዮት አለሙ በዚህ አይነት ሰበብ አስባብ በቃሊቲ እና በቂሊንጦ እስር ቤት ታግተው፤ ነጻነታቸውን አጥተውና ህክምና ተነፍገው ይታሰሩ እንጂ፤  ለእውነት የቆሙ ወገኖች ግን ለመልካም ስራቸው ሽልማትን አልነፈጓቸውም::
ማርቲን ሉተር ኪንግ በበርሚንግሃም እስር ቤት ታስሮ ቢማቅቅም የአሜሪካም ሆነ የአለም አቀፉ ማህበረሰብ አልዘነጋውም:: ቆይቶም ቢሆን የአለም አቀፉ ኖቤል ተሸላሚ እስከመሆን ደርሷል:: ዛሬ በእስር ላይ የሚገኙት የነጻው ፕሬስ ጋዜጠኞች የኖቤል ተሸላሚ ባይሆኑም አለም ግን አልረሳቸውም:: ከታሰሩበት የጨለማ ወህኒ ቤት ጀርባ፤ ከብረት ፍርግርግ እና ከግድግዳዎቹ ባሻገር በመቶዎች፣ በሺዎች እና በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች እነዚህን ጋዜጠኞች በመልካም ስራቸው ያስታውሷቸዋል; ይዘክሯቸዋል:: ስለሆነም የጻድቃን ሞት፤ የሰማዕትነት ጽድቅ ተደርጎ እንደሚቆጠረው ሁሉ… የነ እስክንድር፣ ውብሸትና ርዕዮት እስር፤ ከቶውኑ ዋጋ ቢስ እና ፍሬ አልባ ሊሆን አይችልም::
ኢትዮጵያ ውስጥ በነበርኩበት ወቅት በፕሬስ ጉዳይ ተደጋጋሚ የሆነ እስር ደርሶብኛል:: በ’ነዚህ የእስር እና እንግልት ጊዜያት ግን… ከጨለማው እስር ቤት ማዶ ለምን እንደታሰርኩ የሚረዱ ሺዎች በመኖራቸው ሁልጊዜ እጽናና ነበር:: በተደጋጋሚ እስር ቤት እየመጣ የሚጠይቀኝ እና የዋስ መብቴን አስጠብቆ ከእስር እንድወጣ ያደርገኝ የነበረው ወላጅ አባቴ፤ “የታሰርከው ሰርቀህ ወይም ሌላ ወንጀል ሰርተህ ሳይሆን፤ እውነትን ስለተናገርክ ነው:: ስለዚህ አንገትህን ቀና ልታደርግ እንጂ ልትሸማቀቅ አይገባህም::” የሚል አጽናኝ ቃል ሁሌ ይነግረኝ ነበር:: ዛሬ አባቴ በህይወት የለም:: ቃሉ እና ምክሩ ግን አብሮኝ አለ:: በእስር ላይ ለሚገኙ የነጻው ፕሬስ ጋዜጠኞች፤ “አንገታችሁን ቀና አድርጉ!” የሚለውን መልዕክት አጋራቸዋለሁ::

ሀገርን ቆርሶ በመስጥት በስልጣን መቆየት አይቻልም

አንባገነኑ የኢትዮጵያ  መንግስት የሀገሪቱ እና የህዝቦችን ጥቅም ያላአንዳች ይሉኝታ ለባእዳን አሳልፎ ሲሰጥ እነሆ 22 አመታት ተቆጥረዋል፡፡ መቼም እያንዳንዱን የወያኔ ጉድ መዘርዘር አንባቢን ማሰልቸት ቢሆንም ከሰሞኑ ደግሞ የአቶ መለስን ራዕይ ከማስፈጸም ውጭ የራሱ የሆነ አመክንዮ የሌለው ጠ/ር ሀይለማሪያም ደሳለኝ በአያት ቅድመ አያቶቻችን አጥንት ተከብሮ የቆየውን የሀገራችን ለም መሬት ለሱዳን አሳልፎ ለመስጠት ሙሉ ፈቃደኝነቱን አሳይቶ ተፈራርሞ ተመልሷል፡፡ወያኔ የኢትዮጵያን ህዝብ በምንም ጉዳይ ላይ አማክሮት አያውቅም፡፡ሀገሪቱን ለማስተዳደር መጀመሪያም ውክልና ስላልተሰጣቸው ምንም ጎጅ ውሳኔ በሀገር ላይ ሲያስተላልፉ ህዝቡ ምን ይለናል ብሎ የሚያስብ ህሌና የላቸውም፡፡ባለፉት 2 ወራት በመቶ ሺ በላይ ኢትዮጵያውን በአሰቃቂ ሁኔታ ከሳውዲ አረቢያ ሲባረሩ በቦታው በመገኘት ወገናቸውን ለመርዳት ያልሞከሩ ባናዳዎች ዛሬ ሱዳን ድረስ በመሄድ ዳር ድንበራችን ለሱዳን ለመስጠት ሽር  ጉዱን ተያይዘውታል፡፡ወያኔ ተደብቆ የሚቀር እየመሰለው ሀገራዊ ክህደት ሲፈጽም  ከህዝቡ የሚመጣውን ተቃውሞ ለማርገብ ምንም የማይቆፍረው ድንጋይ የለውም፡፡
የአሰብን ወደብ ለኤርትራ አሳልፎ በሰጠበት ወቅት የክህደት አባት የሆነው ሟቹ አቶ መለስ ዜናዊ ለአንድ ሀገር እድገት ወደብ ምንም ሚና አይጫወትም ፡፡በገንዘባችን አማርጠን  ወደብ መከራየት እንችላለን በማለት አያናችሁን ጨፍኑ ላሞኛችሁ አይነቱን የደንቆሮ ፕሮፖጋንዳ እንዳላዘኑ ህይወታቸው ቢያልፍም ዛሬም ድረስ አሰብ ከኢትዮጵያውያን ህሌና ሳይፋቅ አብሮን ተቀምጡዋል፡፡  ጦርነት ላለመግባት አሰብን አሳልፎ የሰጠው ወያኔ ውሎ አድሮ ሸአቢያ  ባድመ ላይ ወረራ ሲፈጽም የማይቀረውን ጦርነት ተገባ፡፡ ነገር ግን ኢትዮጵያውያን ከአራቱም ማዕዘን ትንቀሳቅሰው መተኪያ  የሌለው ህይወታቸውን ከፍለው ባድሜን በቁጥጥር ስል ቢያውሉም የህዝቡን ይሁንታ ሳያገኝ በደም የተገዛውን መሬት በጠረጴዛ ዙሪያ ቁጭ ብለው በሄግ  አለም ፍርድ ቤት ለትግል አጋራቸው  አስረክበው ተመለሱ፡፡ ድንበሩን ማስረከባቸው ሳያንስ ደሙን አፍሶ አጥንቱን ከስክሶ  ድል የተቀዳጀውን ወታደር ፤ ጡዋሪ ቀባሪ ልጆቻቸውን በሞት የተነጠቁ ወላጆችን እና ባሉዋን በሞት ተነጥቃ በሀዘን የተጎሳቆለች የሙዋች ወታደር ባለቤትን ሰብስቦ ባድሜ ለኢትዮጵያ ተፈረደልን ወጥታችሁ በሰላማዊ ሰልፍ  ደስታችሁን ግለጹ በማለት የሀሰት ከበሮ እያስደለቀ ህዝቡን አታለዋል፡፡ዛሬም በሱዳን ድንበር ዙሪያ እውነታውን በመደበቅ  እያታለሉት ይገኛሉ፡፡
ወያኔ መድሀኒታችን እየሱስ ክርስቶስን በ30 ብር አሳልፎ የሸጠውን ይሁዳን እና ለምስር ንፍሮ ብሎ ብኩርናውን የሸጠውን ኢሳውን ይመስል፡፡ ይሁዳ ፈጣሪውን ለገንዘብ አሳልፎ ቢሰጥም በገንዘቡ እንኩዋን ሳይጠቀምበት ህይወቱ እንዳለፈው ሁሉ ወያኔም ምንም ያክል በስልጣን ለመቆየት ሀገርን እየቆረጠ ቢሰጥም በክህደት የሚገኝ ስልጣን እንደይሁዳ ሞትን ይዞላቸው እየመጣ ነው፡፡ ይሁዳ በደም የገዛውን መሬት አኪልዳማ ብሎ እንደሰየመው ወያኔም በስልጣን የሚቆይበትን ጊዜ አኪልዳማ ነው፡፡
ለሱዳን መሬትን ቆርሶ በመስጠት በስልጣን ለመቆየት የሚደረግ የቀቢጸ-ተስፋ ተግባራት በምንም መልኩ ህዝባዊ ጥያቄን አዳፍኖ ማስቀረት አይችልም፡፡ወያኔ ህዝቡን ሳያውቀው አንድ ቀን እንኩዋን በድፍረት ክህዝብ ሳይወያይ ሌባ እና ፖሊስ ድብብቆሽ በመጫወት ወደ ግብአተመሬቱ እየተቃረበ ይገኛል፡፡ሁሉንም የመጫወቻ ካርዶች ወደመሬት ጥሎ ፋርዳ የወጣው አንባገነን የዘር ጥላቻውንም፤የእምነት ጥላቻ ዘመቻውን በግልጽ እና በስውር ቢያካሂድም ከልዩነት ይልቅ  አንድነቱ እና ወገናዊነቱ እያመዘነ የመጣውን የህዝቦችን ህብረት መቋቋም ተስኖታል፡፡ለዚህም እንዳበደ ውሻ ያገኘውን ሁሉ እየነከሰ ይገኛል፡፡መጻፍ ፤መደራጀት ሽብርተኛ እያሉ  ዜጎችን በጅምላ በማሰር በመግደል የህዝብን አመጽ ማስቆም አይቻልም፡፡ሀገርን እየቆረሱ ለባእዳን በመስጠት በስልጣን መቆየት አይቻል፡፡በስልጣን ለመቆየት የሚያስችለው የማሸነፊያ ካርድ በሱዳን እጅ ሳይሆን በተባበሩት የኢትዮጵያ ህዝቡች እጅ ነው ሚገኘው፡፡

Wednesday, January 22, 2014

የወያኔ ነፍስ በበረከት ስምዖን በኩል ስትቃዥ

አንደኛው መስከረም ጠብቶ ሌላኛው መስከረም እስኪጠባ ድረስ ባሉት የ365.25 ቀናት ውስጥ ስንት ጉድ መስማት እንዳለብን የሚጠቁም አሃዛዊ መረጃ ሊኖር እንደማይችል መቼም ግልጥ ነው፤ ነገር ግን የዘመናችን ኢትዮጵያ የታሪክ ጎርፍ ያመጣብን ከወያኔና መሰሎቹ በስተቀር ሌሎቻችን ያልጠበቅነው ዱብዕዳ ክስተት ምሥጋና ይንሳውና በዬቀኑ የማንሰማውና የማናየው ዕንቆቅልሽ እንዳይኖረን ሆነናል፡፡ በዚህ መልክ በተለይ ባለፉት 22.8 ዓመታት ውስጥ የታዘብነው የታሪክ ምፀትና ወኔያዊ የውሸት ስንክሳር በረጂሙ ታሪካችን ታይቶም ሆነ ተሰምቶ እንደማያውቅ ማንም ጤናማ ኅሊና ያለው ዜጋ የሚመሰክረው ይመስለኛል፡፡ ለዛሬ አንዱን የወያኔ ነጭ ውሸት እንመለከታለን፡፡Bereket Simon, Woyanne propaganda chief
በነገራችን ላይ ወያኔና እውነት ዐይንና ናጫ መሆናቸውን የማይረዳ ወገን እንደማይኖር እገምታለሁ፡፡ የወያኔን ተፈጥሮ ወያኔ ራሱን ጨምሮ ሁሉም ያውቃል፤ የወያኔ እውነት፣ የእውነት ግልባጭ የሆነችው ሀሰት ናት፡፡ ለወያኔ ውሸት ማለት እውነት ናት፡፡ ለወያኔ እንደእውነት የሚመርና የሚያቅር ነገር የለም፡፡ በተቃራኒው ደግሞ ለወያኔ እንደሀሰት የሚጣፍጥ ምንም ነገር የለም፡፡ ወያኔና እውነት በሂሳባዊ አገላለጽ ‘asymptote’ ናቸው – መቼም ሊገናኙ የማይችሉ ተጻራሪ ኑባሬያት በመሆናቸው፡፡ ወያኔ የሀሰት የህግ ባል ነው፤ የሚለያዩት ወይም የሚፋቱት ከሁለት አንድኛቸው ወይም ሁለቱም ሲሞቱ ብቻ ነው፡፡ ሀሰት ግን እስከዓለም ፍጻሜ ስለምትኖር ወያኔ ካልጠፋ ከውሸታምነቱና ከሀገር አጥፊነቱ ተፈጥሯዊ ባሕርይው ሊፋታ አይቻለውም፡፡ ታሪክ ግን ሥራውን የማይረሣ ቆፍጣና ገበሬ በመሆኑ ጊዜውን ጠብቆ እነዚህን ጉግማንጉጎች ወደማይቀረው መቃብራቸው እንደሚሰዳቸው የታመነ ነውና መፍረስ የጀመረው የበሰበሰ ሥርዓታቸው ከነሰንኮፉ ተገርስሶ ሀገራችን በቅርቡ ነጻ እንደምትወጣ በሙሉ ልብ አምናለሁ፡፡ በዚህች መንደርደሪያ ወደሰሞነኛው የበረከት ስምዖን ውሽከታ እንለፍ፡፡
“የኢትዮጵያ አርሶ አደር እስካሁን በተደረገለት ሥራ በሚገባ የረካ ስለሆነ ‹መንግሥት ሰልፍ ውጣ ቢለው ይወጣል፤ መንግሥት ተኛ ቢለው ይተኛል፤ ግፍ ብንፈጽም እንኳን አርሶ አደሩ ይህንን መንግሥት ይሸከመዋል እንጂ ምንም አይለውም፡፡”
ይህን የብፃይ በረከት ንግግር በዓይነቱ ልዩ የሚያደርገው የተባበሩት መንግሥታት ሰሞኑን ባወጣው አንድ ጥናታዊ ዘገባ ላይ በአፍሪካ ፈጣን ዕድገት ከሚያሳዩ አሥር ሀገሮች ውስጥ ኢትዮጵያ አለመካተቷና በተጓዳኝም ይህቺው ኢትዮጵያ – ይህቺው ወያኔን በጫንቃዋ እንደምትሸከም በረከት አፉን ሞልቶ የመሰከረላት ጉደኛዋ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ጠኔ ጓዙን ጠቅልሎ ከመሸገባቸው አምስት የመጨረሻ ድሃ ሀገራት ውስጥ መመደቧ ነው – (በረከት ይህን ሪፖርት ሳያነብ መሆን አለበት ያን በህልሙ የደረሰውን ጅሎችን የማሞኛ ተምኔታዊ(utopian) ቧልታይና ድንቃይ ድርሰቱን የደሰኮረው!)፡፡ በነገራችን ላይ በአምባገነንነትና በድህነት በወያኔ መንግሥት ሳይቀር የምትታማዋ ኤርትራ በነዚህ ዘገባዎች አልተካተተችም(እንዲያውም ዘገባው ኢትዮጵያን ይግረማት ብሎ ከአሥሩ በፍጥነት እያደጉ ካሉ የአፍሪካ ሀገራት ውስጥ አንዷ ኤርትራ እንደሆነች የገለጠ መሰለኝ)፡፡ ኢትዮጵያ ቻድን ብቻ በልጣ በአፍሪካ በርሀብተኝነት ሁለተኛ ስትወጣ ኤርትራ ከአምስቱ የባሰባቸው ሀገራት ውስጥ አልገባችም፡፡ የርሷ መግባት አለመግባት የኔ ራስ ምታት አይደለም፡፡ ነገር ግን ይህች በማዕቀብና በልዩ ልዩ የማሰቃያ መንገዶች የተወጠረች የቀድሞ የኢትዮጵያ ግዛት ከኢትዮጵያ የተሻለች መሆንዋን በመረጃ በተደገፈ ዘገባ የሚረዳ ጤናማ ሰው የወያኔን ሚዲያ አስችሎት እንዴት ሊከታተል እንደሚችል ይታያችሁ፡፡ ክርስቶስ ‹አፌን በምሳሌ እከፍታለሁ› አለ፡፡ ወያኔም ይህችን የክርስቶስ አባባል ቀምቶ በማንሻፈፍ ‹አፌን በሀሰትና ዕብለት እከፍታለሁ› አለና ነጋ ጠባ የማያቅመን የሀሰት ወሬ የማይነጥፍበት አስገራሚ ፍጡር ሆነ፡፡
መዋሸት የማይሰለቸው ‹ልማታዊው መንግሥታችን› በሚዲያው የሚያሳየን ኢትዮጵያና እኛ በግልጥ የምናያት ኢትዮጵያ ተለያይተውብን ተቸግረናል፡፡ እነሱ ‹ኢትዮጵያ በልማት ጎዳና እየተመመች ናት፤ የጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊን ራዕይ ለማሳካት በየፈርጁ የምናካሂደው የልማት ግስጋሴ ግቡን እየመታ ነው፤ የኢትዮጵያ ልማት ማንም በማይወዳደረው ሁኔታ ወደፊት እየተምዘገዘገ ነው፡፡ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓታችንን በማይነቃነቅ ዓለት ላይ ገምብተናል፤ የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች መብት ሳይሸራረፍ የተከበረባትና በሕዝቦች መፈቃቀድ ላይ የተመሠረተ አንድነት እውን የሆነባት አዲሲቷ ኢትዮጵያ ተፈጥራለች፡፡ አሁን ዋናው ጠላታችን ድህነት ነው፡፡ እሱንም እየተዋጋነው ነው…›እያሉ በቲቪያቸው እያላገጡብን ነው – ድህነትን ለመዋጋትና ለማሸነፍ ደግሞ ስንት አሥር ዓመቶች እንደሚያስፈልጉን እነሱው ናቸው የሚያውቁት፤ ለመልካም አስተዳደር እኮ አንድ የመኸር ወቅትም ትልቅ ጊዜ ነው – እንኳንስ 23 ዓመታት፡፡ ወያኔዎች ግን በድህነት ላይ እንደዛቱና ወደታሪክነት እንለውጠዋለን እንዳሉ ሦስት ዐሠርት ዓመታትን ሊደፍኑ ነው፤ አያፍሩም፡፡ በማከያው ግን ዕድሜ ለወያኔው ጉጅሌ በምግብ “ሞልቶ መትረፍረፍ” ከአፍሪካ አንዲት ሀገር ብቻ በልጠን በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎቻችን የተንጣለሉ የአስፋልት መንገዶችንና በአብዛኛው የትግራይ ተወላጆች የሆኑ ኢንቬስተሮች የገነቧቸውን ሕንፃዎች “እየተመገቡና እየጠገቡ” መሆናቸው እየተነገረን ነው፤ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ያጡ የነጡ ዜጎቻችንም ከዬቆሻሻ ገንዳዎች የሀብታም ፍርፋሪና የሙዝ ልጣጭ ለመሻማት ቀን ከሌሊት ሲራኮቱ ይታያሉ፡፡ የወያኔ ዕድገት ይህ ነው፡፡ የወያኔ ‹ልማታዊ ጋዜጠኞች›ም በበኩላቸው የሕዝቡን ሰቆቃ እንዳይመለከቱና እንዳይዘግቡ እንደአቃቂ ፈረስ ዐይኖቻቸውን በወያኔ ተከልለው በብድርና በዕርዳታ በተገነቡ መንገዶችና ድልድዮች ላይ ካሜራዎቻቸውን በመደቀን ሌት ከቀን በተመሳሳይ ዜናዎችና ሀተታዎች ማደንቆራቸውን ተያይዘውታል፡፡ እኛን እሚያሳክከን ሆዳችን ላይ እነሱ እሚያኩልን እግራችንን፡፡ የሚገርሙ ጋዜጠኞችና የሚገርም የማፊያዎች መንግሥት፡፡
ወደበረከት ንግግር እንመለስ፡፡ እንደእውነቱ በረከት ከፍ ሲል የተናገረውን ነገር ለምን እንደተናገረው አልገባኝም፡፡ ምን ማለት እንደፈለገ ለመረዳት አስተርጓሚ ሳያስፈልግ አይቀርም፡፡  አማርኛ ቋንቋን አውቃለሁ ብዬ ደረቴን ነፍቼ እናገራለሁ፡፡ ነገር ግን ይህንን የበረከትን ንግግር እንደመሰለኝ ተርጉሜ እንዲገባኝ ጥረት አደረግሁ እንጂ በቅጡ ልረዳው አልተቻለኝም፤ እርሱም ቢሆን ጎንደር ውስጥ ብዙ ዓመታትን ስለኖረ አማርኛን ከአፍ መፍቻው ባልተናነሰ ያውቃል ብዬ እገምታለሁና ‹ምን ማለት እንደፈለገ ሳይገባው እንዲህ ያለ የተወነዣበረ ንግግር በአደባባይ ተናግሮ የሰው መሣቂያ ለመሆን አይደፍርም› ብዬ ለማመንም በጣም ተቸገርኩ፡፡
ይህን ንግግር በብዙ መልኩ መገንዘብ እንደሚቻል አምናለሁ፤ በአማርኛው “የጊዮርጊስን ግብር የበላ ሳይነኩት ይለፈልፋል” ወይም በሌላ ፈሊጣዊ አገላለጽ “የምላስ ወለምታ” የምንላቸው ምሥል ከሳች አባባሎች አሉ፡፡ በፈረንጅኛው “Fruedian slip” የሚባል በሥነ ልቦና የትምህርት ዘርፍ የሚጠቀስ ሐረግ አለ፡፡ ይህ ሰው የተናገረውን ከነዚህ ጽንሰ ሃሳባዊ ዕይታዎች አንጻር ብንመለከተው ወያኔ ከመጃጀቱና በወንጀል ድርጊቶች ከመጨመላለቁ የተነሣ ነፍሱ እየቃዠች መሆኗን መረዳት አያዳግተንም፡፡ አለበለዚያ ግፍ በመሥራት ላይ የቆመ የወሮበሎች መንግሥት  “ገበሬው ግፍ ብንፈጽምበትም ይሸከመናል” ብሎ መናገሩ ምን ትርጉም ይኖረዋል? አንድ ጤነኛ ሰው ከመሬት ተነስቶ “በጥፊ ባጮልህና ዐይንህን በጉጠት ባወጣውም እንደማትቀየመኝ አውቃለሁ! ከኔ በበለጠ ሊያሰቃይህ የሚችል ወገን እንደሌለ ስለማውቅ ለስቃይ ለስቃይ እኔው እሻልሃለሁና ምርጫህ እኔው ብቻ ልሆን ይገባኛል” ብሎ እንዴት ሊናገር ይችላል? እንዲህ ብሎ የሚናገር ሰው ካለ ደግሞ እንደበረከት የለዬለት በሽተኛ እንጂ ጤናማ ሰው ሊሆን አይችልም፡፡ ከወፈፌና በሽተኞች ንግግር ይሠውረን፡፡ “ዱባ ካላበደ ቅል አይጥልም” አሉ? የሚገርም በረከት ነው የሆነብኝ እባካችሁን፡፡
ይህን ንግግር በቁሙ መረዳት እንደሚቻለው በረከት ማለት ቅል ራስና እሚናገረውን እንኳን የማያውቅ ገልቱ ሰው ነው፡፡ ለመደዴ የቃላት አጠቃቀሜ ይቅርታ ይደረግልኝና እንደዚህ ያለ ድፍን ቅልና ባልጩት ራስ የኢትዮጵያ አንዱ ባለሥልጣን እንደነበረ በነገው የታሪክ መዝገባችን ሠፍሮ ሲታይ በቀጣይ ትውልዶቻችን ዘንድ በእጅጉ ከምናፍርባቸው የታሪክ ስብራቶቻችን መካከል አንዱና ትልቁ ነው፡፡ ሰው ምን ቢጃጃል እንደዚህ አይናገርም ወይም አይጽፍም፤ አለበለዚያም አብዷል ማለት ነው፡፡ “አፍ ሲከፈት ጭንቅላት ይታያል” የሚባለው እኮ እንደዚህ ያለ በደናቁርት አስተሳሰብ የተለወሰ የአነጋገር ጭቅቅት ሲያጋጥም ነው፡፡ ተመልከቱልኝ፡-
“መንግሥት ሠልፍ ውጣ ቢለው ይወጣል፤ ተኛ ቢለው ይተኛል፡፡”
ምን ማለት ነው? ገበሬውን በማስገደድም ይሁን በማታለል ሠልፍ ማስወጣት ይቻል ይሆናል፡፡ ነገር ግን እንዴት ነው እንደሕጻን ልጅ ገበሬውን በትዕዛዝ አባብሎ ማስተኛት የሚቻለው? ምን ዓይነት ዕብሪትና ትምክህት ነው? ምን ዓይነት የድንቁርና አነጋገር ነው? ለነገሩ ወያኔዎች ከአለቃቸው ከመለስ ጀምሮ ለአነጋገራቸው ደንታ የላቸውም፤ የሚያስቡት እንደጤናማ ሰው በጭንቅላት ሣይሆን እንደ አውሬ በጡንቻ ሣይሆን አይቀርም – አውሬ በጡንቻው ካሰበ፡፡ ሀገር፣ ታሪክና ወገን አለን ብለው ራሳቸው ስለራሳቸው የሚያምኑ አይደሉም፤ ባህል የላቸውም፤ ሞራል ወይም ‘ethical values’  ብሎ ነገር አያውቁም፤ ምናልባት ከሴቴኒዝም በስተቀር ሁነኛ ሃይማኖትም ያላቸው አይመስሉም (ለዚህም ይመስላል ወንጀለኝነት የሚያዝናናቸውና በሰዎች ስቃይ የሚደሰቱት)፤ በትውፊትና በወግ ልማድ አያምኑም፤ ባጭሩ ወፍዘራሽ የመርገምት ውጤቶች ናቸው፡፡ ከሁሉም ነገር የወጡና ከዜሮ መጀመር የሚወዱ በፈረንጅኛው አገላለጽ nihilists ናቸው – hedonist የሚል ምርቃትም ማከል ይቻላል፡፡ ታሪክን ማጥፋትና ነባር ባህልን ማውደም ያረካቸዋልና፡፡
ወያኔዎች ማለት ባጭሩ ማሊ በምትባለዋ አፍሪካዊት ሀገር ‹አዛዋድ› በሚል ራሳቸው በፈጠሩት አዲስ ግዛት ውስጥ ፈረንሣይ ድምጥማጣቸውን እስክታጠፋቸው ድረስ ለተወሰነ ጊዜ በሼሪዓ ህግ የሚተዳደር እስላማዊ መንግሥት መሥርተው እንደነበሩት የቱዋሬግ አማፅያን  የሚመሰሉ ናቸው – ወያኔዎች እንደሶማሊያው አልሻባብ ዓይነትም ናቸው – ነገር ግን መንግሥት ስለያዙ ደፍሮ በአሸባሪነት የፈረጃቸው ዓለም አቀፍ ኃይል ሊገኝ አልቻለም፡፡ ለነገሩ ወያኔዎች ሀገራዊ አጀንዳ ስለሌላቸውና የማንንም ፀረ-ኢትዮጵያ የሆነ አጀንዳ አንከርፍፈው በተባባሪነት ስለሚጓዙ ለዓለም አቀፍ ታዋቂ ኃይሎች እስትራቴጃዊ ጠቀሜታ እስከሰጡ ድረስ በአጋርነት የሚያስጠጋቸውና ሙሉ ድጋፍ የሚሰጣቸው አያጡም(ኢትዮጵያውያንን ለጊዜውም ቢሆን እያስቸገረን ያለው ይህን መሰሉ የወያኔ እስስታዊ ተፈጥሮ ነው)፡፡ እነዚያ የአልቃኢዳ የአፍሪካ ክንፍ የሆኑ አማጽያን በቲምቡክቱ ውስጥ የነበሩ ዕድሜያቸው በሺዎች ዓመታት የሚገመት የታሪክ ቅርሶችን በዶማና አካፋ እንዲሁም በግሬደር በአጭር ጊዜ የሥልጣን ቆይታቸው ውስጥ ድራሻቸውን ማጥፋታቸውን የቅርብ ጊዜ ትዝታ በመሆኑ ከዐይነ ልቦናችን ገና አልተሰወረም፡፡ ወያኔዎችም እያዋዙ በእስከዛሬው የኃይል አገዛዛቸው እጅግ በርካታ የኢትዮጵያ ቅርሶችንና ታሪኮችን አጥፍተዋል – ከሁሉም የሚብስ ጥፋታቸው ግን ከቁሣዊው ይልቅ ሥነ ልቦናዊውና  ኅሊናዊ ወመንፈሣዊው አጠቃላይ ውድመት የበለጠ ኪሣራ ያደረሰብንና ለማገገምም ብዙ ጊዜ የሚወስድብን ከባዱ ጥፋት ይመስለኛል፡፡ እነዚህ ናቸው እንግዲህ ጅብ እማያውቁት ሀገር ሄዶ ቁርበት አንጥፉልኝ እንደሚል በምናውቃቸው ምሥኪን ዜጎች መሀል ሆነው ገበሬው የነሱ እንደሆነ የሚሰብኩን፡፡ ለነገሩ ጅብ እንኳን በማያውቁት ሀገር ነበር ተናገረው የተባለውን የተናገረው፡፡ ወያኔዎች ግን ዐይናቸውን በጨው አጥበው እኛው ፊት ሸፍጣቸውንና የሀሰት ቱሪናፋቸውን ካለተቀናቃኝ ለብቻቸው በተቆጣጠሩት ሚዲያቸው ያናፉብናል፡፡
የኢትዮጵያ ገበሬ ኑሮው ምን ይመስላል?
በአሁኑ ወቅት በወያኔ ሥርዓት እንደገበሬው የሚማረር የለም፡፡ የወያኔን የውሸት ፕሮፓጋንዳ ለወያኔና ወያኔያውያን ትተን እውነቱን ብቻ እናውራ ካልን የገበሬው ኑሮም ሆነ የአጠቃላዩ የሀገሪቱ ሕዝብ ሕይወት ያሳዝናል ብቻ ሳይሆን ያስለቅሳል፡፡ እኔ ይህን መልእክት የምጽፍላችሁ ዜጋ በሀገር ቤት የምኖርና አልፎ አልፎ ወደገጠር ለሥራ ጉዳይ ወጣ የምል በዚያም ምክንያት የብዙ አካባቢዎችን ነዋሪዎች ሰቆቃና የዕለት ከለት ውጣ ውረድ የምታዘብ ሰው ነኝ፡፡ ስለዚህም የምለው ነገር በስማ በለው የተገኘ ሳይሆን በራሴም ሕይወት እየደረሰ ያለ እውነተኛ ሰቆቃ መሆኑን ላስታውስ እፈልጋለሁ፡፡ የገበሬው ኑሮ ከእኛ ከከተሜዎቹ የባሰ እንጂ የተሻለ እንዳልሆነ በውነት እመሰክራለሁ፡፡
የአንድ አምባገነን መንግሥት ትልቁ ሕዝብን የመግዣ መሣሪያ ሌላ ሳይሆን በማይምነትና በድንቁርና ሸብቦ በማስፈራራትና በማስራብ አንቀጥቅጦ ወደተናጋሪ እንስሳነት መለወጥ ነው፡፡ ወያኔም እያደረገ ያለው ይህንኑ ነው፡፡ በየትኛውም የኢትዮጵያ አካባቢ ብትሄዱ ለይስሙላ ትምህርት ቤቶች ይሠሩ እንጂ ጥራቱን የጠበቀ ትምህርት ባለመኖሩ መማር ካለመማር የሚለይበትን መሠረታዊ ነጥብ ፈልጋችሁ ልታገኙ አትችሉም፡፡ በመሆኑም ገበሬው ከትምህርት ርቋል፤ የጨለማ አዘቅት ውስጥም ከገባ ቆይቷል፡፡ በማይምነት አለንጋ እየተገረፈ፣ በብጥቅጣቂ እርሻ ላይ በሚዘራት አነስተኛ ሰብል እየተሰቃዬ፣ ከዚያችም ሰብል ላይ ከፍተኛ ግብር እንዲከፍል እየተገደደና ከብቱንና ንብረቱን ሸጦ ግብር እንዲያስገባ እየተጠየቀ የሚገኝ ገበሬ ወያኔን ጣዕረሞት ሲይዘው “በፍቅርና በትግስት ይሸከመዋል” ሳይሆን “የወያኔን ሬሣ ተሸክሞ ወደመቃብሩ ይሸኘዋል” ቢባል ነው ትክክለኛው፡፡  ገበሬው በቀን አንድ ጊዜም የሚቀምሰው በሌለበት ሁኔታ፣ ገበሬው የልጁን ወስፋት የሚሸነግልበት አንዳችም እህልና ጥሪት አልባ በሆነበት ሁኔታ፣ ገበሬው ከገጠር እየፈለሰ ወደከተሞች በመግባት ለወያኔ ሕንጻና ፋብሪካ ግንባታዎች የቀን ሠራተኛ እየሆነ ባለበት ሁኔታ፣ ገበሬው ልጆቹ ወደዐረብ ሀገር እየተሰደዱ ለዐረብ ጀማላ የሠይፍ እራትና የአስገድዶ መድፈር ሲሳይ እየሆኑ ባሉበት ሁኔታ፣ ገበሬው በማዳበሪያ ዕዳ የስንግ ተይዞ ኤሎሄ እያለ በሚገኝበት ሁኔታ፣ ገበሬው በአድሎኣዊ የመሬት ሥሪት ምክንያት መድሎ እየተሠራበት ማለፊያው የውሃ መሬት ለካድሬዎችና ለወያኔዎች እየተሰጠ ጭንጫውና መናኛው መሬት ግን ለድሃ ገበሬ እየተሸነሸነ ባለበት ሁኔታ፣ገበሬው ከማሳውና ከመኖሪያው እየተፈናቀለ መሬቱ በልማት ስም ለወያኔ ከበርቴዎች እየተቃረጠ ባለበት ሁኔታ፣ አህያ የተጫነችውን እንደማትበላ ሁሉ ገበሬውም ያመረተውን ምርት ለዕዳ ክፍያ ሲል ለጠገቡ የወያኔ ‹ልማታዊ ባለሀብቶች› በርካሽ እንዲሸጥና ጨርቁ በላዩ ላይ አልቆ በባዶ እግሩ እየሄደ በእሾህና በእንቅፋት አሣሩን እንዲበላ ተፈርዶበት ባለበት ሁኔታ፣ … በረከት የተናገረውን መስማት በርግጥም ተዓምር እንጂ ሌላ ምን ሊሆን ይችላል? በቀደመው ዘመን “እስመ አልቦ ነገር ዘይሰአኖ ለእግዚአብሔር” ነበር ሲባል እምንሰማ፡፡ አሁን ደግሞ “እስመአልቦ ነገር ዘይሰኣኖ ለወያኔ”ብንል እንሳሳት ይሆን? ወያኔ ጥቁሩን ነጭ፣ ነጩን ጥቁር፤ ልቅሶን ሠርግ፣ መርዶን ብሥራት ማድረግ የሚችል ልዩ ምትሃት ያለውና በአፍ ጤፍ የሚቆላ ፍጡር ነው፡፡ ወያኔን ለሚያውቅ የወያኔ ዲስኩርና ፕሮፓጋንዳ  ችግር የለውም – በወያኔ ፕሮፓጋንዳ የሚጃጃል ወያኔን የማያውቅ ወይም ማወቅ የማይፈልግ ብቻ ነው፡፡ ‹ብታምኑም ባታምኑም የኢትዮጵያ ሕዝብ ወያኔን ከእግር እስከራሱ ጠንቅቆ ያውቀዋል!›፡፡ እናም በተለይ በአሁኑ ወቅት ወያኔ ማንንም ሊያታልል በማይችልበት ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ሞቶ በሞቶ እርግጠኛ ሆኜ እናገራችኋለሁኝ፡፡
እናም ወያኔ ስለገበሬው የሚያወራውና እኛ ስለገበሬው የምናውኧው፣ ገበሬውም ስለወያኔ የሚለውና ስለራሱም ከራሱ ኑሮ የሚስተዋለው ለዬቅል መሆናቸውን ልብ ማለት ይገባል፡፡ ‹ይሉሽን በሰማሽ ገበያ ባልወጣሽ› ይባላል፡፡ በረከት የሚናገረው ለሌሎች ብቻም ሳይሆን ለራሱም ሀሰት መሆኑን ማንም አያጣውም፡፡ በረከትን በማታው ‹ክብ ጠረጴዛ› አግኝተን “ምነው ወዲ ስምዖን፣ እንደዚያ ያለ ነጭ ውሸት ማናፈስ ደግ ነው እንዴ ? ለመሆኑ አንተስ ታምንበታለህ? ኅሊናስ የሚባል ነገር የለ(ህ)ም እንዴ?” ብንለው መልሱ ቀላል ነው፡፡ “ወንድሜ፣ በፖለቲካ ኅሊና ብሎ ነገር የለም፡፡ ዋናው ማምለጥ ነው፡፡ የምታደርገውን አድርገህ፣ የምትናገረውን ተናግረህ በፊትህ ከተደቀነብህ ችግር ማፈትለክ እንጂ ስለምትናገረው ነገር እውነትነት ከተጨነቅህ ፖለቲካ ውስጥ ቀድሞውን መግባት የለብህም፡፡ በተለይ እንደኛ ዓይነቱን ችግር ለጠላትም አይስጥ ወንድሜ፡፡ የገባንበት አጣብቂኝ በቀላሉ የሚወጡት አይደለም፡፡ መጥኖ መደቆስ አስቀድሞ ነበር ወዳጄ፡፡ በደም ጨቅይተናል፤ በሙስና በክተናል፤ በዘረኝነቱም ረገድ ያጠፋነውን ጥፋትም ቆም ብለው ሲያስተነትኑት የአንጎልን ሚዛን የሚያዛባና የሚያሳብድ ነው፤ ወደትግል ከገባንበት ጊዜ ጀምሮ የገደልነውና ለስደትና ለእሥራት የዳረግነው ዜጋ የኅሊና ዕረፍት እያሳጣ መቆሚያ መቀመጫ ያሳጣናል፤ ለዚህም ነው ብዙዎቻችን ቢሯችን ውስጥ ሣይቀር በብርጭቆ ውስጥ መደበቅን የምንመርጠው፡፡ ሰው ወዶና ፈቅዶ ጉበቱን በመጠጥ ቦጫጭቆ ሞትን በራሱ አይጋብዝም፡፡ ታዲያ አሁን ምን እናድርግ? ነገር የተበላሸው ዱሮ ነው፤ አሁን ሁሉም ነገር ጠርዝ ከለቀቀ በኋላ ከመዋሸትና ከማምታታት ውጪ ምን አማራጭ አለን? አንድ ነገር ሲገቡበት ቀላል ነው፤ ለመውጣት ግን ከባድ ነው፡፡ የኛ ወደዚህ ሥፍራ መምጣትና አንድ ሰው ወደአደንዛዥ ዕፅ ሱስ መግባት ሂደቱ ተመሳሳይ ነው፤ ሁለታችንም እንደዋዛ እንገባለን – እንደዋዛ መውጣት ግን ለሁለታችንም ከባድ ነው፡፡…” አዎ፣ በረከት በዊስኪ ጨዋታው ለሁነኛው ልክ እንደዚህ እንደሚያጫውተው ‘subconscious’-ኡን በርቀት በማንበብ መረዳት ይቻላል፡፡ አንዳንድ ጊዜ ለወደቀም ማዘን ተገቢ ነው፤ ‹ለሚወድቅ› ብላችሁ ልታሻሽሉትም ትችላላችሁ፡፡ እንደኔ ግን ወያኔዎች ሲነሱ ነው የወደቁት፡፡ ሰው ሲወለድ ነው የሞተው እንደምንል መሆኑ ነው፡፡ ወያኔዎችም ክፋትን መሥራት ሲጀምሩ፣ በቂም በቀል የተቃኘ የጥላቻ አገዛዛቸውን በስፋት ሲያጧጡፉ፣ ሀገርን ሲሸጡና ሲለውጡ፣ ምድርን በደም ረግረግ ሲሞሉ፣ አማራን ከትግሬ፣ ትግሬን ከኦሮሞ እዬለዩ አንዱን መጥቀምን ሌላውን መጉዳትን ባህላቸው ሲያደርጉ፣ ዳር ድንበርን እንዳወጣ ለባዕድ ሀገራት ሲቸበችቡ፣ ሀገርን ካለመውጫ በር ዘግተው የሚሊዮኖችን እስትንፋስ ሲዘጉ፣ … ያኔ ነው ወያኔዎች ገና በጧት ሳይወለዱ የሞቱት፡፡ እዚህ ላይ የሞት ዓይነት ብዙ መሆኑን ልብ ይሏል፡፡ እንጂ የአሁኑ እስትንፋሳቸውማ በ“ሥልጣን” ካሳለፉት ጊዜ አንጻር ሲታይ የደቂቃዎች ያህል ጊዜ ብቻ የቀራቸው ጉድጓዳቸው የተማሰ ልጣቸውም የተራሰ ስለመሆኑ ጨረቃና ፀሐያቸውን በማየት ብቻ የምንረዳው ነው – ዘመናቸው አልቋል፡፡ … የኔ አይደለም …የርሱ እንጂ፡፡ የፍርድ ሂደቱና ብያኔው ከታች አይደለም – ከላይ እንጂ፡፡
የኢትዮጵያን ገበሬ ኑሮ በረከት አያውቀውም ማለት ዘበት ነው፡፡ የኢትዮጵያን ገበሬ ወያኔ አያውቀውም ብሎ በዚህ ሰውዬ ንግግር መደመምም ከንቱ ነው፡፡ በገበሬው መቀለድ አምሯቸው እንጂ የሚናገሩት ነገር እውነቱ የተገላቢጦሽ መሆኑን አጥተውት አይደለም፡፡
ስለሆነም በረከት የሚለው ነገር “አይሰማም!” እንላቸዋለን ፡፡ በረከት ልፋ ብሎት ተናገረ የተባለውን ይናገር እንጂ የራሱ ስብሰባ አባላት ሳይቀሩ ሲችሉ በግልጥ ሳይችሉ ደግሞ በውስጣቸው ይስቁበታል፡፡ ለዚያውም ከትከት ብለው ነው እሚስቁበት – እንደጅል በመቁጠር፡፡ እርግጥ ነው – በረከት ጅል አይደለም፡፡ ጅል ለመምሰል የቆረጠው ግን ምርጫ በማጣት ይመስለኛል፡፡ አንድ ሰው ፀሐይ የሞቀውን እውነት ለመሸፈን በመሞከር በግልባጩ ለማውራት ከተገደደ አንድም ያስጨነቀው ነገር አለ ማለት ነው፤ አለበለዚያም የመዋሸት ተፈጥሯዊ ጠባይ  አለበት ማለት ነው – ልክ እንደመለስ ዜናዊ፡፡ መለስ ዜናዊ በሣይንስ የተረጋገጠ ላይሆን ይችላል እንጂ በእንግሊዝኛው ‘pathological liar’  የሚባል ዓይነት ግለሰብ እንደነበር መረዳት አይቸግርም፡፡ እርሱ በቲቪ ቀርቦ የሚናገራቸውን ንግግሮችና መሬት ላይ ይታይ የነበረውን እውነት በማስተያየት የዚህን ሰው ውሸት በመናገር የመርካት ጠባይ ወይም የተዛባ ተፈጥሯዊ ባሕርይ በቀላሉ መገንዘብ ይቻል ነበር፡፡ በዚህ መልክ ይህ ተጋቦታዊ ደዌ በትግል አጋርነትና በጥቅም ተጋሪነት ምክንያት ለበረከትም ተርፎ ይሄውና በረከትም አንድም ሰው ላያምነው – አንድም የራሱ ሰው ሳይቀር አምኖ ላይቀበለው – እንዲሁ ድከም ብሎት ሲወሻክት እናደምጠዋለን፡፡ እስከመቼ እየወሻከተ በሰው ስቃይ ሲደሰትና የሰውን ስቃይ ለሚዲያ ፍጆታ ያህል ለከንቱዎች በመሸጥ እንደሚኖር ገና የምናየው ይሆናል፡፡ ወደኅሊናው የሚመለስ አይመስለኝም እንጂ ከተመለሰ ግን የገበሬውም ሆነ የአጠቃላዩ የኢትዮጵያ ሕዝብ ካሉት በታች ከሞቱት በላይ የሆነ የሰቆቃ ሕይወት በሚያሳድርበት የእርግማን መዘዝ እንደይሁዳ ራሱን ሰቅሎ እንደሚገድል አምናለሁ፡፡ ያ ቀን ደግሞ በጣም ቀርቧል፤ ምን አለ በሉኝ እነዚህ ጉዶች የሥራቸውን የሚከፈሉበት ጊዜ በብርሃን ፍጥነት እየገሰገሰ በመምጣት ላይ መሆኑ ይሰማኛል፡፡ ቋቱ ሞልቷል፤ የሚቀረው የሚጠራርጋቸውን ማዕበል የሚያስነሣው የፈጣሪ ፊሽካ ብቻ ነው፡፡
የኃጢኣት ትንሽና ትልቅ ባይኖረውም አንድ ሰው ሰርቆ ቢበላ እርቦት ሊሆን ይችላልና ምንም አይደለም ሊባል ይችላል፤ ቢሳደብ ተናድዶ ሊሆን ይችላል በሚል ይቅርታ ሊደረግለት ቢችል ምንም አይደለም፡፡ ነገር ግን በመንግሥት ሠራሽ ርሀብና በግፈኛ አገዛዝ እያለቀሰ የሚኖርን ገበሬ በሚያስለቅሰው ዘረኛ ሥርዓት ተደስቶና ደልቶት እንደሚኖር በሚያስገርም አነጋገር ሰይጣናዊ ስብከትን በመገናኛ ብዙኃን መልቀቅ ከይቅርታ በላይ ነው፡፡ ብሶቱን ችሎ፣ የሚደርስበትን ግፍና መከራ ተቋቁሞ በሞትና በሕይወት እየተንጠራወዘ በሚኖር ሕዝብ ላይ ይህን የመሰለ ቀልድና ድራማ እየሠሩ መሣለቅ ለዘር የሚተርፍ መራራ ቅጣት ሊያስከትል እንደሚችል በረከትም ሆነ ግብረ አበሮቹ መረዳት አለባቸው፡፡ ይህ መሪር ቀልዳቸው ዛሬና ለነሱ ምንም ላይመስል ይችላል፡፡ ይሁንና እያንዳንዷ የምናደርጋት መጥፎ ነገር ሁሉ ትልቅ ዋጋ ሳታስከፍል እንዲሁ የምትቀር እንዳልሆነች ቀልደኞቹና በኢቲቪ የሚገኙ ሆዳም ወናፎች ሁሉ ሊገነዘቡት ይገባል፡፡ ዛሬ ገበሬውም ሆነ ከተሜው አንደበቱ ተለጉሟል፤ አይናገርም፤ ሊናገርም አይፈልግም፡፡ ሰሚ ስለሌለውና ፈጣሪው ፊቱን እንዳዞረበት ስለተረዳ ሁሉም በዝምታ  ተቀምጧል፡፡ ይህ ማለት ግን ዘመን አይለወጥም፣ ዝም ያለም ሁሉ ደንቆሮና አላዋቂ ነው  ማለት አይደለም፡፡ ወያኔ እንዳልነበር ሁሉ የማይኖርበት ጊዜ ሲመጣ ሊከሰት የሚችለውን ትዕይንት አለማየት ነው፡፡ ያኔ እንደዛሬው እዩኝ እዩኝ እንደተባለ ሁሉ ደብቁኝ ደብቁኝ የሚባልበት ጊዜ መድረኩን ይረከባል፡፡ ጥጋብ ደግሞ ወደራብ መንዳቱ ያለና የነበረ ነው፡፡ የጠገበ የሚራብ የማይመስለው የመሆኑ መጥፎ አጋጣሚ ግን አሳዛኝ የታሪክ ግጥምጥሞሽ እንደሆነ እስካሁን አለ – ሲገርም፡፡ አንዱ ከአንዱ ገመና ትምህርት ቢገበይ፣ የሚነሣው ከሚወድቀው ቢማር ግና የችግሮቻችን መንስኤዎች እንደጤዛ በረገፉ፣ እንደጉምም በበነኑ ነበር፡፡ ይህ አለመታደል እስከመቼ እንደሕግ ሆኖ እንደሚበጠብጠን አላውቅም፤ እስኪ የመጨረሻችን ያድርግልን፡፡
በማጠቃለያዬ ማሳሰብ የምፈልገው ነገር አለኝ፡፡ በረከትም ሆንክ ሌላ ጊዜ ሰጠኝ የምትል ባለሥልጣን ሁሉ ካለፈው ታሪክ ተማር፡፡ የሚያሳዝነኝ ነገር አፄዎቹ ከቀደሙት አፄዎች መማር ሳይፈልጉ ቀሩ፤ ቀሩናም ሕዝብን ሲንቁ ሲንቁ ቆይተው በናቁት ሕዝብ እርግማንና አመፅ ምክንያት እንዳልሆኑ ሆኑ – ዘር እንኳን አልወጣላቸውም፡፡ ደርግም ፈጣሪን ሣይቀር ከድቶና አስከድቶ ራሱን የፈጣሪን ያህል በመቁጠር ሕዝብን ሲንቅና ሲያዋርድ ቆይቶ በናቀውና ባዋረደው ሕዝብ እርግማንና ሁለንተናዊ የእምቢታ አመፅ ሰበብ እንደባቢሎን አይሆኑ ሆኖ ተንኮታኮተ – ስንትና ስንት ዘመናዊ ትጥቅ እያለው አንዱም አላዳነውም፤ ይንቃቸው በነበሩ መናኛ የጫካ ወሮበሎች በቀላሉ ተገፍትሮ ወደቀ፡- መጽሐፉ ‹ንጉሥ በሠራዊቱ ብዛት አይድንም› እንደሚል መዘንጋት አይገባም፡፡ እነዚህኞቹ ፀረ-ኢትዮጵያ ጉጂሌዎችም አይነጋ መስሏቸው የኢትዮጵያ ታሪክ መዝገብና ሕዝቡ ሊሸከሙት ያልተቻላቸው ግፍና በደል በሀገርና በሕዝብ ሠሩ፤ ዋናዎቹ የአገዛዙ ቁንጮዎች በሣምንታት ልዩነት ወደማይቀሩበት የሲዖል ሥፍራቸው ተጓዙ፤ ቀሪዎቹም በመኖርና ባለመኖር አጣብቂኝ ውስጥ ተሰንቅረው ያደርጉትን በማጣት ፈጣሪ ሩህያቸውን ጨርሶ እስኪወስዳት እየተንጠራወዙ ይገኛሉ – ይህን እውነት ማስተሃቀር ፈጽሞውን የሚቻል አይደለም፡፡ ለውስጥ አዋቂዎች ወያኔዎች በሕይወት እንደሌሉ ከገባን ቆይተናል፡፡ በሕይወት ያሉ እንዲመስሉ የሆነው ምናልባት ለበጎ ነው፡፡ እንጂ እንደእውነቱ ወያኔ አከርካሪው የተመታው ዋናውን የሥርዓቱን መሃንዲስ መለስ ዜናዊን ፈጣሪ ባልተጠበቀ ወቅት ገና በ‹ማለዳ ዕድሜ›ው ሲጠራው ነው፡፡ ልብ ከተገኘ “ሁሉም ከእያንዳንዱ፣ እያንዳንዱም ከሁሉም እንዲማር ጊዜ ለመስጠት ተብሎ ነው የወያኔ የማይቀር ኅልፈት አዝጋሚ እንዲሆን የተደረገው” ብሎ ማሰብም ይቻላል – ምንም ነገር ማሰብ በማንም አልተከለከለምና (ወያኔዎች ግን ይህንንም ተፈጥሯዊ መብት ሊነፍጉን ይቃጣቸዋል፤ ኢትዮጵያ ውስጥ እየኖርክ ወያኔን ስለመጣል ወይም በሀገሪቷና በሕዝቡ ላይ የጣሉትን ግፈኛ የአገዛዝ ቀምበር ስለመቃወም “ማሰብ”ም አትችልም – ማሰብህ በዐይነ ውኃህ የፊት-ንባብ ከተደረሰበት በአሸባሪነት ተጠርንፈህ ዘብጥያ ትወርዳለህ)፡፡ ማሰብ በቻልንበት ሃሳብ ውስጥ በጊዜ ሰጪነት የምንጠረጥረውን አካል ደግሞ ለሁላችንም እኩል በሚገባን ቋንቋ አቶ ታሪክ ልንለው እንችላለን፡፡ ታሪክ የሚያዳላ ይመስለናል እንጂ ለማንምና ለምንም በጭራሽ አያዳላም – የራሱ የጊዜ ቀመር እንዳለው ግን ማጤን ተገቢ ነው (እርግጥ ነው – ‹መብሰሉ ለማይቀረው ጭንቅላት እንጨት ይፈጃል› እንደሚባለው አንድ ታሪካዊ ኹነት ተከናውኖ ቀጣዩ ሌላ ኹነት እስኪከናወን የሚኖረው የጊዜ እርዝማኔ በትግስታችንና በሃይማኖታችን ጭምር አሉታዊ ጥላውን ማጥላቱ የማናልፈው የዘመን ቅጣት ይመስላል፤ ማን ነበረች – አዎ፣ ሜሪ አርምዴ – “ፍቅር ያዘኝ ብለሽ አትበይ ደንበር ገተር፤ እኛም አንድ ሰሞን እንደሱ አ’ርጎን ነበር፤› ያለችውን የዘፈን ግጥም አለመዘንጋት የአጽናኝነት ጠቀሜታ አለውና እናስታውሰው፡፡) ዕድሜ ይስጠን ሁሉን እናያለን፡፡ ሌላ ዘፋኝም “እናያለን ገና” ብሏል፡፡ ይህንኑ ዘፈን ልጋብዛችሁና እንለያይ፡፡ ጣሊያኖች ሲለያዩ “አሪቬዴርቺ” ይላሉ – በ“ሰላም ያገናኘን” ለማለት፡፡
ሰበር መርዶ!
ይህን ጦማር ጽፌ የጨረስኩት ሌሊት ነው፡፡ ጧት ወደሥራ ልሄድ ስነሳ እንደወትሮው ሁሉ ቤቴ አጠገብ የሚገኙ ትምህርት ቤቶች ተማሪዎቻቸውን ወደዬክፍላቸውን ከማስገባታቸው በፊት ሰንደቁ አጠገብ አሠልፈው ብሔራዊ መዝሙር በቴፕ ከፍተው ሲያጮኹ ሰማሁ፡፡ ይሄኔ ኮምፒውተሬን ከፍቼ ይህችን ሃሳብ በሰበር መርዶነት ለመሰንቀር ወደድኩ፡፡ የሀገር ሞት ከዚህ በላይ የለም፡፡ በጥንት ጊዜ ብሔራዊ መዝሙር ተማሪው ነበር በስሜት ተውጦ በመዘመር ወደክፍሉ የሚገባው፡፡ አሁን ዕድሜ ለወያኔ አዲሱ መዝሙር ሊያውም በመሣሪያ ብቻ የተቀነባበረው በቴፕ ይዘፈንና ወደክፍል ይገባል፡፡ ዛሬ ዛሬ የኢትዮጵያን ብሔራዊ መዝሙርና ባንዴራ የሚያውቅ ትውልድ እየጠፋ ነው፡፡ ራሱ መለስ ዜናዊ (በሕይወት ኖሮ) ይህን መዝሙር ውጣው ቢባል የሚችለው አይመስለኝም፡፡ ሌሎቹ የወያኔ ባለሥልጣናት ቢጠየቁም የሚያውቁት ስለመሆናቸው እርግጠኛ መሆን አይቻልም – ብቸኛ ዘመዳቸው ሆዳቸው በመሆኑ ስለሀገር ምንነት የሚያውቁት ነገር የለም ማለት ይቻላል፡፡ የሚሰቀለው ባንዴራ ደግሞ የተቀዳደደ፣ የነተበ፣ ቀለሙን የለወጠ፣ ከተሰቀለ የማይወርድና ተበጣጥሶ እስኪያልቅ 24 ሰዓት የሚውለበለብ የማን ሀገር ባንዴራ መሆኑም የማይታወቅ ነው፤ የጥንቱን የባንዴራ አሰቃቀልና አወራረድ ሥርዓት የሚያስታውስ ዜጋ የአሁኑን ሲያይ ያለቅሳል፡፡ ከአዲስ አበባ ወጣ በሚል ቦታ ደግሞ የኦሮሚያ ባንዴራና የኦሮሚያ ብሔራዊ መዝሙር በትምህርት ቤቶች እንደዚሁ በቴፕ ሲዘመር ወይም ልጆች በግዴታ አጥንተው እንዲዘምሩት ሲደረግ ታያላችሁ፡፡ ይህችን የነፃነት ምኩራብ የሆነች የታሪክ አምባ ሀገራችንን እንዲህ ባለቤት ያሳጧት የሰይጣን ልጆች ዋጋቸውን ሳያገኙ ከቀሩ በርግጥም ኢትዮጵያ ፈጣሪ የላትም፡፡ አላስችል ብሎኝ አሁን በእግረ መንገድ ትንሽ ለመናገር ፈለግሁ እንጂ ይህ ጉዳይ ብዙ የሚያናግር ነው – የጋራ የሚባለል አንዳችም ነገር እንዳይኖረን ከፍተኛ የጥፋት ሥራዎች በመሠራታቸው አሁንና ለጊዜው ጠፍተናል፤ አለን እንላለን እንጂ በርግጥም በወኔያዎች ደባና ሤራ የአብሮነት ኅልውናችን አደጋ ላይ ወድቋል – ብዙ የትስስር ገመዶች ተበጣጥሰዋል፡- የጋራ ቋንቋ፣ የጋራ መሪ(ዎች)፣ የጋራ የመከላከያ ጦር፣ የጋራ የፖሊስ ሠራዊት፣ የጋራ ድንበር፣ የጋራ ባህል፣ የጋራ ትውፊት፣ የጋራ ሥነቃልና ሥነ ጽሑፍ፣ የጋራ ቤተ መንግሥት፣ የጋራ መንግሥታዊ መዋቅር፣ የጋራ… የጋራ… የጋራ… የምንለው ነገር እንዳይኖረን ተደርገን አንዳችን አንዳችንን የጎሪጥ እንድናይና እንድንፈራራ ተደርገናል፡፡ ሌላው ሁሉ ቀርቶ የጋራ ስብዕና ወይም የሰውነት ደረጃ እንኳን የለንም፤ አንዱ ከሌላው የበለጠ ሰው ነው – ሌላውም ከአንዱ ያነሰ ሰው ነው፡፡ አንዱ የሰው ዘር ከሌላው በተለዬ ምርጥ ነው – ሌላው ደግሞ ውዳቂና ቢገድሉት የበቃ ነፍሱ ከእንስሳት ነፍስም ሳይቀር ያነሰ ዋጋ ያለው ነው – ሩቅ ተመልካቹ ጆርጅ ኦርዌል ጨርሶታል – “All animals are equal, but some are more equal than the others.”፡፡ በዚህ መልክ በፈረጁን ሰዎች ነው እንግዲህ አጥንታችን ድረስ ዘልቆ በሚጠዘጥዝ መሪር ፈረዖናዊ አገዛዝ እየተቀጠቀጥን የምንገኘው፡፡
ያን ደገኛ ኢትዮጵያዊ የአንድነት መንፈስ ለማምጣት እነቴዲ አፍሮን የመሰሉ የቁርጥ ቀን ልጆች ብቻ ሣይሆኑ ሁላችንም የየበኩላችንን ጥረት ማድረግ ይኖርብናል – ለራሳችንና ለልጆቻችን ስንል፡፡ ከራስ ወዳድነትና ከአህያይቷ የ‹እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል› ያረጀ ያፈጀ አስተሳሰብም ባፋጣኝ እንውጣ፡፡ አርቀን መመልከትን ባህላችን እናድርግ፡፡ ጎርፉ ሳይደርስብን ራሳችንን በኅሊና ጸጸት አጥበን ለመጪው መልካም ኢትዮጵያዊ ዘመን ዝግጁ ሆነን ለመጠበቅ እንሞክር፡፡ በየድረ ገጹ የሚታዬው ዘረኝነት ላይ የተመሠረተ ወያኔያዊ የዱባ ጥጋብ መሰል ቡራከረዩና ወንዝ የማያሻግር ከፋፋይ ፕሮፓጋንዳ ዘመኑን እያገባደደ በመሆኑ የአንዲት እናት ልጆች ነንና እንሶብር፡፡ ወያኔ የጋተንን ብርብራና መቅመቆ ማርከሻ እንፈልግለት፤ “ስሜት-ወለድ” ማስጠንቀቂያየን እዚህም ላይ ልድገመው – “እዩዩኝ ያለ ደብቁኝ ደብቁኝ ይላል”፡፡

Saturday, January 18, 2014

የወያኔን የሚዲያ አፈና ማመከን የጊዜው አጣዳፊ ተግባር ነው

ዘረኛዉ የወያኔ አገዛዝ የአገራችንን በትረ ሥልጣን ከተቆጣጠረበት ጊዜ ጀምሮ ህዝባችን ስለራሱና ሰለአገሩ ምንም አይነት መረጃ ከአማራጭ የመገናኛ ብዙሃን ምንጮች እንዳያገኝ ያሉትን ዕድሎች በሙሉ ድርግም አድርጎ ዘግቶ ኖሮአል።
የወያኔ መሪዎችና ተሿሚዎች በየግላቸው ምንም ቁብ በማይሰጡትና ተቃዋሚዎች እንዲያከብሩት ነጋ ጠባ በሚወተውቱት የአገሪቱ ህገመንግሥት አንቀጽ 29 ዕውቅና ካገኙ የዜግች መብቶች አንዱ ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ ተፈጥሮአዊ መብት ሆኖ ሳለ እየተካሄደ ያለውን የሥልጣን ብልግናና አገሪቱን እያራቆተ ያለውን ዘረፋ በመተቸታቸው ብቻ በአንድ ወቅት እንደ አሸን ፈልተው የነበሩ የነጻ ጋዜጣ አዘጋጆችና አሳታሚዎች በሽብርተኝነት ተወንጅለው ከፊሉ ከአገር እንዲሸሽ ሌላው አፉን ዘግቶ እንዲቀመጥ አለያም የፈጠራ ክስ እየተመሰረተባቸው እስር ቤት እንዲማቅቁ ተደርገዋል። አሁንም በመደረግ ላይ ናቸው። በወያኔ ሃሳብን በነጻነት የመግለጽና የዜጎች መረጃ የማግኘት መብት አፈና የአሜሪካና የጀርመን መንግሥታት በየግላቸው የሚያስተዳድሩዋቸው የአሜሪካና የጀርመን ድምጽ ሬዲዮኖች እንኳ ከጥቃቱ ማምለጥ ስላልቻሉ እነሆ እስከዛሬ ያልተቋረጠ የማጥላላት ዘመቻ ይካሄድባቸዋል።
ዜጎች ሃሳባቸውን በነጻነት መግለጽ ከቻሉና ከየትኛውም መዲያ መረጃ የማግኘት መብታቸው ከተረጋገጠ ሥልጣን ላይ ውሎ እንደማያድር ጠንቅቆ የተረዳው የወያኔ አገዛዝ በዚህ የሚዲያ አፈና ተግባሩ በመቀጠል ከሰሞኑ የኢትዮጵያ ሳታላይት ቴለቪዥንና ሬዲዮን እንዲሁም ህዝብ አልፎ አልፎ ሃሳቡን ለመግለጽ በሚገለገልባቸው ጥቂት የአገር ውስጥ ህትመቶች ላይ የተለመደውን የጥቃት ጅራፉን ለማሳረፍ ታጥቆ ተነስቶአል። ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ላይ በመረጃና ደህንነት መሥሪያ ቤቱ ተዘጋጅቶ የህወሃት ቀድሞ ታጋዳላዮች በሚቆጣጠሩትና እንደግል ንብረታቸው በሚፈነጩባቸው የኢትዮጵያ ቴሌቪዥንና ሬዲዮ የተሰራጨው ዘገባ እንደሚያመለክተው ከአሁን ቦኋላ ማንኛዉም የመንግስት ባለስልጣን፤ የገዢዉ ፓርቲ አባላትና የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎች ምንም አይነት ቃለመጠይቅ ለኢትዮጵያ ሳተላይት ቴለቪዥንና ሬዲዮ እንዳይሰጡ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቶአል። ማስጠንቀቂያውን ተላልፎ በተገኘ ማንም ሰው ወይም ድርጅት ላይ የአሸባሪነት ወንጀል ክስ እንደሚመሰረትበትም ዛቻና ማስፈራሪያ በተለመደው የቃላት ጋጋታ ተገልጾአል።
ይህ ከሰሞኑ የወያኔ ብሄራዊ መረጃ ደህንነትና ኮሚኒኬሽን መስሪያቤት ያወጣዉ ማስጠንቀቂያ አዘል መግለጫ የሚያሳየን ነገር ቢኖር ወያኔ ኢትዮጵያ ዉስጥ ዜጎች የሚናገሩትን ፤ የሚጽፉትን፤ የሚያነቡትንና የሚሰሙትን ብቻ ሳይሆን የሚያስቡትንና ሊደግፉት ወይም ሊቃወሙት ይችላል ተብሎ የሚጠረጠረውን ሁሉ አስቀድሞ ለመቆጣጠር ፍላጎቱ ያለው መሆኑን ነው።
ከሰሞኑ መግለጫ የተለየ ነገር ቢኖር ህዝባችንን በፍርሃት አንገት ለማስደፋት ሲባል የወያኔ ፓርላማ በሽብርተኝነት የፈረጀውን ንቅናቄያችንን ግንቦት 7ንና የኢትዮጵያ ሳተላይት ቴለቪዥንን በአንድነት የመፈረጅ ስልት ይፋ መደረግ መቻሉ ብቻ ነው።
የወያኔን ቁንጮዎች ጨምሮ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ይገነዘበዋል ብለን እንደምናምነው የኢትዮጵያ ሳተላይት ቴለቪዥን ኢሳት የተቋቋመው የአገራቸው ጉዳይ የሚያንገበግባቸው ቅን ዜጎች ባዋጡት የገንዘብ መዋጮና በሚሰጡት ያልተቋረጠ የእውቀትና የፋይናንስ ድጋፍ ነው። ተቋሙ ከተመሠረተበት ጊዜ ጀምሮ ላለፉት 22 አመታት በወያኔ የሚዲያ ሞኖፖሊ ተይዞ የኖረውን የአገራችንን አየር ክልል ሰንጥቆ በመግባት ህዝባችን ስለ አገሩና ስለራሱ ጉዳይ በቂ መረጃ እንዲያገኝ በመጣር ላይ ያለ ብቸኛ መገናኛ ብዙሃን ሆኖ በማገልገል ላይ የሚገኝ ነው።
ሃቁ ይሄ ሆኖ ሳለ ለምንድነዉ ታዲያ ላለፉት ሁለት አመታት ስብሀት ነጋን ጨምሮ የተለያዩ የገዢዉ ፓርቲ ቱባ ቱባ ባለስልጣናት ሳይቀሩ በተደጋጋሚ ቀርበዉ በስነ ስርኣት የተስተናገዱበትን ይህንን ሚዲያ የወያኔ ፓርላማ ቀደም ሲል በአሸባሪነት ከፈረጀው ንቅናቄያችን ግንቦት 7 ጋር መወንጀሉ ለምን ይሆን ? መልሱ ቀላል ነው። ከአገዛዙ ያልወገኑ ማናቸውም ሚዲያዎች እንደሚያደርጉት ኢሳት ስርጭቱን ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ነጋ ጠባ በኢትዮጵያ ቴለቪዥንና ሬዲዮ የሚደሰኮረው ልማትና ዕድገት ተጠቃሚው ሥልጣንን የሙጥኝ ያሉ የቀድሞ ታጋዳላዮችና የቅርብ ዘመዶቻቸው እንጂ ህብረተሰቡ አለመሆኑን በግልጽ ከማጋለጥ ባለመቆጠቡ ጥርስ ውስጥ ገብቶአል። ከዚህም በተጨማር ለምዕራባዊያን ፍጆታና ድጋፍ ማግኛ በየአምስት አመቱ የሚደረገው የምርጫ ተውኔት ወቅት ስለተቃረበ ተቃዋሚዎች አጋጣሚውን ተጠቅመው በዚህ ሚዲያ ያብጠለጥሉኛል፤ የስልጣን ብልግናውንና የሙስናውን ጉዳይ ይዘከዝኩታል የሚል ፍርሃትና ስጋትም አለው። በእርግጥ ዝክዘካው በይስሙላ ምርጫው ላይ ምንም ለውጥ እንደማያመጣ እኛ የጉዳዩ ባለቤቶች ቀርተን ምዕራባዊያን ለጋሾችም አያጡትም። ሆኖም ግን ወያኔ ፈርቶአል ተረብሾአል። ስለዚህም ኢሳትና አሁን በአክራሪ ድርጅቶች ልሳንነት የተፈረጁት የአገር ውስጥ ህትመቶች ከምርጫው በፊት መጥፋት ይኖርባቸዋል። ያ ካልሆነ በመላው አገሪቱ የሰፈነው የሥልጣን ብልግናና የሃብት ዘረፋ የፈጠረው የኑሮ ውድነት ያስመረራቸው ሚሊዮኖች የመጪውን ምርጫ ውጤት አስታከው ሆ ብለው አደባባይ ሊወጡና የአገዛዙን የሥልጣን እድሜ ለማሳጠር ተቃዋሚዎች ለሚያካሄዱት ትግል መሳሪያ ሊሆኑ ይችላሉ ተብሎ ተፈርቶአል። ግንቦት 7 የፍትህ የነጻነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ ከብዙ የወያኔ ጥቃትና አፈና ተርፈው አገር ውስጥ በመታተም ላይ በሚገኙ 8 መጽሄቶች እና ለኢትዮጵያዊያን ብቸኛ የመረጃ ምንጭ ሆኖ በማገልገል ላይ በሚገኘው የኢትዮጵያ ሳተላይት ቴለቪዥንና ሬዲዮ ላይ የተጀመረውን አዲሱን ዘመቻ በቸልታ አይመለከተውም።
መረጃ ሃይል ነውና አገራችን ውስጥ ፍትህ እንዲሰፍን፡ በመልካም አስተዳደር እጦት ሥር እየሰደደ የመጣው ድህነት እንዲቀረፍና ሰላምና መረጋጋት እንዲፈጠር የሚሻ ዜጋ ሁሉ ወያኔ በሚዲያ ላይ የጀመረውን ጥቃት ለማስቆም ከጎናችን እንዲሰለፍ ግንቦት 7 የትግል ጥሪውን ያቀርባል።
ወያኔ በመረጃና ደህንነት መሥሪያቤቱ አማካይነት ያስተላለፈው የሰሞኑ ማስፈራሪያና ማስጠንቀቂያ በተለይም በሰላማዊና ህጋዊ ትግል ወያኔን መቀየር ይቻላል በማለት አገር ውስጥ የሚንቀሳቀሱትን የፖለቲካና የስቪክ ድርጅቶች መተንፈሻ ለማሳጣት ሆን ተብሎ የተቀነባበረ መሆኑን ህዝባችን እንዲረዳና በህዝባዊ እምቢተኝነት ሴራውን ለማክሸፍ መነሳት ጊዜው ግድ የሚል የወቅቱ አንገብጋቢ የትግል ጥሪ መሆኑን ግንቦት 7 የፍትህና የነጻነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ ያስገነዝባል።
ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ!!!