የአማራ ክልል ም/ ፕሬዚዳንት እና የብአዴን ጽ/ቤት ሃላፊ የሆኑት አቶ አለምነው መኮንን “የአማራው ህዝብ ሰንፋጭ የሆነ ትምክተኝነት የተጠናወተው በመሆኑ በቤንሻንጉልና በሌሎችም ቦታዎች ለመሰደዱ ምክንያት ሆኖታል” በማለት፣ ለብአዴን ነባርና አዳዲስ ካድሬዎች ተናግረዋል።
ካድሬዎቹ “የአማራው ህዝብ ለምን ይሰደዳል? ለምን በእየክልሉ ጥቃት ይደርስበታል? አማራውን ከጥቃት ለመከላከል ለምን ሙከራ አይደረግም በማለት ጥያቄ ያቀረቡ ሲሆን፣ ም/ል ፕሬዚዳንቱ የአማራው ህዝብ በቅድሚያ እንዳይሰደድ ለማድረግ ስራ እየተሰራ ነው፣ ነገር ግን ከተሰደደ በሁዋላም ቢሆንም ሰንፋጭ የሆነውን ትምክህተኝነቱን በመተው ከሌላው ጋር ለመኖር መልመድ አለበት ብለዋል።
አማራው “በባዶ እግሩ እየሄደ የሚናገረው ንግግር ግን መርዝ ነው” ያሉት ምክትል አስተዳዳሪውና የብአዴን የጽህፈት ቤት ሃላፊው፣ ይሄ መርዝ ንግግሩ አንድ የሚያደርግ አይደለም ሲሉ አክለዋል።
ከኢትዮጵያውያን ጋር አብሮ ለመኖር አማራው የትምክህት ለሃጩን ማራገፍ አለበት ያሉት አቶ አለምነው፣ ይሄ ለሃጭ ሳይራገፍ በጋራ መኖር አይቻልም ሲሉ ድምድመዋል።
ማንኛውም ስም ያወጣ ሙትቻ ፓርቲ ሁሉ መንገሻው አማራ ክልል ነው ያሉት ምክትል ፕሬዚዳንቱ፣ ምክንያቱንም ሲገልጹ ትምክህትን እንደ ምግብ ስለሚመገበው ነው ብለዋል። ያንን ምግብ እየተመገበ እንደሚያቅራራም ገልጸዋል።
አንዳንድ የብአዴን አባላት የምክትል ፕሬዚዳንቱ ንግግር እጅግ እንዳበሳጫቸው ለኢሳት ተናግረዋል።
የብአዴን ካድሬዎች አንቀጽ 39 ለምን አይወጣም በማለት ላነሱት ጥያቄ፣ እኝሁ ፕሬዚዳንት ሲመልሱ አንቀጽ 39 ባይኖር ኖሮ ኢትዮጵያ ደቡብ ሱዳን እንደሆነቸው ትሆን ነበር በማለት መልሰዋል ። አንቀጽ 39 በህዝቦች ዘንድ መተማመን መፍጠሩን፣ አቶ መለስ ዜናዊ በሞቱበት ጊዜ በገሃድ መታየቱን ም/ፕሬዚዳንቱ ገልጸዋል
No comments:
Post a Comment