ተከሳሾቹ ከግንቦት ሰባትና ከኦነግ ጋር ግንኙነት እንዳላቸው በመዝገቡ ተገልጿል
በፌደራል ፖሊስ ከታሰሩ አራት ሳምንት የሆናቸው ስድስት የድረገጽ ፀሐፊዎች (ጦማሪዎች) እና ሦስት ጋዜጠኞች ትናንት በአቃቤ ህግ የሽብር እና የአመጽ ክስ የቀረበባቸው ሲሆን፤ በክሱ ላይ አስተያየት ለመስጠት ለሐምሌ 28 ቀን ተቀጠሩ፡፡ “ዞን 9” በሚል ስያሜ የሚታወቁት ስድስቱ ጦማሪዎች እና ሦስቱ ጋዜጠኞች፤ በድብቅ (በህቡዕ) ተደራጅተው ሲሰሩ ቆይተዋል በማለት የገለፀው አቃቤ ህግ፤ ህቡዕ የተባለው ድርጅት “ዞን 9” ይሁን ሌላ በስም አልጠቀሰም፡፡ የግል የመልእክት ልውውጦችን በሚስጥር የመጠበቅ ዘዴ በአገር ውስጥና በውጭ ስልጠና ወስደዋል በማለትም አቃቤ ህግ ሁሉንም ተከሳሾች ጠቅሷል፡፡ ስልጠናዎቹ በማን እንደተሰጡ ባይገለጽም፤ ፀሐፊዎቹና ጋዜጠኞቹ በአለም አቀፉ የፕሬስ ነፃነት ተቋም (አርቲክል 19) አማካኝነት፤ ለጋዜጠኞች የሚዘጋጅ የመረጃ አጠባበቅ ስልጠና ወስደዋል ተብሎ ሲዘገብ ከነበረው ስልጠና ጋር የሚገናኝ መሆን አለመሆኑ በግልጽ አልታወቀም፡፡ አቃቤ ህግ በስም ዝርዝር ባቀረበው ክስ፤ ተከሳሾቹ ተቃውሞና አመጽ እንዴት ማካሄድና መቀስቀስ እንሚደቻልም ሰልጥነዋል ብሏል፡፡
በተከሳሾቹ ኮምፒዩተር፣ ፍላሽ ዲስክ ወይም በመኖሪያ ቤት የተለያዩ የፖለቲካ ጽሑፎች እንደተገኙ የጠቀሰው አቃቤ ህግ፤ በግንቦት ሰባት ወይም በኦነግ የተሰራጩ ጽሑፎችን አግኝቼባቸዋለሁ ብሏል፡፡ ጽሑፎቹ ከተከሳሾቹ የጋዜጠኝነት ሙያ ጋር የተያያዘ መሆን አለመሆን በእርግጠኝነት ለማወቅ እንዴት እንደሚቻል በክሱ ውስጥ ባይጠቀስም፤ አቃቤ ህግ ጽሑፎቹ የግንቦት ሰባት አስተሳሰብና እቅድ መቀበልን እንደሚያሳዩ ያመለክታል ብሏል፡፡
በዘጠኙ ታሳሪዎች እና በውጭ አገር በምትገኘው ሶልያና ሽመልስ ላይ የቀረበው ክስ ተመሳሳይ ቢሆንም፤ ሶልያና እና ሌሎች ሦስት ተከሳሾች በቀጥታ ወይም በተዘዋዋሪ ከግንቦት ሰባት ጋር ግንኙነት ፈጥረዋል ተብሏል፡፡ በአንድ ተከሳሽ ላይ ደግሞ፤ ለአመጽ በሚውሉ ተቀጣጣይ ነገሮች ላይ ስልጠና ወስዷል የሚል ሃሳብ በክሱ ውስጥ ተካትቷል፡፡ አቃቤ ህግ በአስር ገጽ ካቀረበው ክስ ጋር፣ ማስረጃ ይሆኑኛል የሚላቸው በመቶዎች የሚቆጠሩ የጽሑፍ ገፆችን አያይዞ አቅርቧል፡፡ ተከሳሾችና ጠበቆች በአቃቤ ህግ በቀረበው ክስ እና የማስረጃ ሰነዶች ላይ አስተያየት ለመስጠት ለሐምሌ 28 ቀን ቀጠሮ ሰጥቷል - ከፍተኛ ፍ/ቤት፡፡
የተከሳሾች ጠበቆች በበኩላቸው፤ በፀረ ሽብር አዋጁ አንቀፅ 3 ከ1-6 ከተዘረዘሩት ወንጀሎች አንዱንም ስላልፈፀሙ ዋስትና የሚያስከለክል ጉዳይ የለም፣ ቋሚ አድራሻ አላቸው፣ ከዚህ በፊት በዋስ ተለቀው አልቀርብም ያሉበት ሁኔታ ስለሌለ የዋስትና መብታቸው ተከብሮ ጉዳያቸውን ይከታተሉ በሚል ተከራክረዋል፡፡
በተለይም የ9ኛ ተከሳሽ የኤዶም ካሳዬ ጠበቃ ዶ/ር ዳንኤል ለገሰ፤ ደንበኛዬ የተከሰሰችበት ሁኔታ በጸረ-ሽብር አዋጁ አንቀፅ 3 ከተዘረዘሩት ውስጥ የፈፀመችው የሽብር ድርጊት ስለሌለ ዋስትና መከልከሏ ከህገ መንግስቱ ጋር የሚጣረስ በመሆኑ ለፌደራል ህገ መንግስት አጣሪ ጉባኤ ጉዳዩ ይላክልኝ ሲሉ ፍ/ቤቱን የጠየቁ ሲሆን አቃቤ ህግ ማሰብ፣ ማሴር፣ በህቡዕ መደራጀት የሚሉት ክሶች በፀረ-ሽብር አዋጁ ተካትተዋል፣ በፀረ ሽብር አዋጁ የተከሰሰ ሰው ዋስትና ተከልክሎ በእስር ይቆይ ስለሚል ጉዳዩን ወደ ህገ መንግስት አጣሪ ጉባኤ ውሰዱልኝ የሚለው መከራከሪያ ህጋዊ መሰረት የለውም ሲል ተከራክሯል፡፡ ጠበቃው አመሃ መኮንን በበኩላቸው፤ “ተደራጁ - አሰቡ” የሚባለው ጉዳይ መብታቸውን ተጠቅመው ተደራጁ እንጂ
የፈፀሙት ወንጀል የለም፣ ዞን ዘጠኝም ቢሆን በተወካዮች ምክር ቤት አሸባሪ የተባለ ቡድን አይደለም፤ ስለዚህ በሽብር አዋጁ ስለተከሰሱ ብቻ ዋስትና አያስከለክላቸውም ብለዋል፡፡ ፍ/ቤቱ ግራ ቀኙን ካዳመጠ በኋላ ዋስትናን በተመለከተ የተካሄደው ክርክር ተገልብጦ የመዝገቡ አካል እንዲሆን ካዘዘ በኋላ፣ የህገ-መንግስት ትርጉምንና ዋስትናን በሚመለከት ብይን ለመስጠት ለሐምሌ 28 ቀን ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡
No comments:
Post a Comment