‹‹መውጫና መግቢያ ሰዓታችሁ መመዝገብ ይጀመራል ተብለናል›› ነዋሪዎቹ
ከትናንት በስቲያ በጨርቆስ አካባቢ አንድ ሰው በአሰቃቂ ሁኔታ ተገድሎ መገኘቱን እና ሌሊት ላይ በቦሌ አካባቢ የተለያዩ የመብት ጥያቄዎችን የሚያስተጋቡ ወረቀቶች በየግድግዳውና የኤሌክትሪክ ፖሉ ላይ ተለጥፈው መገኘታቸውን ተከትሎ በከተማዋ ውጥረት መንገሱን የነገረ ኢትዮጵያ ምንጮች ገልጸዋል፡፡
‹‹አንድ የጨርቆስ አካባቢ ነዋሪ ተገድሎ መገኘቱን ተከትሎ ‹የጨርቆስ ወጣቶች› ተሰባስበው ይህን ድርጊት ይፈጽሙ ይሆናል ብለው በገመቱት ላይ ቁጣቸውን ገልጸው ነበር፡፡ በተለምዶ ካታንጋ ወደሚባል ስፍራ ሄደው ገዳዩን አውጡ ብለዋል፡፡ መኪኖችን ሰባብረዋል፡፡ ካታንጋ ምንም ፍንጭ ሲያጡ ወደ ፊላሚንጎ አምርተዋል፡፡ በዚህ ጊዜ ፖሊስ የተወሰኑትን ይዟል፤ ያመለጡም አሉ፡፡ እስካሁንም ውጥረቱ አለ›› ስትል አንዲት የአካባቢው ነዋሪ ለነገረ ኢትዮጵያ ተናግራለች፡፡
ቀደም ብሎ ተለጥፎ በተገኘው ወረቀትና በሟቹ ምክንያትም ፖሊስና የኢህአዴግ ካድሬዎች የተለያዩ ጫናዎችን በነዋሪዎች ላይ ማሳደር መጀመራቸው ታውቋል፡፡ ‹‹ለስድስት ወራት ችላ ብለውት የነበረው የአንድ ለአምስት አደረጃጀት ስብሰባ አሁን እንደገና ጀምረውታል፡፡ አደረጃጀቱ ስራውን ካቆመና ስብሰባ ካደረግን 6 ወራት አልፈውት ነበር፡፡ ከትላንት ጀምሮ ግን በግዳጅ ጀምረውታል›› ሲሉ ምንጮች አስታውቀዋል፡፡
ምንጮች አክለው እንዳስታወቁት ነዋሪዎችን ፖሊስና ካድሬዎች በስብሰባ በመያዝ የተለያዩ የማሳመኛ ሰበቦችን እንደሚያነሱ ተገልጾአል፡፡ ‹‹ምርጫ ደርሷልና አብረን እንስራ፡፡ 97 የሆነውን ታውቃላችሁ፡፡ ያ እንዲሆን አንፈልግም፡፡ ስለሆነም ሙሉ ሌሊቱን በራችሁ ላይ መብራት ማብራት አለባችሁ፤ የተከራይ መታወቂያ ማየት አለባችሁ፡፡ እያንዳንዷን መረጃ ለፖሊስና ለአንድ ለአምስት አደረጃጀቱ ማቀበል አለባችሁ›› እንዳሏቸውም ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡
በየስብሰባዎቹ በአብዛኛው የሚገኙት ሴቶች መሆናቸው የተገለጸ ሲሆን፣ ነዋሪዎች በግዳጅ በተፈጠሩት የአንድ ለአምስቱ አደረጃጀቶች መሪ ለመሆን የሚፈልግ አለመኖሩንም ምንጮች ተናግረዋል፡፡
‹‹እያንዳንዱ ሰው የሚወጣ የሚገባበትን ሰዓት መመዝገብ ይጀመራል ተብለናል›› የሚሉት ነዋሪዎቹ፣ ‹‹አከራዮች ተከራዮቻችሁ የሚገቡበትን ሰዓት ገደብ ማስቀመጥ አለባችሁ፤ የበር መብራቱንም ማጥፋት ክልክል ነው፡፡ ሌሊቱን ሙሉ መብራት ያላበራ ይቀጣል፤ ፍርድ ቤት ሁሉ ሊቀርብ ይችላል›› ተብሎ በየስብሰባዎቹ እንደተነገራቸው የነገረ ኢትዮጵያ ምንጮች ጨምረው አስረድተዋል፡፡
No comments:
Post a Comment