ተለማማጆቹ በህሙማን ላይ የማዘዝ ስልጣናቸው እስከ ምን ድረስ ነው?
ተማሪዎቹ በየሆስፒታሎቹ የሚስተናገዱበት ወጥነት ያለው ሥርዓት የለም
ተማሪዎቹ በሚፈጥሩት ስህተት በህሙማኑ ላይ እስከሞት የሚደርስ ጉዳት ይከሰታል
“በደረሰብኝ ድንገተኛ የመኪና አደጋ ሣቢያ በጥቁር አንበሣ ሆስፒታል ለወራት ተኝቼ ስታከም ነበር፡፡ በእነዚህ ጊዜያትም በሆስፒታሉ ውስጥ ለተግባር ልምምድ ከግል የጤና ኮሌጆች በመጡ ተለማማጅ ተማሪዎች ተደጋጋሚ ችግሮች ሲከሰቱ አስተውያለሁ፡፡ በሆስፒታሉ ቆይታዬ እኔም በቀሪው የህይወት ዘመኔ አብሮኝ ለሚዘልቅ የጤና ችግር የዳረገኝ ግን የህመም ማስታገሻ መድሃኒት በመርፌ ለመስጠት ሙከራ ባደረገች አንዲት ተለማማጅ ተማሪ በእግር ነርቮቼ ላይ የደረሰው ጉዳት ነበር፡፡ በመኪናው አደጋ ጉዳት ለደረሰባቸው አንገቴና የራስ ቅሌ የሚደረግልኝ ህክምና ከፍተኛ ህመምና ስቃይ ስለነበረው የህመም ማስታገሻ መድሃኒት በየአራት ሰዓት ልዩነት እወስድ ነበር፡፡ በዚህም ሳቢያ መድሃኒቱ በመርፌ በሚሰጥበት ወቅት ከሚሰማው ስሜት ጋር ተለማምጄ ነበር፡፡ በተለማማጅ ተማሪዋ መርፌውን የተወጋሁ ቀን የተሰማኝ የህመም ስሜት ግን ፈጽሞ ልቋቋመው የምችለው አልነበረም፡፡ ጩኸቴ አስደንግጧት ከሥፍራው የደረሰች አንዲት መደበኛ ነርስ፤ ተማሪዋን መርፌውን በአግባቡ እንዳልወጋችኝና ይህም በነርቮቼ ላይ ጉዳት ሊያስከትል እንደሚችል በቁጣ ስትነግራት ሰምቼ ነበር፡፡ እንደተባለውም የሁለት ወራት ከአስራ ስምንት ቀን የሆስፒታል ቆይታዬን አጠናቅቄና በመኪናው አደጋ ሣቢያ ከደረሰብኝ ጉዳት አገግሜ ከሆስፒታሉ ስወጣ በእግሮቼ ነርቮች ላይ ዕድሜ ልኬን አብሮኝ ለሚዘልቅ የጤና ችግር መዳረጌን ተገንዝቤአለሁ፡፡ በግራው እግሬ ላይ በደረሰው ችግርም ያለ ድጋፍ መንቀሳቀስ ተስኖች ካለፉት ስድስት ዓመታት ለዚያች ተለማማጅ ተማሪ ያጋለጠኝን ዕድሌን እየረገምኩ እኖራለሁ፡፡ ይህ ጉዳይ ሃይ ባይ ማጣቱና ትኩረት መነፈጉ ሁልጊዜም የሚገርመኝ ጉዳይ ነው፡፡ ሃኪሞች ጉዳቱ ከመኪናው አደጋ ጋር የተያያዘ እንደሆነ በመግለፅ ሊያሣምኑኝ ብዙ ጥረት አድርገዋል፡፡ ይሁን እንጂ በወቅቱ በሥፍራው በነበሩ የህክምና ባለሙያዎች መርፌውን ያለአግባብ በመወጋቴ ምክንያት በእግር ነርቮቼ ላይ ጉዳት እንደደረሰ ተነግሮኛል፡፡ በተለያዩ የግል ክሊኒኮችም ህክምና ሳደርግ ቆይቻለሁ፡፡ ሆስፒታሉ የደረሰውን ችግር ለማድበስበስ ከመሞከር ይልቅ ችግሩ ዳግም እንዳይከሰት ለማድረግ የሚችልበት መንገድ ላይ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት አለበት፡፡ የእኔ አንዴ የሆነ ጉዳይ ነው፡፡ ግን በዚህ መልኩ ተማሪዎቹ በህሙማን ላይ የሚፈጥሩትን የጤና ጉዳት ለማስቀረት ህብረተሰቡ፣ የጤና ባለሙያዎች፣ ኮሌጆቹና መንግስት የሚጠበቅባቸውን ማድረግ ይገባቸዋል፡፡ ችግሩ በሁሉም ሰው ላይ እስኪደርስ ድረስ መጠበቁ አግባብ አይመስለኝም፣ መሸፋፈኑም የትም አያደርስም፡፡ ችግሩን ገልጦ ማየትና መፍትሔ መፈለግ ነው የሚያዋጣው፡፡”
ይህንን ያለችኝ በደረሰባት ድንገተኛ የመኪና አደጋ ምክንያት በጥቁር አንበሣ ሆስፒታል ለወራት ተኝታ ህክምናዋን ስትከታተል የቆየችውና በአካል ድጋፍ (በክራንች) የምትንቀሳቀሰው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሶስተኛ ዓመት የውጪ ቋንቋዎችና ሥነ ጽሑፍ ተማሪዋ ወ/ሪት ኤልሣቤጥ ታምራት ናት፡፡
ከአመት በፊት በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ተፈፀመ የተባለውና ከጉሉኮስ ጋር በተያያዘ የህክምና ስህተት ሣቢያ የተፈጠረውን ችግር በሆስፒታሉ ረዘም ላሉ አመታት በነርስነት ያገለገሉት (ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ) የጤና ባለሙያ ነግረውናል፡፡ “ለተግባር ልምምድ ወደ ሆስፒታል የማመጡት ተማሪዎች ችኩሎች በመሆናቸው አንድን ነገር አይተው ከመማር ይልቅ በተግባር አድርገው ማወቅን ይመርጣሉ፡፡ ይህ ደግሞ ብዙ ዋጋን ያስከፍላል፡፡ በሰው ህይወት ላይ ሙከራ እያደረጉ መማር ማለት እኮ ነው፡፡ ልጆቹን ተከታትሎ የሚመራና የሚያስተምራቸው፣ ማድረግ ያለባቸውንና የሌለባቸውን የሚነግራቸው ሰው ያስፈልጋቸዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ህብረተሰቡ ራሱ ተማሪዎቹ የሚያደርጉትን ነገር በደንብ መከታተል፣ ችግር ያለ መስሎ ከተሰማው ለህክምና ባለሙያው መጠቆም ይገባል፡፡ ያለበለዚያ የሚፈጠረውን ችግር ማቆሙ ቀላል የሚሆን አይመስለኝም” ብለዋል፡፡
በተመሳሳይ ሁኔታ በጋንዲ ሆስፒታል በኦፕሬሽን ለመውለድ ዝግጅት ታደርግ ለነበረች ነፍሰጡር ሴት ካቴተር (አርቲፊሻል የሽንት ማስወገጃ መሣሪያ) ለመግጠም ሙከራ ስታደርግ ስህተት በፈፀመች ተለማማጅ ተማሪ ምክንያት በነፍሰጡሯ ላይ የደረሰው ችግር፣ በራስ ደስታ ሆስፒታል ለላብራቶሪ ምርመራ ደም ለመቅዳት ሞክሮ ባልተሣካለት ተለማማጅ ተማሪ የተፈፀመው ችግር፣ በዘውዲቱ ሆስፒታል በዶክተሩ የታዘዘውን መድሃኒት ከታዘዘው መጠን በላይ እንዲወስዱ በማድረግ የተፈፀመ ስህተት፣ በጥቁር አንበሣ ሆስፒታል በዋናው ሃኪም የታዘዘውን መድሃኒት በሌላ መድሃኒት ቀይሮ በመስጠት የተፈፀመው ስህተት ተጠቃሽ ናቸው፡፡
ለመሆኑ እነዚህና መሰል ችግሮችን እየፈፀሙ የሚገኙትን እነዚህን ተለማማጅ የህክምና ተማሪዎች እንቅስቃሴ የሚከታተል አካል ማነው? ተለማማጅ ተማሪዎቹስ በህሙማን ላይ ያላቸው ስልጣን እምን ድረስ ነው?
የአገሪቱን የህክምና ባለሙያዎች እጥረት ለመቅረፍና የህክምና ባለሙያዎችን ቁጥር ለማሳደግ በሚል ዓላማ በርካታ የግል የጤና ኮሌጆችና ዩንቨርሲቲዎች ተከፍተው ተማሪዎችን በህክምና ሙያ በማሰልጠን ላይ ይገኛሉ፡፡ ኮሌጆቹ የሚያስተምሯቸውን ተማሪዎች በንድፈ ሃሳብና በተግባር በማሰልጠን ብቁ ባለሙያዎች ለማድረግ ጥረት ያደርጋሉ፡፡ ተማሪዎቹ በክፍል ውስጥ የተሰጣቸውን የንድፈ ሃሳብ ትምህርት በተግባር እንዲያዩና የሥራ ላይ ልምምድ እንዲያደርጉም ወደ ተለያዩ የጤና ተቋማት ይልካሉ፡፡ እነዚህ ተለማማጅ ተማሪዎችን ተቀብለው የሚያስተናግዱት የጤና ተቋማት፣ ተማሪዎቹ የሚመሩበትና የሚተዳደሩበት ወጥ የሆነ አሰራርና ደንብ ስለሌላቸው በርካታ ችግሮች እንደሚፈጠሩ ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡ አንድ ስማቸው እንዳይገለፅ የፈለጉ የጥቁር አንበሣ ሆስፒታል የህክምና ባለሙያ እንደነገሩን፤ በአገራችን እንደዚህ ባሉ ጉዳዮች ላይ ጥናት ማድረግ የተለመደ ባለመሆኑ በማስረጃ የተደገፈ አሃዝ ለማቅረብ ቢቸግርም በተለማማጅ የህክምና ተማሪዎች በሚፈፀሙ የህክምና ስህተቶች የደረሱ በርካታ አሳዛኝና አስደንጋጭ ጉዳቶች አሉ፡፡ “ተማሪዎቹ በንድፈ ሃሳብ ያገኙትን ትምህርት በተግባር ለማየትና ራሳቸውን ለመፈተን ከፍተኛ ጉጉት አላቸው፡፡ በዚህም ምክንያት ችኩሎች ሲሆኑ ነገሮችን ተረጋግተው ለማጤን ዝግጁ አይደሉም፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ተማሪዎቹ ለተግባር ትምህርቱ እንግዳ ስለሚሆኑ ድንጉጥና ፈሪ ይሆናሉ፡፡ ይሄ ደግሞ በህሙማን ላይ ችግር እንዲፈጥሩ ያደርጋቸዋል” ብለዋል፡፡
ተማሪዎቹ በህሙማን ላይ ለሚፈጥሯቸው ችግሮች በዋነኝነት የሚጠቀሱት የዕውቀትና ልምድ ማነስ፣ ሁሉንም ነገር የማወቅ ጉጉትና ችኩልነት እንዲሁም በስልጠና ወቅት ተማሪዎችን በመከታተል ችግር እንዳይፈጥሩ የሚቆጣጠር አካል አለመኖር እንደሆኑ የገለፁልን በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የጠቅላላ ህክምና ባለሙያ የሆኑት ዶክተር ዳዊት አለባቸው ናቸው፡፡ ተለማማጅ ተማሪዎቹ በህሙማኑ ላይ ያላቸው የማዘዝ መብትና ስልጣን እስከ ምን ድረስ እንደሆነ በግልፅ የሚታወቅ ባለመሆኑና ስህተት ከመፈፀሙ በፊት እነርሱን ተከታትሎ የሚመልስ ባለሙያ አብሮአቸው የሚመደብበት አሰራር ባለመኖሩ፣ ህሙማን ላይ ጉዳት ሲያደርሱ ማየቱ የተለመደ ጉዳይ ነው” ብለዋል - ሃኪሙ፡
በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል የህክምና ባለሙያ የሆኑና ስማቸው እንዲገለፅ ያልፈለጉ ሌላ አስተያየት ሰጪ በበኩላቸው፤ ችግሩ በስፋት የሚታይና የተለመደ ቢሆንም እርምት ለመውሰድ የሚችል አካል አለመኖሩ ሁልጊዜም የሚያሳስባቸው ጉዳይ እንደሆነ ገልፀውልናል፡፡ በእነዚህ ተለማማጅ ተማሪዎች ጉዳት ደረሰብን የሚሉ ህሙማንን በምን መልኩ መቀበልና ማስተናገድ እንደሚቻል ግራ እንደሚገባቸውም ነግረውናል፡፡ “እንኳንስ ተለማማጅ የጤና ባለሙያ ቀርቶ በህክምና ሙያ ረዘም ያሉ ጊዜያት የሰሩ የጤና ባለሙያዎች በህክምና ላይ በሚፈጥሯቸው ስህተቶች የሚደርሱ ጉዳቶችን ለመፍታት የሚችልና በባለሙያዎቹ ላይ እርምጃ የሚወስድ አካል በሌለበት የጤና ስርዓት ውስጥ የተለማማጅ ተማሪዎቹ የሚፈጥሯቸውን ስህተቶችና ጉዳቶች እንዴት መፍታት እንደሚቻል ግራ ያጋባል” ብለዋል፡፡
ለዚህ መፍትሔ ይሆናል ብለው የሚያስቡት የጤና ጥበቃ ሚኒስቴርም ሆነ ከጤናው ጋር ተያያዥ የሆኑ ጉዳዮች የሚመለከታቸው አካላት በጤና አገልግሎት አሰጣጡ ላይ ጠበቅ ያለ ደንብ ማውጣትና ተለማማጅ ተማሪዎች የሚመሩበት መመሪያ በማውጣት ተግባራዊ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል ይላሉ ባለሙያው፡፡
ከዚህ በተጨማሪም “ተለማማጅ ተማሪዎቹ በታካሚው ላይ የሚኖራቸው የማዘዝ ስልጣን እስከ ምን ድረስ እንደሆነ በግልፅ መታወቅ አለበት፡፡ ይህንንም ራሳቸው ተለማማጅ ተማሪዎቹ፣ የህክምና ተቋሙ፣ የጤና ባለሙያውና ህሙማኑ በአግባቡ እንዲያውቁት ሊደረግ ይገባል፡፡ ተማሪዎቹ ለሚፈፅሟቸው ስህተቶችና ለሚያደርሷቸው ጥፋቶችም ተጠያቂ የሚሆኑበት ስርዓት ሊዘረጋ ይገባል” ብለዋል፡፡ በየሆስፒታሉ በተለማማጅ የጤና ተማሪዎች የሚፈፀሙ የህክምና ስህተቶች በእርግጥም ትኩረት ሊሰጣቸውና ጥብቅ ቁጥጥር ሊደረግባቸው ይገባል፡፡ ችግሩ ህይወትን ያህል ዋጋን የሚያስከፍል ነውና!
No comments:
Post a Comment