በቦሩ በራቃ*
ለራስዎም በወጉ መመከር የነበረብዎት የ‘ጠቅላይ ሚኒስትሩ’ ‘ኣማካሪ’ ኣቶ ኣባይ ፀሃዬ ሆይ! የፍንፍኔን ማስተር ፕላን ተግባራዊነት ኣጉዋተቱ ባሉዋቸው የኦሮሞ ህዝብ ወገኖች ላይ ያቺን ኣነጋጋሪዋን ‘ልክ እናስገባለን’ ቃልዎትን ከሰነዘሩ እነሆ 50 ቀን ገደማ ሆነው። 50 ቀን ማለት ባለስልጣናት ነን ለሚሉት እንደርሶ ላሉ ‘የኣገር መሪዎች’ ቃል ማረሚያ ኣንደ 50 ኣመት የሚቆጠር ረጅም ጊዜ ነው። በቅንነት ተነሳስተው በኣስነዋሪ ንቀት የተሞላውን ቃልዎትን ለማረም ቢፈልጉ ኖሮ ኣይደለም 50 ቀናት የመጀመሪያዎቹ 50 ደቂቃዎችም ከበቂ በላይ ነበሩ።
ነገሩ ግን ወዲህ ነው። ኣቶ ኣባይ ፀሃዬ በወቅቱ ሃዋሳ ላይ በታደመው የግንባራችሁ ጉባኤ ላይ ‘የማስተር ፕላኑን ተግባራዊነት ያጉዋተቱትን የፍንፍኔ ዙሪያ ልዩ ዞን መስተዳድር ባለስልጣናትን ልክ እናስገባለን’ ሲሉ የኦሮሞን ህዝብ ከቁብ ኣልቆጠሩም ነበር። የርሶ ‘ልክ እናስገባለን’ ዛቻ እንደፈጣሪ ቃል ወዲያው ገቢራዊ የሚሆን ኣየመሰልዎት ‘ወደዱም ጠሉም’ እያሉም ጭምር በሃይለ-ቃል ደንፍተው ነበር። ነገሩ ግን እርሶና ግንባርዎ ባሰባችሁት መሰረት የጠቀሱትን የመንግስታችሁ ኣካልና የኦሮሞን ህዝብ ‘ልክ የሚያስገባ’ ሆኖ ኣልተገኘም። እንዲያውም ይባስ ብሎ ይህ መረን የለቀቀው በንቀት የተሞላው ቃላት ኣጠቃቀምዎ ከድሮም ጀምሮ ልቡ ተክፍቶላችሁ የማያውቀውን የኦሮሞ ህዝብ በይበልጥ ኣንቅሮ ኣንዲተፋችሁ ከማገዝ በተጨማሪ በኦፒዲኦ ውስጥ ሳይቀር መቁዋቁዋም የማይቻላችሁን የተቃውሞ ማእበል ኣንደሚያስነሳ የተገነዘባችሁት ከድፍን 50 ቀናት በሁዋላ መሆኑ ነው። ይህ ደግሞ የመንግስታችሁ መንግስታዊ ስነምግባርና ኣደጋን የመቀልበስ ኣቅም ምን ያህል የወደቀ መሆኑን ያስገነዝባል።
ወዲ ፀሃዬ ሆይ! በወቅቱ ቃላት ኣጠቃቀም ላይ ያሳዩት የስነ ምግባር ጉድለት ለመንግስታችሁ ህልውና ምን ያህል ኣደገኛ እንደሆነ ተገምግሞ ማስተባበያ እንዲሰጡበት በድርጅትዎ ታዘው ሰሞኑን ልሳናችሁ በሆነው ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማእከል በኩል ብቅ ብለው የተናገሩት ነገር ብዙዎቻችንን ፈገግ ኣሰኝቷል። ‘ቃሉን (ልክ ኣናስገባለን የሚለውን) ከየት ኣንዳመጡት ኣላውቅም፣ እኔ በበኩሌ እንደዛ ኣላልኩም፣ የተናገርኩት ንግግር ሙሉ ቃል ሰሞኑን ሊሰራጭ ይችላል፣ እዛ ውስጥ ይሄ ቃል የለም’ ነበር ያሉት። ኣይደለም እንዴ? ነገሩ ጅብ ከሄደ ውሻ ጮሄ ኣንዲሉ በሃዋሳው ንግግርዎ ተመስሎ ኣዲስ በዋልታ ስቱዲዮ ውስጥ በቅርቡ የተቀረጸውንና ‘ልክ እናስገባለን፣ ወደደም ጠላም ልክ ይገባል’ የሚሉት እነዚያ ከሃዋሳ የተሰሙት የድንፋታ ቃላት ተገድፈው በምትኩ ስነ ምግባር የታከለበት የማስተባበያ ‘ንግግርዎን’ ለማስተዋወቅ ብቅ ያሉበት ቃለመጠይቅ መሆኑ ነው። ይህን ደግሞ ኣንድ የጎሮቤቴ የ4ኛ ክፍል ጩጬ ተማሪ ሳይቀር ነቅቶብዎታል። ኣይገርምም? በዚህ ዘመን ኣይደለም ሰፊውን የኦሮሞ ህዝብ ጨቅላ የ1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎችን ኣንኩዋን ማታለል ከቶ የማይሞከር መሆኑን ኣዩት?
ሌላው ኣስደማሚ ነገር ደግሞ እርሶ ኣልተናገርኩም ያሉት ‘ልክ እናስገባለን’ የምትለዋ ቃል በንግግሬ ውስጥ ኣልነበረችም የሚሉ ከሆነ ከየት መጣች ብለው ያስባሉ? እርሶንና መንግስትዎን የሚያዋርደው የለየለት ኣስነዋሪ ውሸት ደሞ ይሄ ነው። ኦሮምያ ሚድያ ኔትዎርክ (OMN) ላይ ሰምተውት ከሆነ የድምፅዎት ቅላፄ፣ የትንፋሽዎ ተመሳስይነት፣ የውስጣዊ ስሜትዎ ግለትና የባክግራዉንዱ ድምጸት ኣንድ ላይ ተደምሮ ሲገመገም ቃሉ በፍፁም ባንድ ወቅት ኣንድ ቦታ ላይ ሆነው ባንድ ትንፋሽ የተናገሩትና ቆርጦ-ቀጥል (doctored) ያልሆነና ገሃዳዊ እውነታ ፈጦ የሚታይበት (authentic) ኦዲዮ መሆኑን ለመገንዘብ ኣያዳግትም። ዳሩ ግን ይህን ለማስተባበል 50 ቀን ሙሉ የወሰደባችሁ ያለምክንያት ኣይደለም።
ጉዳዩን ለማስተባበል በጣም ኣስቸጋሪ ኣንደሆነባችሁና በምን መልኩ ቢስተባበል እውነት ሊመስል ይችላል የሚለው ምክክርና ክርክር ሰፊ ጊዜ እንደወሰደባችሁ ያሳብቃል። በመሰረቱ ኣንዴ ያመለጠን ቃል ለማስተባበል ያሉት ኣማራጮች ሁለት ብቻ ናቸው ብዬ ኣስባለሁ። ኣንዱ ያው ኣሁን እንዳደረጋችሁት ሁሉ ‘ቃሉ የኔ ኣይደለም’ ብሎ በድርቅና መዋሸት። ኣልያም የምሬን ‘ለክፋት’ ሳይሆን በቃ ‘ቀልዴን’ ነበር ብሎ መጃጃልና ማጃጃል ነው። የሁለተኛው እንደማይሰራ ሲገባችሁ የመጀመሪያውን ለመምረጥ ተገደዳችሁ። ምክንያቱ ደግሞ ግልፅ ነው። ከ50 ቀናት በሁዋላም ቢሆን ይህን ኣደገኛ ቃል ሳያስተባብሉ መቅረት በዚህ የምርጫ ዋዜማ ኣደጋ ኣለው። ለነገሩ እናንተ ኣትሞክሩትም እንጂ ሶስተኛ ኣማራጭም ነበረ። ማስተባበል ትቶ በኢፋ ይቅርታ መጠየቅ። ‘በወቅቱ ስሜታዊ ሆኜ እንደዛ በመናገሬ ጉዳዩ ያነጣጠረባቸው ወገኖች ብቻ ሳይሆኑ መላው የኦሮሞ ህዝብም ጭምር ይቅርታ ያድርግልኝ። እውነት ለመናገር ማንም ማንንም ልክ ማስገባት ኣይችልም’ ብሎ ማረም በሳልነት ነበረ። ግን እድሉ ያመለጣችሁ ይመስለኛል። 24 ኣመት ሙሉ ኣንድም ጊዜ መንግስታዊ ስህተትን የማረም ክህሎት ያላዳበራችሁ ጉዶች ዛሬ ድንገት ኣይዲያው ከየት ይመጣልና! ሞልቶ የፈሰሰው ትእቢታችሁ ለዚህ ቅንነት የተሞላበት መንግስታዊ ማስተባበያ ኣይፈቅድላችሁም። በበደል ላይ በደል ደርባችሁ መጀመሪያ ያሰማችሁን ዛቻና ድንፋታ ሳያንሳችሁ ኣሁን ደግሞ በስመ ማስተባበያ ኣስነዋሪ ውሸት ትዋሹናላችሁ።
መታወቅ ያለበት ሃቅ ግን በጣም ዘግይታችሁዋል። በተለይም እርሶ ኣቶ ኣባይ ፀሃዬ ከኦሮሞ ህዝብ ላይ እጅዎትን ማንሳት ተስኖዎታል። የቀደመው ድንፋታዎ ሲገርመን በቅርቡም በኦፒዲኦ ውልደትና እድገት ታሪክ ኣስታክከው ሰፊውን የኦሮሞ ህዝብ በጠባብነት ዘልፈዋል። መላው ለማለት በሚቻል መልኩ ኣብዛኛው የኦሮሞ ህዝብ ኦነግን ስለደገፈ ብቻ በርሶ ኣንደበት ‘ጠባብ ህዝብ’ ተብሏል። ይህንንም 50 ቀናት ከቆጠሩ በሁዋላ ነገ ኣስተባብላለሁ ብለው በኣንዱ የመንግስታችሁ ሚድያ ልሳን ብቅ ብለው በሳቅ እንዳይገድሉን ፈራሁ። ለነገሩ እንኩዋን ያን ጊዜ መከረኛው የ ‘ምርጫ’ ጫጫታችሁ ያልፋልና ምን ያስለፋችሁኣል? ስለሆነም እንደገና ተቆጥሮ የማያልቀውን የዘለፋና የድንፋታ ቃልዎን ለማረም ከምርጫው በሁዋላ ዳግም ብቅ ለማለት ኣንደማይገደዱ እርግጠኛ መሆን ይቻላል።
ኣቶ ኣባይ ፀሃዬና ወያኔዎች ሆይ! በቅርቡ ለማሰራጨት ኣስባችሁ ዋልታ ስቱዲዮ ውስጥ የቀረፃችሁት ‘የሃዋሳው ንግግር ሙሉ ቃል’ ኣምሳል ድራማ በኦሮሞ ህዝብ ዘንድ ጨርሶ ተቀባይነት የለውም። በከንቱ ነው የምትለፉት። ለማስመሰል ነው እንጂ እናንተም ታውቁታላችሁ። እንደምታውቁትማ ‘የኦሮሞ ህዝብ በኦነግ ዙሪያ የተሰባሰበ ጠባብ ህዝብ ነው’ ብላችሁ የለም እንዴ? ይህ ማለት እኮ የኦሮሞ ህዝብ ከትላንት እስከዛሬ ድረስ እንደማይደግፋችሁና በጠመንጃ ኣፈሙዝ እየገዛችሁት መሆኑን በይፋ ማመናችሁን ያሳያል። ስለሆነም ኣንድ ጊዜ ቀርቶ ኣንድ ሺ ጊዜ ስቱዲዮ ውስጥ የምትተውኑት የማስተባበያ ድራማችሁ ህዝባችን ዘንድ ተቀባይነት ኣይኖረውም! ከኦሮሞ ህዝብ ጋር የተያያዛችሁት ጠብም ውድቀታችሁን ከማቃረብ በቀር የኣድሜ ገመዳችሁን ኣይቀጥልም።
No comments:
Post a Comment