ጌታቸው ሺፈራው
ከሳምንታት በፊት ከጓደኞቼ ጋር እስክንድር ነጋን ልንጠይቀው ወደ ቃሊቲ አቅንተን ነበር፡፡ በወቅቱ ስለ ለውጥ አውርቶ የማይጠግበውን እስክንድርን ስለ ኢትዮጵያ መጻኢ እድል ስንጠይቀው የመለሰልን ቀላል ግን ደግሞ የሚገርም መልስ ነበር፡፡ እስክንድር ተስፋ አስቆራጭ የሚመስለው ትግል ፍሬያማ ሊሆን እንደሚችልና በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ፖለቲካ የሚነሳው ጥያቄን ልክ እንዲህ ነበር ያስረዳን፡፡
‹‹እነ ጋናን፣ ዛምቢያን፣ እና ሌሎቹንም የአፍሪካ አገራት ነጻ እንዲወጡ ኢትዮጵያ ትልቅ አስተዋጽኦ አድርጋለች፡፡ አብዛኛዎቹ የአፍሪካ አገራት አሁን ነጻ ካወጣቻቸው ኢትዮጵያ የተሻለ ዴሞክራሲ ገንብተዋል፡፡ እኛ እየጠየቅን ያለነው እንደነዚህ አገራት አይነት ስርዓት እንዲሰፍን ነው፡፡ የቅንጦት ጥያቄ አልጠየቅንም፡፡ መጠየቅ ከነበረብን እጅግ ትንሹን ነው እየጠየቅን ያለነው፡፡››
ከሶስት ቀናት በፊት እስክንድር እኛ ነጻ አውጥተናቸው ከእኛ ይሻላሉ ካላቸው አገራት መካከል ቡርኪናፋሶዎች ለስርዓቱ ሌላ ጥያቄ አንስተው ራሳቸው ሲመልሱት ስመለከት ያስታወስኩት እስክንድርን ነው፡፡ እኛ ምንም ጥያቄዎች ሳይመለስልን እነሱ ሌላ ጥያቄዎችን እያነሱ እራሳቸው መመለሱን ተያይዘውታል፡፡
ቡርኪናፋሶ ምንም እንኳ እንደ አብዛኛዎቹ የአፍሪካ አገራት ድሃ ብትሆንም እንደ እኛ 6ና 7 ሚሊዮን ህዝብ አይራብባትም፡፡ ምንም እንኳ እስከ ትናንትና ድረስ በመፈንቅለ መንግስት ስልጣን ላይ የተቆናጠጠ መሪ ያስተዳድራት የነበር ቢሆንም ፓርቲዎችና ህዝቡ ሀሳቡን የሚያንጸባርቅባቸው ሚዲያዎችና ሌሎች ዴሞክራሲያዊ ተቋማትን ዘርግታለች፡፡ ገና እ.ኤ.አ በ1990 ጀምሮ ሬድዮና ቴሌቪዥንን በግል በመያዛቸው ህዝቡ ለአማራጭ ሚዲያ ቅርብ ነው፡፡ ኢንተርኔት ኢትዮጵያ ውስጥ እንደሚደረገው በስርዓቱ አይታፈንም፡፡ ቡርኪናፋሶ እንደ ኢትዮጵያ ጋዜጠኞች በጅምላ እስር ቤት የሚታጎሩባት፣ በገዥው ፓርቲ ጫና የሚሰደዱባት፣ ሚዲያዎች የሚታፈኑባትና የሚዘጉባት አገር አይደለችም፡፡
ባለፉት አመታት ለአጭር ጊዜ ከሶስት የማይበልጡ ጋዜጠኞች ታስረዋል፡፡ ባለፉት 20 አመታት በሚዲያው ታሪክ አስከፊው የሚባለው የአንድ ጋዜጠኛ ባልታወቁ ሰዎች መገደል ብቻ ነው፡፡ በቡርኪናፋሶ ያለፉት 20 አመታት ታሪክ ውስጥ በሚዲያው ጠባሳ ነጥብ ተደርጎ የሚወሰደውና የውጭ ተቋማት ጫና ለማሳደር የሚጥሩበት ጉዳይም የዚህ ጋዜጠኛ ሞት ነው፡፡ ከአምስት አመት በፊት አንድ ጋዜጠኛ የ‹‹እንገድልሃለን›› ማስፈራሪያ ስለደረሰበት ዓለም አቀፍ የጋዜጠኛ ማህበራት አሁንም ድረስ ስርዓቱን በመውቀሻነት ይጠቀሙበታል፡፡ በቡርኪና ፋሶ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ስብሰባ እንዳያደርጉ፣ ሰላማዊ ሰልፍ እንዳይወጡ አይከለከሉም፡፡ የአገሪቱ ሲቪክ ማህበራት ኢህአዴግ መራሹ ‹‹መንግስት›› ስር ካሉት የተለዩ ናቸው፡፡ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችና አባላት በሽብር ስም ወህኒ አይወረወሩም፡፡ በአጭሩ ቡርኪናፋሶ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚጠየቁትን አብዛኛዎቹን የፖለቲካ ጥያቄዎች መልሳለች፡፡
ምንም እንኳ ቡርኪናፋሶ ከእኛ የተሻለ፣ እኛ የምጠይቀውን ጥያቄ የመለሰች ቢሆንም፣ ፖለቲካዊ ስርዓት ብትገነባም በሚፈለገው መንገድ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ሰፍኖበታል ለማለት ግን አያስደፍርም፡፡ ቡርኪናፋሶን ለባለፉት 27 አመታት ያስተዳደሩት ፕሬዝደንት ብላይሴ ኮምፓሬ ወደ ስልጣን የመጡት ተወዳጁን የቀድሞ የአገሪቱን ፕሬዝደንት ቶማስ ሳንካራን አስገድለው ነው፡፡ የገዳዮቹ ቻርለስ ቴለርና ሙአመድ ጋዳፊ የቅርብ ጓደኛም እንደመሆናቸው ለህዝቡ ምቹ ናቸው ማለት አይቻልም፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ሶሻሊስት ከነበረው ቶማስ ሳንካራ የተለየ ሆነው በመገኘታቸው የምዕራባውያን ተላላኪ ሆነው አገልግለዋል፡፡ በተለይ የምዕራብ አፍሪካን አለመረጋጋት ለመቆጣጠር ፈረንሳይና አሜሪካ ቡርኪናፋሶን ተጠቅመውበታል፡፡
እ.ኤ.አ በ1991፣ በ1998፣ በ2005ና 2010 በተደረገው ምርጫ አሸነፍኩ ቢሉም ያልተዋጠላቸው በርካቶች እንደነበሩ ይነገራል፡፡ በፕሬዝዳንትነቱና በፓርቲያቸው ደስተኛ ያልሆኑት ቡርኪናፋሶውያን እ.ኤ.አ በ2011 በርካታ አመጾችን አስነስተው ስርዓቱን አስደንግጠዋል፡፡ ለአብነት ያህል በዚሁ አመት ሰራዊቱ ደሞዜ አልተከፈለኝም ብሎ የጀመረው አመጽ ፕሬዝደንቱ ወደ ተወለዱበት መንደር እንዲደበቁ አስገድዷቸው ነበር፡፡ የህገ መንግስቱ መሻሻል ሀሳብ የቀረበው ከአመት በፊት ሲሆን ተቃሞው ገጥሞት እንደገና ተቋርጦ ቆይቷል፡፡
ከእኛ አገር የተሻለ ግን ደግሞ መሻሻል በነበረበት የቡርኪናፋሶ ዴሞክራሲ ውስጥ ህዝቡ ጥያቄውን ሲያቀርብ ቆይቶ ሰሞኑን አቅሙን አሳይቷል፡፡ ቶማስ ሳንካራን ያህል ተወዳጅ መሪ አስገድለው ስልጣን ላይ የወጡትን ፕሬዝዳንት በሰዓታት ውስጥ ማፍረክረክ ችሏል፡፡ የገዥው ፓርቲ ዋና ጽ/ቤት፣ ቴሊቪዥን ጣቢያው፣ ፓርላማው፣ የባለስልጣናትን ቤትና ሌሎችም የመንግስት ቢሮዎች በመቆጣጠርና በእሳት በማጋየት የጀመረው የተቃውሞው ጎራ የአንድ ቀን ውሎ ህገ መንግስቱን በማሻሻል ስልጣናቸውን ለማራዘም ደፋ ቀና ሲሉ የነበሩት ፕሬዝዳንት ‹‹መንግስትን አፍርሸዋለሁ፡፡ መልዕክቶቻችሁን ሰምቻለሁ፡፡ የሽግግር መንግስት ይቋቋማል›› ብለው የተለየ አቋም እንዲይዙ አስገድዷቸዋል፡፡ ከዛ በፊት ብዙም ቁብ ሰጥተዋቸው ያልነበሩትን ተቃዋሚዎች ‹‹አመጹን እንድታቆሙ እለምናለሁ፡፡ ከዛሬ ጀምሮ ከሁሉም የፖለቲካ ኃይሎች ጋር በመወያየት ችግሩን መፍታት አለብን›› ብለው እንዲማጸኑ ግድ ሆኖባቸዋል፡፡ በስተመጨረሻም በአንድ ቀን የህዝብ አመጽ ስልጣን መልቅቃቸውን ይፋ አድርገዋል፡፡
በቡርኪናፋሶው ገዥ ፓርቲ ላይ የተነሳው አመጽ ሰራዊቱንም ጭምር ያሰባሰበ ሲሆን ቀድሞው የጦር ሚኒስትር ጀኔራል ኩአሜ ሎውጉን ጨምሮ በርካቶች ሰላማዊ ታጋዮችን ተቀላቅለዋል፡፡ ፓርላማ፣ የመንግስት መስሪያ ቤቶችንና የባለስልጣናቱን ቤት ባነደደው እንቅስቃሴ የሞቱት ሰዎች ጥቂቶች እንደሆነ የታወቀ ሲሆን ይህም መከላከያና፣ ፖሊስና ደህንነቱ ከህዝብ ጎን እንደቆመ በግልጽ አሳይቷል፡፡
ከኡጋዱጉ ወደ አዲስ አበባ?
የአረቡ የጸደይ አብዮት በተነሳበት ወቅት ጂቡቲ፣ ሱዳን፣ ዚምባብዌ፣ ማዕከላዊ አፍሪካና ሌሎችም አምባገነኖች ስልጣን ላይ የተቆናጠጡባቸው አገራት ውስጥ ጅምር እንቅስቃሴዎች ተስተውለው ነበር፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ደግሞ ምንም አይነት እንቅስቃሴ
ባልታየበት ስለ ጸደይ አብዮት ያወሩት እነ እስክንድር በሽብርተኝነት ስም 18 አመት ተፈርዶባቸው የእርስ ቤት በር ተቆልፎባቸዋል፡፡ ይህን አብዮት ኢትዮጵያ ውስጥ እንዲከሰት ያደርጋሉ ተብለው የተፈሩ በርካታ የታዋሚ ፓርቲ መሪዎችና ጋዜጠኞም በተመሳሳይ መልኩ ለዘመናዊ ግዞት ተዳርገዋል፡፡
የአረቡን አብዮት ኢትዮጵያ ውስጥ እንዲከሰት ያደርጋሉ ብሎ በርካቶችን የሚያስረው ስርዓቱ በአንድ በኩል የዓረቡ አብዮት ኢትዮጵያ የማይደገምባቸው የሚላቸው ምክንያቶችን በማስቀመጥ፣ በሌላ በኩል ለኢትዮጵያ በእጣ ፈንታ እንደማያዋጣ በማስመሰል ህዝብን ለማሳመን ጥሯል፡፡ ይህ ሁሉ የስርዓቱ ተቃርኖ የህዝቡን ጥያቄ መመለስ ካለመቻሉ የመጣ መደነባበርና ግራ መጋባት እንደሆነ ግልጽ ነው፡፡ በተለይ ስራ አጥነት፣ ሙስና፣ አፈና፣ በአረቡ ዓለም በስፋት የታየና ለአብዮቱም ዋነኛ ምክንያት እንደነበር የሚያውቀው ህወሓት/ኢህአዴግ ኢትዮጵያውያን ያሉበት ተመሳሳይ ሁኔታ እንቅልፍ ቢነሳው የሚገርም አይሆንም፡፡
የአረቡ ዓለም አብዮት ከኢትዮጵያ ጋር ግንኙነት የለውም ሲባል ኢትዮጵያ ከሰሜን አፍሪካ ይልቅ ከሰሃራ በታች ለሚገኙት የአፍሪካ አገራት ቅርበት እንዳላት የሚያመለክት ነው፡፡ ግን አሁን ደግሞ በቡርኪናፋሶ ያ ገዥዎቹን እንቅልፍ የሚነሳው ውሽንፍር ተነስቷል፡፡ እንዲያውም ከእኛ በተሻለ ፖለቲካ ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ ላይ የምትገኝ አገር ውስጥ፡፡
60 በመቶ የሚሆኑት ቡርኪናፋሶውያን ወጣቶች ናቸው፡፡ ኢትዮጵያም ከዚህ ያላነሰ ደግሞም ስራ አጥ፣ በሙስና፣ በአስተዳደራዊ በደል፣ በአፈና አሳሩን የሚያይ ወጣት አገር ነች፡፡ ቡርኪናፋሶውያን እ.ኤ.አ በ2011 አመጽ ወጥተውበት ከነበረው የኑሮ ውድነት በላይ ኢትዮጵያውያን ላለፉት 10 አመታት በዚህ በገዥው ፓርቲ የበላይነት የሚመራው የፖለቲካ ኢኮኖሚያ ካመጣው ጣጣ ጋር ከርመዋል፡፡
የሙስሊሙ፣ ኦርቶዶክሱ፣ ኦሮምኛ፣ አማርኛ፣ ትግርኛ…. ተናጋሪው በአሸባሪነት ሆነ በሌላ ስም እስርና ስቃይ እጣ ፈንታው ሆኗል፡፡ ጋዜጠኞች ስርዓቱ በሚያሳርፍባቸው በትር በጅምላ አገር ለቀው እየተሰደዱ ነው፡፡ መከላከያው ስርዓቱ ካመጣው በማንነት የመከፋፈል አባዜ ባሻገር በሌሎች ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጥያቄዎች እንደተወጠረ በየጊዜው የሚወጡት መረጃዎች ዋቢዎች ናቸው፡፡ የኤርትራ ተቃዋዎች ሰፋፊ ቢሮዎች ተሰጥቷቸው ሲፈልጉ ሰለማዊ ሰልፍ፣ ሲፈልጉ ስብሰባ በሚያደርጉበት አገር የኢትዮጵያ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በገዛ አገራቸው ጽ/ቤት ከማግኘት ጀምሮ፣ ስብሰባና ሰላማዊ ሰልፍ ማድረግ፣ ወረቀት መበተን ቅንጦት ሆኖባቸዋል፡፡
በእርግጥ ኢትዮጵያ ውስጥ እንዲህ ተርፎ የፈሰሰው ግፍ ቱኒስ ላይ የተነሳውን የአረቦችን አብዮት አዲስ አበባ ላይ ይደግማል ተብሎ በመፈራቱ በርካቶች ታስረዋል፡፡ መስቀል አደባባይ ‹‹የኢትዮጵያውያን ታህሪር›› እንዳይሆን በመፈራቱ የኃይማኖት በዓላትና የኢህአዴግ የድጋፍ ሰልፎች ውጭ ተቃዋሚዎች ዝር የማይሉበት ክልክል ቦታ ሆኗል፡፡
የሰሜን አፍሪካ ጎዳናዎች በወጣቶች በተሞሉበት ጊዜ ኢትዮጵያውያን ለዚህ አብዮት ሞተር ከሆነው የማህበራዊ ሚዲያ ጋር የነበራቸው ትውውቅ ከአሁን ካለው አንጻር አነስተኛ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ ህዝቡ ውስጥ የነበረው የኢኮኖሚ ችግር ከጊዜ ወደ ጊዜ ከመባባስ ውጭ የተለየ መፍትሄ አልተሰጠውም፡፡ የህዝብ አገልግሎት ከመቆራረጥ ወደ መጥፋት በመሸጋገሩ ህዝብ በራሱ ሰላማዊ ሰልፍ እስከመውጣት ደርሷል፡፡ የሽሮ ሜዳ ነዋሪዎችን ያስታውሷል!
ቡርኪናፋሶ ውስጥ ስርዓቱን በሁለት ቀን ያስወገዱት ወጣቶች ከ1500 አይበልጡም፡፡ ከዚህ አንጻር በኢትዮጵያ በተቃውሞ ጎራ ያለው ሳይጨምር አርብ አርብ መስጊዶችን በተቃውሞ ሲሞሉት የታዩት ሙስሊሞች ብቻ ለውጥ ሊያመጡ እንደሚችሉ የሚያጠራጥር አይሆንም፡፡ ተቃዋሚዎች የተበታተኑና የፋይናንስ አቅም የሌላቸው በመሆናቸው ኢትዮጵያ ካለው የተቃዋሚ ሁኔታ የተለየ ነገር አይታይባቸውም፡፡ ሆኖም ሰላማዊ ሰልፍም ሆነ ስብሰባ የማድረግ፣ በሚዲያዎች ሀሳባቸውን በመግለጽ ከኢትዮጵያ የተሻለ አጋጣሚ ነበራቸው፡፡
የቡርኪናፋሶው ገዥ ፓርቲ 27 አመት ሲቆይ ህዝብ ደስተኛ ሆኖ አይደለም፡፡ ከዚህ ይልቅ ከኢትዮጵያው ጋር የማይነጻጸር ቢሆንም ከምዕራባውያን ጋር ባለው ግንኙነትና በፈርጣማ ክንዱ ስልጣን ለማስጠበቅ የሚችለውን ሁሉ አድርጓል፡፡ በእነዚህ ሁሉ አመታት ህዝብ ደስተኛ ባይሆንም በሁለት ቀን ይህን ያህል ለውጥ ያመጣል ብሎ የገመተው ግን አልነበረም፡፡ የቡርኪናፋሶ ሁኔታ አፈናም ሆነ በምዕራባውያን ተላላኪነት ራሱን ለማቆየት የሚጥር ስርዓት በህዝብ ኃይል በአጭር ጊዜ ሊሸነፍ እንደሚችል የቅርብ ጊዜ ምስክር ሆኗል፡፡ በተቃውሞው ጎራ ድካም፣ በአፈናው ብዛት እስካሁን ቡርኪናፋሶውያን ያገኙትን መብትና ጥቅም ማግኘት ያልቻለው የኢትዮጵያ ህዝብ በስርዓቱ ላይ ይህ ነው የሚባል ጫና ሊያደርግ እንደማይችል የሚገምቱት ብዙዎቹ ናቸው፡፡
ነገር ግን ሙስሊም፣ ክርስቲያን፣ መምህራን፣ መከላከያ ሰራዊት፣ የራሱ አባል ድርጅቶች ጋር መስማማት ያልቻለው የኢትዮጵያ ገዥው ፓርቲም በህዝብ የሚፈተን ለመሆኑ ትናንት እነ ጋዳፊ፣ እነ ሙባረክና ቤን አሊ ላይ ከታየው ባሻገር የዛሬው የቡርኪናፋሶው ህዝብ ድል ትልቅ ምስክርነት ይሰጣል፡፡ በቱኒስ የተነሳው ለውጥ ከቱኒዚያ ከተሞች አልፎ የግብጹን ታህሪር፣ ትሪፖሊና ሌሎች የሊቢያ ከተሞችን እንዳጥለቀለቀው፣ ስርዓትም እንደለወጠ ሁሉ ኡጋዱጉ ከሚገኘው ፓርላማ የተነሳው እሳትም አገሪቱ ውስጥ የነበረውን የስርዓቱ ቆይታ አውድሞታል፡፡
ጽሁፉን በእስክርንድ እንደጀመርኩት በእሱው መደምደሚያ መጨረስ ወደድኩ! ‹‹በሰሜን አፍሪካው አብዮት እንቅስቃሴዎቹ የተቀጣጠሉት በዋና ዋና ከተማዎቹ ነው፡፡ እኛ አገርም ቢሆን ተመሳሳይ ነው የሚሆነው፡፡ አዲስ አበባ ላይ የሚፈጠር ለውጥ አጠቃላይ የአገሪቱን ፖለቲካዊ ሁኔታ ይቀይራል፡፡… ውሃ በ99ንኛው ዲግሪ ሴንቲግሬድ ነው የሚፈላው፡፡ እስከዛ ድረስ ምንም አይነት ለውጥ አይታይበትም፡፡ ውሃ የሚያፈላ ሰው 99 እስኪደርስ ድረስ ማህል ላይ ተስፋ ቆርጦ ሊተውው ይችላል፡፡ ግን 99 ዲግሪ እስኪደርስ ድረስ የራሱ የሆነ የማይታይ ለውጥ ያደርጋል፡፡ ተስፋ ያልቆረጠ በአንድ ዲግሪ ለውጡን ያየዋል፡፡››
ኦጋዱጉ ላይ ተስፋ ያልቆረጡት 1500 ወጣቶች የለውጡን የመሞቂያ ነጥብ ቀይረውታል፡፡ አዲስ አበባ ውስጥ ኡጋዱጉ ላይ ካለው የከፋ ችግር ቢኖርም እስካሁን 99 ዲግሪ አልደረሰም! ይህ የመፍያ ነጥብ፣ የኡጋዱጉው ውሽንፍር፣ ከአረቡ ይልቅ ለኢትዮጵያ ይቀርባል የሚባለው የጥቁር አፍሪካ ‹‹ጥቁሩ አብዮት›› ወደ አዲስ አበባ መቼ ይደርሳል የሚለውን ለጊዜውም መገመት የሚቻል አልሆነም፡፡ ግን ጭቆና በተትረፈተፈበት አገር ለውጥ ተፈጥሯዊ ነውና ነገ፣ ሳምንት፣ የዛሬ ወር፣ አመት… መከሰቱ ግን የማይቀር ነው፡፡ ገዥዎቹ ለለውጥ ዝግጁ እስካልሆኑ ድረስ ቁጥሩ አንድ ሺህም ሆነ ሚሊዮን የለውጡን ዲግሪ ሴንቲግሬድ የሚቀይረው ሳይታሰብ አደባባይ ላይ የሚገኘው ህዝብ ነው!
No comments:
Post a Comment