Search This Blog

Sunday, June 16, 2024

የብልጸግና መንግስት የሰብአዊ መብት ጥሰቶች


 በኢትዮጵያ በ2023 ከተመዘገቡ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች መካከል 70 በመቶ የሚሆኑት በመንግስት የጸጥታ ሀይሎች የተፈጸሙ ናቸው ስል የመንግስታቱ ድርጅት የሰብአዊ ጉዳዮች ከፍተኛ ኮሚሽን ገለፀ።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ ጉዳዮች ከፍተኛ ኮሚሽን ቢሮ በኢትዮጵያ የሰብአዊ መብት ሁኔታን አስመልክቶ ሪፖርት ይፋ አድርጓል።
ሪፖርቱ በኢትዮጵያ በተለይም በኦሮሚያ ክልል የሚፈጸሙ ሰብአዊ መብት ጥሰቶች አሳሳቢ ናቸው ብሏል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ ጉዳዮች ከፍተኛ ኮሚሽን በፕሪቶርያ የተደረሰውን የሰላም ስምምነት ተከትሎ በትግራይ የነበረው የሰብአዊ መብት ሁኔታ የተሻሻለ ቢሆንም ኢትዮጵያ በ2023 ፈተና የተሞላበት ሁኔታ ውስጥ አሳልፋለች ሲል ገልጿል።
ለዚህም ዋነኛ ምክንያቱ አብዘኛዎቹ የኦሮሚያ እና የአማራ ክልል አከባቢዎች በከፍተኛ ግጭቶች እና ውጊያዎች የተሞሉ መሆናቸው ነው ብሏል።
በዘፈቀደ የዜጎችን መብት መግፈፍ፣ በፖለቲካ ምክንያት የሚደርስ የአካል ማጉደል፣ የወሲብ ጥቃት፣ የመሰብሰብ ነጻነትን መግፈፍ፣ የዘፈቀደ እስር፣ የመናገር ነጻነት መግፈፍ፣ እገታ እና መሰወር የመሳሰሉ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች በኢትዮጵያ በ2023 መመዝገባቸውን አስታውቋል።
በሀገሪቱ በተደጋጋሚ ከተጣሱ ሰብአዊ መብቶች መካከል ዋናዋናዎቹ የዘፈቀደ እስር እና የንጹሃን ግድያዎች መሆናቸውን ጠቁሟል።
የመንግስታቱ ድርጅት የሰብአዊ ጉዳዮች ከፍተኛ ኮሚሽን ቢሮ ይፋ ባደረገው 24 ገጽ ሪፖርቱ እንዳመላከተው በ2023 በኢትዮጵያ 594 የሰብአዊ መብት ጥሰቶች የተፈጸሙ ሁነቶች መመዝገቡን ጠቁሟል።
በእነዚህ በተመዘገቡት የጥቃት ሁነቶችም 8ሺ 253 ኢትዮጵያውያን ተጠቂ መሆናቸውን ገልጿል።
ከቀደመው አመት ጋር ሲነጻጸር የ56 በመቶ የሚጠጋ የሰብአዊ መብት ጥሰት ጭማሪ ታይቶበታል ብሏል።
የጥቃቱ 70 በመቶ ፈጻሚዎች የመንግስት የጸጥታ ሀይሎች ማለትም የሀገር መከላከያ ሰራዊት አባላት፣ የፌደራል እና ክልል ፖሊስ አባላት እና በመንግስት የሚደገፉ የሚሊሻ ታጣቂዎች ናቸው ሲል አስታውቋል።
7ሺ 103 ተጠቂዎች የነዚህ የመንግስት ጸጥታ ሀይሎች ሰለባዎች ናቸው ሲል ጠቁሟል።
በአማራ ክልል እየተፈጸመ ያለው የሰብአዊ መብት ጥሰት እጅግ አሳሳቢ ነው ያለው ሪፖርቱ በ2023 ብቻ 740 ንጹሃን ሰዎች በክልሉ መንግስት ከፋኖ ሀይሎች ጋር እያደረገው ባለው ውጊያ መሞታቸው ተመዝግቧል ብሏል።
በ2023 በኦሮሚያ ክልል የመንግስት የጸጥታ ሀይሎች ከኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ጋር እያካሂዱት ባለው ውጊያ የ366 ንጹሃን ሞት መመዝገቡን እና ከነዚህም ውስጥ 46 የሚሆኑት ሴቶች መሆናቸውን አመላክቷል።
የመንግስታቱ ድርጅት ሪፖርት በተጨማሪ የፌደራል መንግስቱ የመከላከያ ሀይል የድሮን ጥቃት እየፈጸመ መሆኑ እንዳሳሰበው አመላክቷል።
በ2023 በአምስት ወራት ብቻ በመከላከያ ሀይል በድሮን የተፈጸሙ 18 ጥቃቶች መመዝገቡን አስታውቆ በእነዚህም ጥቃቶች 248 ሰዎች መገደላቸውን 55 ሰዎች ላይ ጉዳት መድረሱን ጠቁሟል።
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መታወጁን ተከትሎ በከፍተኛ ሁኔታ የዘፈቀደ እስር መፈፀሙንም የመንግስታቱ ድርጅት ሪፖርት ገልጿል።
በሀገሪቱ በሚገኙ 16 የማጎሪያ ማዕከላት 5ሺ የሚጠጉትን መመዝገቡን ጠቁሟል።

No comments:

Post a Comment