ስብሰባውን በባህርዳር ከተማ ሲያካሂድ የሰነበተው የብአዴን ማእከላዊ ኮሚቴ የንቅናቄው የጽህፈት ቤት ሀላፊ የአማራውን ህዝብ የዘለፉበትን ንግግር ያስተባብላል ተብሎ ቢጠበቅም፣ ምንም ሳይል ቀርቷል። ንቅናቄው ” ህዝቡ በተቃዋሚዎችና ተባባሪዎቻቸው የሚነዙ አሉባልታዎችን ወደ ጎን በማለት ከብአዴን ጎን ጎን እንዲሰለፍ” የሚል መግለጫ በማውጣት ስብሰባውን አጠናቋል። በጉዳዩ ላይ አስተያየቱን የጠየቅነው አንድ የብአዴን አባል፣ አቶ አለምነው ቀድሞውንም የተናገረው የብአዴንን አቋም መሆኑን አውስቶ ንቅናቄው ከገባበት አጣብቂኝ ለመውጣት ለይምሰልም ቢሆን፣ የጸጸት ድምጹን በማሰማት ህዝቡን ለማረጋጋት ይደፍር ይሆናል የሚል እምነት ነበረኝ፣ አሁን እንደምናየው ግን ብአዴን እንደ ህወሃት ሁሉ ህዝብ ምን ያመጣል” በሚል ንቀት መጓዝን መርጧል ” ብሎአል። አቶ አለምነው መኮንን በአማራው ህዝብ ላይ የተናገሩትን አስጸያፊ ስድብ በመቃወም በባህርዳር በርካታ ህዝብ በተገኘበት የተቃውሞ ሰልፍ መካሄዱ ይታወሳል።
በሌላ በኩል ደግሞ በመተማ አካባቢ የሚኖሩ አንዳንድ ሰዎች ለግንቦት7 ህዝባዊ ሃይል ወጣቱን ታመላልሳላችሁ በሚል ተይዘው አሰቃቂ ድብደባ እንደተፈጸመባቸው ለኢሳት ገልጸዋል። እነዚሁ የአካባቢው ተወላጅ ያልሆኑ የደህንነት ሃይሎች፣ የሚጠረጥሩዋቸውን ሰዎች እየያዙ ” ለግንቦት7 ሰዎችን ወደ ኤርትራ የሚያመላልሱ ሰዎችን ታውቃላችሁ፣ አውጡ በማለት በማሰቃየት ላይ መሆናቸውን ኢሳት ያነጋገራቸው ሰዎች ገልጸዋል። አንድ የአካባቢው ነዋሪ፣ በደረሰበት ከፍተኛ ድበደባ ቆሞ ለመሄድ አለመቻሉንና የሰሜን ጎንደር የአንድነት ፓርቲ ተወካዮች ተባብረው መጠነኛ እርዳታ እንዳደረጉለት ተናግሯል።
No comments:
Post a Comment