መንስኤ
ከ2005 አጋማሽ በኋላ የአወሊያ ግቢን መሰረት ያደረገውንና በ2004 ታህሳስ ወር የተጀመረውን የህዝበ ሙስሊሙን ተቃውሞ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች መረከብ እንዳለባቸው የሚያስረዱ ጥሪዎች ከየአቅጣጫው ይሰሙ ጀመር፡፡ ይህ ጥሪ ልቦናው ውስጥ ከፍተኛ ፍርሃት የፈጠረበት የኢህአዴግ መንግስት የዩኒቨርስቲ ተማሪዎችን በራሳቸው ጉዳይ እንዲጨናነቁ በማድረግ በህዝበ ሙስሊሙ ትግል ተሳትፏቸውን እንዲቀንሱ ለማድረግ ማቀዱን ከአንድ ከፍተኛ ባለስልጣን የወጣ መረጃ አመለከተን፡፡ ይህን ውሳኔ ተከትሎ በጥር ወር መጀመሪያ 2005 በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ሊኖር የሚገባውን የአለባበስ፣ የአመጋገብና የአምልኮ ሥነ-ስርዓት አስመልክቶ ትምህርት ሚኒስቴር አውጥቶት የነበረውን ኢ-ህገ መንግስታዊ ‹‹ረቂቅ ደንብ›› የባህርዳር ዩኒቨርስቲ በቀጥታ ተግባራዊ አደረገ፡፡
ረቂቅ ደንቡ ምንም እንኳን የሁሉንም ሃይማኖት ተከታዮች የሚመለከት ቢመሰልም ቅሉ ግን ያነጣጠረው ድሮም በእናት አገሩ ኢትዮጵያ ፍዳውን እያየ የኖረው ሙስሊም ተማሪ ላይ ሲሆን በውስጡም ሒጃብን (የሴቶች ኢስላማዊ አለባበስን) እና ሶላትን የሚገድቡ ህገ-ወጥ ሴራዎች የተጎነጎኑበት ነበር፡፡ በሂደቱም 13 የባህር ዳር ዪኒቨርስቲ ኒቃብ (ዓይነ-ርግብ) የሚለብሱ ሴቶች በይፋ እንዲባረሩ ተደረገ፡፡ የባህር ዳር ዩኒቨርስቲ ፖሊ ግቢ ሙስሊም ጀምዓ ዋና አሚር ተባረረ፡፡ በወቅቱ የተፈጠረውን ውዝግብ ያባብሳሉ ተብለው የሚታሰቡ 12 ሙስሊም ተማሪዎች ማስፈራሪያ ተለጠፈባቸው፡፡ በግቢው የጀምዓ ሶላት የሚሰገድባቸው ንብረቶች ተዘረፉ፡፡ ኒቃባቸውን አውልቀው እንዲማሩ ወይም ዊዝድሮዋል ሞልተው ወደየቤታቸው እንዲሄዱ፣ ይህ የማይሆን ከሆነ እንደሚባረሩ አስከፊ ምርጫ የተሰጣቸው ሙተነቂብ (ኒቃብ የሚለብሱ) እህቶች ‹‹አናወልቅም እንማራለን!›› በማለታቸው በዩኒቨርስቲው ፖሊሶችና የተማሪዎች የመኝታ አገልግሎት ሰራተኞች ከነሻንጣቸው እንደ ባእድ ከግቢ ውጭ ተወረወሩ፡፡ ተሰብስበው ሲሰግዱ የተገኙ 28 ሴት ተማሪዎች ማስጠንቀቂያ ተሰጣቸው፡፡ ጭራሽ ‹‹100 ሜትር ተራርቃችሁ መስገድ አለባችሁ›› እስከመባልም ተደረሰ፡፡ ዶርም ውስጥ በግል የሚሰግዱ ተማሪዎች መታወቂያ ካርዳቸውን ተነጠቁ፡፡
ከኢትዮጵያ ህገ-መንግስት ሀይማኖታዊ ድንጋጌዎች አንጻር፣ ከዓለም አቀፍ ህግጋት አኳያ፣ ኢትዮጵያ ‹‹ፈለጋቸውን እከተላለሁ›› ከምትላቸው ሴኪውላር ሀገራት ተሞክሮ አንጻር የረቂቅ ደንቡን ህገ-ወጥነት ለማሳየትና ለማውገዝ ስብሰባዎች ላይ አቋሙን ያንጸባረቀው መላው የዩኒቨርስቲው ተማሪ (ክርስቲያኖችንም ይጨምራል) በባህር ዳር ዩኒቨርስቲ አስተዳደር ህገ-ወጥ አካሄድ ቁጣውን መግለጽ ጀመረ፡፡ ጾም፣ ፔቲሽን፣ የገንዘብና የሞራል ድጋፍ ወዘተ ሲደማመሩ በየዩኒቨርስቲው ውጥረት ነገሰ፡፡ ቁጥራቸው ከ700-1200 የሚደርሱ የባህር ዳር ዩኒቨርስቲ ሙስሊም ተማሪዎች ‹‹ሀይማኖታችን እስትንፋሳችን ነው! ካለ እሱም መማር አንችልም!›› በማለት ግቢውን ለቀው ወደየቤታቸው ተመለሱ፡፡ የዚህ ሁሉ የተማረ ሀይል ትምህርት መስተጓጎል ጥቂት እንኳን ያላሳሰበው ዩኒቨርስቲ (መንግስት) በአንጻሩ ተመልሰው ትምህርታቸውን የማይቀጥሉ ከሆነ ውጤታቸው ቢበላሽ ኃላፊነቱን የማይወስድ መሆኑን የሚገልጽ ዛቻ አዘል ማስታወቂያ በመለጠፉ ድሮም ዓላማቸው የተማረውን ሙስሊም ወጣት ከትምህርቱ ማደናቀፍ እንደሆነ አሳበቀ፡፡
እስር
ይህንን ተከትሎ ነው እንግዲህ የተማሪዎች እስር የተጀመረው፡፡ መንግስት ልክ በ2003 ስድስቱን የወሎ ዩኒቨርስቲ ጅልባብ ለባሽ ሴቶች እንዳፈነው ሁሉ ‹‹በየዩኒቨርስቲው ይህንን ተቃውሞ እያቀጣጠሉብኝ ነው›› ያላቸውን 17 ተማሪዎችንና 1 አስተማሪ ከየዩኒቨርስቲው በማደን በግፍ ማእከሉ የፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ዘርፍ (ማእከላዊ) በየተራ ማጎር ጀመረ፡፡ በምርመራ ሂደቱም ማንም ሙስሊም የግፍ እስረኛ ሊደርስበት የሚችለውን ሰቆቃ ሁሉ አሳልፈናል፤ በሌሊት ተመርምረናል፤ እርቃናችንን ቆመን እንድንሸማቀቅ ተደርገናል፤ ተገልብጠን ውስጥ እግራችንን ተገርፈናል፤ በጠያቂ ቤተሰቦቻችን ፊት ሳይቀር ቀፋፊና ክብረ-ነክ ስድቦችን ተሰድበናል፤ እጅግ በጣም ጨለማ፣ ጠባብና ቀዝቃዛ ክፍሎች ውስጥ ታስረናል፤ ግድያ ተዝቶብናል፤ የህዝበ ሙስሊሙ መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላት ላይም በሐሰት እንድንመሰክር ተጠይቀናል፤ ያለ ፍርድ ቤት ትእዛዝና እውቅና በጭምብል ታፍነን በደህንነት ማጎሪያዎች ውስጥ ለቀናት ቆይተናል፤ ሌላም ሌላም!
ፖሊስም ‹‹ሁሉንም የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታቸው በማፈናቀል የጎዳና ላይ ነውጥ ለማስነሳት ያለሙ ናቸው፤ ምናልባትም ከግብጽና ከሳዑዲ መንግስት ጋር ግንኙነት ሳይኖራቸው አይቀርም፤ ግብረ-አበሮቻቸው ከኢትዮጵያ የወጡ በመሆኑ እነሱን ለመያዝ መንግስት ከጎረቤት ሃገሮች ጋር እየተወያየ ነው፤ የቴክኒክ ማስረጃዎችን እያሰባሰብን ነው፤ የታሰሩትን ኮሚቴዎች ራእይና ዓላማ ለማስቀጠል ሲንቀሳቀሱና ተማሪውን ሲያሳምጹ የነበሩ ናቸው፤ ተማሪዎችን ለጂሀድ ሲያነሳሱ ነበር... ወዘተ›› የሚሉ በሬ ወለደ ውንጀላዎችን በማቅረብ በሽብርተኝነት ወንጀል ከሶ ለአራት ወራት ያክል ማእከላዊ፣ ሲፈልግም እስከ ምሽቱ 2 ሰአት በሚፈነጭበት የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት አራዳ ምድብ ችሎት አመላለሰን፡፡
ክስ
ከ4 ወራት ኢ-ሰብዓዊ የምርመራ ጊዜያት በኋላ 5ቱ (4 ወንድና 1 ሴት) ተለቀው 13ታችን ደግሞ (12 ወንድና 1 ሴት) የፌደራል አቃቤ ህግ በፌደራል ከፍ/ፍ/ቤት 4ኛ ወንጀል ችሎት ‹‹በ 196 ዓ.ም ተደንግጎ የወጣውን የኢ.ፌ.ዲ.ሪ የወንጀል ህግ አንቀጽ 32/1/ሀ፣ 38/1/ እና 257/ሀ/ ስር የተመለከተውን በመተላለፉ›› የሚል ክስ መሰረተብን፡፡ የክሱ ይዘትም በጥቅሉ ‹‹መንግስት (ትምህርት ሚኒስቴር) ለከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ያዘጋጀውን የሥነ-ምግባር ደንብ ከወዲሁ ተግባር ላይ እንዳይውል ዓላማውን ለማደናቀፍ፣ እንዲሁም የሙስሊም መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ በማለት ራሳቸውን በመሰየም ሲንቀሳቀሱ የነበሩና በአሁኑ ሰዓት በሽብርተኝት ወንጀል ክስ ቀርቦባቸው የክስ ሒደታቸው በፍ/ቤት በመታየት ላይ ያሉትን ግለሰቦች በመንግስት ላይ ተጽእኖ በማሳደር ለማስፈታት ሲንቀሳቀሱ የተያዙ ሲሆን...›› የሚል ነው። ቀጥሎም 4ኛ ወንጀል ችሎት ይህንን ጉዳይ የማየት ስልጣን የሌለው መሆኑንና ክሱ በአንድ ዳኛ ብቻ የሚታይ መሆኑን ገልፆ ክሱ 14ኛ ወንጀል ችሎት በዳኛ አብርሃም ተጠምቀ እንዲታይ ተደረገ። እኛም ከጠበቆቻችን ጋር በመሆን የተከሰስንበት አንቀፅ የዋስትና መብት የማያስከለክል በመሆኑ የዋስትና መብታችን ተጠብቆልን ጉዳያችንን እየተማርን እንድንከታተል ፍ/ቤቱን ጠይቀናል፡፡ ነገር ግን እጅግ በሚገርሙ ውሃ የማይቋጥሩ ምክንያቶች በእምቢታቸው ገፍተውበታል፡፡ ለምሳሌም፡-
•ሰኔ 17/2005 ‹‹አልደረሰም ምን የሚያስቸኩል ነገር አለ?›› በሚል፣
•ሰኔ 19/2005 ‹‹አልደረሰም ሌላ ሪፈር የምናደርገው ነገር አለ›› በሚል፣
•በሌላም ቀጠሮ ‹‹በሚቀጥለው ሳምንት ቁርጣችሁን እንነግራችኋለን፤ ህግ የሚፈቅድ ከሆነ እንፈቅዳለን፤ ህግ የሚከለክላችሁ ከሆነ እንከለክላችኋለን›› በሚል፣
•ሐምሌ 05/2005 ‹‹ከምሥክር ጋር አብረን እናየዋለን›› በሚል፣
•ሰኔ 19/2005 ‹‹አልደረሰም ሌላ ሪፈር የምናደርገው ነገር አለ›› በሚል፣
•በሌላም ቀጠሮ ‹‹በሚቀጥለው ሳምንት ቁርጣችሁን እንነግራችኋለን፤ ህግ የሚፈቅድ ከሆነ እንፈቅዳለን፤ ህግ የሚከለክላችሁ ከሆነ እንከለክላችኋለን›› በሚል፣
•ሐምሌ 05/2005 ‹‹ከምሥክር ጋር አብረን እናየዋለን›› በሚል፣
በእነዚህና በሌሎች መሰል ምክንያቶች ፍ/ቤቱ የዋስትና መብታችንን ለመወሠን 15 የሚደርሱ ቀጠሮዎችን ሰጥቶ ካመላለሰን በኋላ ከ2005 የዒድ ተቃውሞ በኋላ በነበረን ቀጠሮ አቃቤ ህግ ‹‹ተማሪዎቹ የተያዙበት ጉዳይ አሁንም በሌሎች መስጂዶችና ከተሞች የቀጠለ በመሆኑ የእነሱ መፈታት ተፅእኖ ሊኖረው ስለሚችል የዋስትና መብታቸው ይከልከል›› ብሎ ባመለከተው መሰረት ዳኛው አብርሀም ተጠምቀ ቀደም ሲል በተጠቀሱት ቀጠሮዎች በአንዱ ‹‹ህግ ከፈቀደ ይፈቅድላችኋል›› ያለውን በመፃረር አይኑን በጨው አጥቦ ‹‹አቃቤ-ህግ ያቀረበውን ምክንያት ተቀብለነዋል፤ የዋሥትና መብት ከልክለናል፤ ከፈለጋችሁ ይግባኝ ማለት ትችላላችሁ›› በማለት ታሪካዊ ስህተት ፈፅሟል። ከዚያ በመቀጠልም ፍ/ቤቱ ምስክር መስማት ቀጠለ።
ጠቅላይ ፍ/ቤት
እንግዲህ በዚህ ሂደት ውስጥ እያለን ነው የፌደራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ጥቅምት 1/2006 ‹‹የወንጀል ቅጣት አወሳሰን መመሪያ ማሻሻያ›› የሚል አዲስ መመሪያ የፀደቀው፡፡ በዚህ መመርያ የተከሰስንበት አንቀፅ 257 ምንም እንኳን መንግሥት እንዳሰኘው ለመለጠጥ በሚያስችለው መልኩ የተዘጋጀ ቢሆንም ተሻሽሏል። በአንቀፅ 257/ሀ የተከሰሰ ሰው ጥፋተኛ ሆኖ ቢገኝ ሊቀጣ የሚችለው ከ 10 ቀን እስከ 6 ወር እስራት በሚደርስ ቅጣት ወይም የጉልበት ስራ መሆኑንም ያትታል። እኛ ደግሞ አመት ከሁለት ወር በላይ እስር ላይ አሳልፈናል። ስለዚህ የተቀነባበረውን የሀሰት ውንጀላ ‹‹ፈፅማችኋል›› ተብሎ ጥፋተኛ እንኳን ብንባል ልንቀጣ የምንችለውን ቅጣት በ3 እጥፍ ጨርሰናል ማለት ነው።
ይህ በእንዲህ እያለ የዋስትና ይግባኝ ጥያቄያችን ፌ/ጠ/ፍ/ቤት መስከረም 15/2006 እንዲገባ የተደረገ ሲሆን ፍ/ቤት ለጥቅምት 25 እና 26 የይግባኝ ክርክር ለመስማት ቀጠሮ ሰጠ። (ለሁለት ተከፍለን ነበር የቀረብነው) በቀጠሮዎቹም ‹‹ቀድሞውኑ ዋሥትና በማያሥከለክል አንቀፅ ተከሰው ሳለ ያለ በቂ ምክንያት መከልከላቸው ትክክል አይደለም፤ ወንጀል ግለሰባዊ በመሆኑ ሊጠየቁ የሚገባው በራሳቸው ብቻና ብቻ መሆን ሲገባው ውጭ ላይ በታዩ እንቅስቃሴዎች ምክንያት ደንበኞቻችን ዋስትና መከልከላቸው ህጋዊ መሠረት የለውም፤ የተሰሙት ምስክሮችም ቢሆን ክስ ማመልከቻው ላይ የተጠቀሰውን ጭብጥ ያስረዱ አይደሉም፤ አሁን ደሞ ጠ/ፍ/ቤቱ በዚሁ አመት ባወጣው የቅጣት አወሳሰን መመሪያ መሠረት ጥፋተኛ እንኳን ሆነው ቢገኙ ሊቀጡ ከሚችሉት በላይ ታስረዋል፤ ከምንም በላይ ደግሞ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች በመሆናቸው ጉዳያቸውን በውጭ ሆነው እየተማሩ እንዲከታተሉ የዋስትና መብታቸው መረጋገጡ አስፈላጊ ነው...›› ሲሉ ጠበቆቻችን ለፍ/ቤቱ አስረድተዋል። ፍ/ቤቱም ለአርብ ጥቅምት 29/2006 ለውሳኔ ቀጠረ።
በቀጠሮው ቀን ጠዋት በጠ/ፍ/ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት የተሰራው ድራማ ግን እጅግ የሚደንቅ ነበር። ዳኛው ‹‹ዛሬ ጠርተናችኋል እንዴ?›› በማለት ነበር ውሳኔውን በግልፅ ለመናገር መወዛገቡን ያሳበቀው። በዚያው አጋጣሚ ከመዝገብ ቤት የተገኘው መረጃ ግን ‹‹የስር ፍ/ቤቱን ውሳኔ አፅንተናል›› የሚል ነበር። በመሆኑም እኛ ‹‹ውሳኔያችሁን ደርሰንበታል፤ ለምን በግልፅ አይነገርም›› ስንል ዳኛውን ብንጠይቅም ‹‹አይ... ገና ነው... በቃ ዛሬ ከሰአት አይተነው ሰኞ እና ማክሰኞ በፅ/ቤት በኩል ውሳኔያችን ይደርሣችኋል›› በማለት እጅግ ተሸማቆ ምላሽ ሊሰጠን ችሏል። ራሱ ጠቅላይ ፍ/ቤት ያወጣውን እና በዚሁ አመት በዚሁ ወር ያፀደቀውን መመሪያ ተቃርኖ ውሣኔ በመስጠት መመርያው ድሮም ለኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ባዳ መሆኑን እና ለጭቁኖቹ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ቦታ የሌለው የሌለው መሆኑን አሳይቷል። በጣም የሚገርመው ነገር ደግሞ በዚያው ቀን ከሰአት ውሳኔው ከመዝገብ ቤት እንዲሰወር የተደረገ መሆኑ እና ለእኛ የደረሰን ከ27 ቀን በኋላ መሆኑ ነበር!
ምስክር
የፌዴራሉ ከ/ፍ/ቤት 14ኛ ወንጀል ችሎት ሐምሌ 18/2005፣ ሐምሌ 19/2005 እና ህዳር 2006 በዋለው ችሎት በክስ ማመልከቻው ላይ ከተመለከቱት 28 ምስክሮች የ17ቱን በክፍት እና የ2ቱን በዝግ ችሎት በድምሩ 19 የሐሰት ምስክሮችን ሰምቷል። ከእነዚህ ‹‹የሰለጠኑ›› ምስክሮች አንዳንዱ በብጣሽ ወረቀት የያዘውን የሚያነብ የነበረ ሲሆን ሌላው ደግሞ የሰለጠነው (የሸመደደው) ጠፍቶት ያልተከሰሰ ሰው ስም ሲጠራ ተደምጧል። ሌላው ደግሞ ‹‹ይህም ተማሪ በአካል አላውቀውም›› እያለ ፍ/ቤቱ ‹‹በማታውቀው ሰው ላይ መመስከር አትችልም›› ማለት ሲገባው ምስክሩን የተቀበለው ሲሆን ሌላው ደሞ አውቀዋለሁ ያለውን ሰው እንኳን ከእኛ መሀል ለይቶ ማሳየት አልቻለም። አላህን ፈርቶ ‹‹እኔ እገሌን የማውቀው ተቃውሞችንን በሰላማዊ መንገድ ለመንግስት ማሳወቅ አለብን ሲል ነው›› ብሎ የመሰከረው ደግሞ በሐሰት ስላልመሰከረ ‹‹አንተ ስነ-ስርአት አድርገህ መስክር! በህግ ትጠየቃለህ!›› የሚል ማስፈራሪያ ከአቃቤ ህግ ሲደርስበት ተስተውሏል። ‹‹ለመሆኑ በህግ የሚያስጠይቀው መዋሸት ነው ወይስ ......?›› ያስብላል!
ዳኛ አብርሀም ተጠምቀ
ይህ ዳኛ ከአሁኑ የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዬች ሚኒስቴር ዲኤታ አቶ ሽመልስ ከማል ጋር በመሆን በምርጫ 97 የቅንጅት ለአንድነት እና ለዲሞክራሲ አመራሮች በነበሩትና በኋላም በተፈጠረው ግርግር ‹‹በአመፅና በሐገር ክህደት›› ወንጀል በተከሰሱት ግለሰቦች ክስ ላይ አቃቤ ህግ የነበረ ሲሆን አሁን ደግሞ የእኛ ክስ ላይ ዳኛ ነው። ዳኛው አንዳንዴ በአምላክ ስም ምሎ ተገዝቶ በሌሎች ፋይሎች የተጨናነቀ ለማስመሰል ሲሞክር፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ ‹‹ማረሚያ ቤት መሆናችሁ ሳይሰማኝ አልቀረም›› በማለት ያዘነ መሆኑን ለማሳየት ይሞክራል። አንዳንዴ ‹‹ሪፈር የምናደርገው ነገር አለ›› በማለት ቀጠሮ እየሰጠ የአለቆቹን ትእዛዝ እንደሚጠባበቅ የሚያሳብቅ ሲሆን ሌላ ጊዜ ደግሞ ‹‹ምን የሚያስቸኩል ነገር አለ?›› በማለት የሁለት አመት የዩኒቨርስቲ ትምህርታችን እንደዋዛ ከሜዳ መቅረቱን ከመጤፍ እንደማይቆጥረው ያሳያል። እጅግ የሚገርመው ደግሞ (የካቲት 05/2006 በቢሮው) ‹‹ዋስትና የከለከላችሁ ወቅቱ ነው›› በማለት እኛን የሚፈታን ጊዜ እንጂ ህግ እንዳልሆነ በግልፅ ማሳየቱ ነበር። ከላይ የተጠቀሱትን ትርኪ ምርኪ ምስክሮች የምስክር ቃል እና ሌሎች ማስረጃዎች ላይ ብይን ለመስጠት የ1 ወር ከ10 ቀን ቀጠሮ ሰጥቶ ነበር።
ይህም 3 ወር ተጠናቆ መጋቢት 15/2006 ስንቀርብ ‹‹ዳኛው ታሟል›› የሚል የሐሰት ምክንያት በመስጠት ሌላ የ1 ወር ቀነ-ቀጠሮ ለሚያዚያ 15/2006 ከሰአት ተቀጥረናል። የሚገርመው ነገር ዳኛው ጠዋት ችሎት ላይ የነበረ ሲሆን ከ2 ቀን በፊት ደግሞ አሶሳ ላይ ችሎት ነበረው።
የሽብር መነጽር
ቀደም ሲል እንደተገለፀው የተከሰስንበት አንቀፅ 257/ሀ ነው። ሆኖም ግን ክስ በተመሰረተብን ማግስት ፍርድ ቤቱ ወደ እስር ቤት የምንሄድበት ማዘዣ ላይ የወንጀል አይነቱን ‹‹ሽብር›› አድርጎ ልኮናል። እናም እስር ቤት ውስጥ ያለን መታወቂያ የወንጀል አይነቱ ‹‹ሽብር›› በመሆኑ ከፍተኛ ማህበራዊ መገለል እየተደረገብን ይገኛል። ሁለተኛ ተከሳሽ የሆነችውን የእህታችንን ፈትህያ ሙሀመድን (አላህ ይጠብቃት) ተጨባጭ እንኳ ብናይ የሚጠይቋትን ቤተሰቦች ዝርዝር በፅሁፍ እንድታቀርብ ተጠይቃለች፤ እሷ የቀጠሮ እስረኛ ሆና ሳለ ለረዥም ጊዜ ከፍርደኞች ጋር እንድትኖር የተደረገ ከመሆኑም በላይ እሷን ሲያናግር የተገኘ የአመክሮ መብቱ እንደሚነጠቅ ማስፈራሪያ እየተነገረ እንደ ጭራቅ እንድትታይ ተደርጓል። በቀን ውስጥ ከ6 ሰአት በኋላ ለ10 ደቂቃዎች ብቻ፣ ለዚያውም የተወሰኑ ሰዎች ብቻ የሚጐበኟት ሲሆን የግል ሚስጥሮቿን እንኳ በ3 አጃቢ ፖሊሶች ፊት እንድታወራ ትገደዳለች። ‹‹ለሴቶች ልዩ መብት እንሰጣለን፤ ለሴቶች ቆመናል›› በሚል ስርዓት ሥር ይህን መሰል መገለሎችን ስንመለከት ‹‹ህጉ ለሙስሊሞች የእንጀራ እናት ነው እንዴ?›› እያልን እንድንጠይቅ ያስገድደናል፡፡
የፍትህ ያለህ!
ይሄን ያህል ጊዜ ‹‹በህግ ጥላ ስር›› ስንቆይ ችሎት ላይ ከቀረብንበት ይልቅ ቀጠሮ ለመቀበል ቢሮ የገባንባቸው ጊዜያት የትየለሌ ናቸው፡፡ ዘመኑ የተገላቢጦሽ ሆኖ ዓቃቤ ህጎች ዳኞችን ሲያሽመደምዱ እየታየ ሲሆን ከፍ ሲል ደግሞ ችሎት ከመገባቱ በፊት ዳኛና ዓቃቤ ህግ ሲወያዩ መመልከት የተለመደ ሆኗል፡፡ የመንግስትን ማስረጃዎች ለመበየን ብቻ እንቆቅልሽ በበዛባቸው ቀጠሮዎች ሆነ ተብሎ ታስረን እንድንቆይ እየተደረገ 4 ወራት እያለፉ ነው፡፡ የሁለት ዓመት ትምህርታችን የተስተጓጎለ ሲሆን የሶስተኛ ዓመቱም አፋፍ ላይ ይገኛል፡፡ ለያውም ደግሞ የባህር ዳር ዩኒቨርስቲ እና ትምህርት ሚኒስቴር በውይይት ላይ ያንጠለጠለውን ረቂቅ ከሜዳ ተነስቶ ተግባራዊ በማድረጉ የተፈጠረ ችግርና ጥፋተኛው ማን እንደሆነ ገና ባልተለየበት ተጨባጭ እየተጉላን እንገኛለን፡፡ ለመሆኑ የእኛን ትምህርት መንግስት ከ15 ዓመት በላይ አልደከመበትምን?! ከምንም በላይ ደግሞ እኛ ራሳችን እና ቤተሰቦቻችን፣ እንዲሁም ሌሎች የሚያውቁን ሁሉ ውጤታማነቱን በጉጉት እንጠብቀው የነበረው ትምህርታችን እንዲህ በሆነ ባልሆነው ሲቀለድበት ማንም የፍትህ አካል ጉዳዩን ሲያስተካክለው አልመታየቱ በጣም አሳዛኝ እውነታ ነው፡፡ ከሀገር የተሰደዱትንስ ማን አለሁላችሁ ይበላቸው?
ጭቆናው አሁንም ቀጥሏል!
የዩኒቨርስቲ ሙስሊም ተማሪዎች ፈተና 2003 ማእከላዊ በሌሊት ታፍነው በተወሰዱት ስድስቱ ሙስሊም ሴት ተማሪዎች እንዳልቆመው ሁሉ ዛሬም ወጥቶ ቢሰራ ሀገር መለወጥና ማልማት የሚችል በርካታ ሙስሊም ተማሪ ትምህርቱን አቋርጦ አሁንም ቀጥሏል፡፡ እኛ ከታሰርን በኋላ እንኳን 48 ኒቃብ የሚለብሱ እህቶች ከዲላ ዩኒቨርስቲ ትምህርታቸውን አቋርጠዋል። የአርባ ምንጭ የኒቨርስቲ ሙስሊም ተማሪዎች መስጂድ ፈርሷል፡፡ የጅማ ዩኒቨርስቲ እህቶችም ችግር ውስጥ ናቸው፡፡ በነጠላ እንኳን የሚሰግዱ ተማሪዎች መታወቂያቸው እየተነጠቀ ይገኛል፡፡ መንግስት ‹‹ኢትዮጵያ ባለሁለት አሃዝ እድገት እያስመዘገበች ነው፡፡ ለመልካም አስተዳደርና ፍትህ ከፍተኛ እመርታ እያሳየች ነው፡፡ ለሌሎችም የአፍሪካ ሀገራት አርአያ መሆን በምትችልበት ደረጃ ላይ ነች›› የሚል አታሞ በሚደልቅበት በዚህ ወቅት ይህን ያህል ያገጠጠ በደልና ሰቆቃ ማየት ያማል፡፡ ስለዚህ ለፍትህ ቆመናል የምትሉ ሁሉ ለሃገር፣ ለሰላም፣ ለእድገት ስትሉ ጆሯችሁን እንድትሰጡንና ‹‹የፍትህ ያለህ!›› ጥሪያችንን እንድታስተጋቡልን እንጠይቃለን፡፡
የተከሳሾች ዝርዝር
1. እስማኤል ኑሩ ሁሴን - - - - - - - ጅጅጋ ዩኒቨርስቲ
2. ፈትህያ ሙሀመድ እንድሪስ - - - - ቤቴል ሜዲካል ኮሌጅ
3. ኑርዬ ቃሲም አሊ - - - - - - - - - ባህርዳር ዩኒቨርስቲ
4. ያሲን ፈየም ዋበላ - - - - - - - - - ጅማ ዩኒቨርስቲ
5. ሙሀመድ አሚን ከድር - - - - - - -ጅማ ዩኒቨርስቲ
6. ሙሀመድ ሰይድ ሙህዲን - - - - - ወሎ ዩኒቨርስቲ
7. የሱፍ ከድር አብዲ - - - - - - - - - ወሎ ዩኒቨርስቲ
8. ጣሂር ሙሀመድ ጣሂር - - - - - - -ወሎ ዩኒቨርስቲ
9. ሙሀመድ ሰኢድ ተሰማ - - - - - - ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርስቲ
10. ሰይድ ኢብራሂም ሲራጅ - - - - - ጎንደር ዩኒቨርስቲ
11. አብደላ ሙሀመድ ሙሳ - - - - - - ሐዋሳ ዩኒቨርስቲ
12. አብዱ ሙሀመድ አብራር - - - - - ጅማ ዩኒቨርስቲ
13. ኢብራሂም የሱፍ ኢብራሂም - - - -ደብረብርሃን ዩኒቨርስቲ
1. እስማኤል ኑሩ ሁሴን - - - - - - - ጅጅጋ ዩኒቨርስቲ
2. ፈትህያ ሙሀመድ እንድሪስ - - - - ቤቴል ሜዲካል ኮሌጅ
3. ኑርዬ ቃሲም አሊ - - - - - - - - - ባህርዳር ዩኒቨርስቲ
4. ያሲን ፈየም ዋበላ - - - - - - - - - ጅማ ዩኒቨርስቲ
5. ሙሀመድ አሚን ከድር - - - - - - -ጅማ ዩኒቨርስቲ
6. ሙሀመድ ሰይድ ሙህዲን - - - - - ወሎ ዩኒቨርስቲ
7. የሱፍ ከድር አብዲ - - - - - - - - - ወሎ ዩኒቨርስቲ
8. ጣሂር ሙሀመድ ጣሂር - - - - - - -ወሎ ዩኒቨርስቲ
9. ሙሀመድ ሰኢድ ተሰማ - - - - - - ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርስቲ
10. ሰይድ ኢብራሂም ሲራጅ - - - - - ጎንደር ዩኒቨርስቲ
11. አብደላ ሙሀመድ ሙሳ - - - - - - ሐዋሳ ዩኒቨርስቲ
12. አብዱ ሙሀመድ አብራር - - - - - ጅማ ዩኒቨርስቲ
13. ኢብራሂም የሱፍ ኢብራሂም - - - -ደብረብርሃን ዩኒቨርስቲ
ድምፃችን ይሠማ ===================================
No comments:
Post a Comment