Search This Blog

Thursday, November 24, 2016

በእነ ጉርሜሳ አያኖ የክስ መዝገብ 3ኛ ተከሳሽ በሆነው አዲሱ ቡላላ ላይ የዓ/ህግ ምስክር ተሰማ

የኦፌኮ ም/ፕሬዚደንት አቶ በቀለ ገርባን ጨምሮ በእነ ጉርሜሳ አያኖ የክስ መዝገብ የሽብር ክስ የቀረበባቸው 22 ሰዎች ላይ የፌደራል አቃቤ ህግ ያቀረባቸው ምስክሮች ቀርበው እየተሰሙ ሲሆን፤ ህዳር 14/2009 ዓ.ም ከሰዓት በኋላ አንድ የዐቃቤ ህግ የደረጃ ምስክር በ3ኛ ተከሳሽ አቶ አዲሱ ቡላላ ላይ ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል፡፡
መዝገቡን እያየ ያለው የፌደራሉ ከፍተኛ ፍ/ቤት 4ኛ ወንጀል ችሎት ጠዋት ላይ ተሰይሞ የነበረ ቢሆንም የ2ኛ ተከሳሽ ጠበቃዎች በወቅቱ ባለመኖራቸው የምስክር ማሰማቱ ሂደት ለከሰአት ተዘዋውሯል።
የቂሊንጦ ማረሚያ ቤት አስተዳደር እያደረሰባቸው ያለውን ሰብአዊ መብት ጥሰት በተመለከተ ተከሳሾች በጠበቃቸው አማካኝነት አቤቱታቸውን በፅሁፍ ለፍርድ ቤቱ አስገብተው እንደነበረ የሚታወስ ነው፤ የማረሚያ ቤቱ አስተዳደር በበኩሉ አቤቱታው ከእውነት የራቀ እንደሆነ፤ እንዲያውም የተከሳሾች ጠበቃ የማረሚያ ቤቱን ስም የማጥፋት ስራ እየሰሩ መሆኑን በመጥቀስ ምላሽ በፅሁፍ አስገብተዋል።
በጠዋቱ ችሎት ተከሳሾቹ ያቀረቡት አቤቱታ የሚመለከታቸው የቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ሃላፊ የሆኑት ሱፐር ኢንቴንደንት ጣእመ በችሎት ውስጥ በመገኘታቸው ዳኞቹ በአካል ቀርበው እንዲያስረዱ ተደርገው፤ ሃላፊው አቤቱታ አቅራቢዎቹ የሚሉት ነገር ከእውነት የራቀ እንደሆነ እና ስለ ጉዳዩ እንደማያውቁ ተናግረው ከሌሎች የስራ ባልደረቦቻቸው ጋር በመነጋገር ችግር ካለ እንደሚፈቱ ተናግረዋል።
FREE ALL POLITICAL PRISONERS !!!
በተለይም 6ኛ፣ 7ኛ፣ 14ኛ እና 17ኛ ተከሳሾች (ገላና ነገራ፣ ጭምሳ አብዲሳ፣ ደረጄ መርጋ እና ገመቹ ሻንቆ) ለቂሊንጦ ማረሚያ ቤት መቃጠል እጃችሁ አለበት ተብለው ቀንና ለሊት እጃቸውን እና እግራቸውን በካቴና ታስረው እንደሚያድሩ፣ ከቤተሰብ እንደማይገናኙ፣ከውሃ እና ሳሙና አንፃር ከቤተሰብ እንዳይቀበሉ መደረጋቸው በፅሁፍ ካቀረቡት አቤቱታ በተጨማሪ በችሎት ውስጥም በምሬት ተናግረዋል።
አራቱ ተከሳሾች ጉዳዩ ይመለከተኛል ብለው ለችሎት ምላሽ የሰጡትን ሃላፊውን ጭራሽ አይተዋቸው እንደማያቁ እና የተናገሩትም ትክክል እንዳልሆነ ተናግረዋል። 14ኛ ተከሳሽ የሆነው አቶ ደረጄ መርጋ ካቴናው እጁ ላይ ከመክረሙ የተነሳ አልከፈት ብሏቸው ከእጁ ካቴናው ሳይወልቅ ችሎት እንዳስገቡት እጁን ከነካቴናው ከፍ አድርጎ ለችሎት አሳይቷል። በሰአቱ ዳኞች በአስቸኳይ እንዲፈታለት ለማረሚያ ቤት ፓሊሶች ቢያዙም፤ ፓሊሶቹ ካልተቆረጠ በቀር መክፈት እንደማይቻል አስረድተው ከነካቴናው ችሎቱን ጨርሷል። እንዲሁም 7ኛ ተከሳሽ ጭምሳ አብዲሳ ካቴናው እጁን ከማጥበቁ የተነሳ እጁ መቁሰሉን ለችሎት አሳይቷል። በካቴና ለ24 ሰአት ከመታሰር በተጫማሪ ያሉበት ክፍል 24 ሰአት ተዘግቶ አንደሚቀመጡ፣ በአንድ ጠባብ ክፍል ውስጥ 84 እረኞች ተጨናንቀው እየኖሩ እንደሚገኙ ተናግረዋል። 14ኛ ተከሳሽ አቶ ደረጄ “በቃጠሎ አላችሁበት ተብለን ሸዋሮቢት ተወስደን ስለ ደረሰብንን ድብደባ እና እንግልት እየተናገርን አይደለም፤ እሱን ታሪክ የሚጠይቃችሁ ይሆናል። በአሁኑ ሰአት ማረሚያ ቤቱ አስተዳደር የሚያደርስብን በደል ግን እንዲቀርልን፤ እንደ ሰው እንድንቆጠር ነው የምንጠይቀው።” በማለት ጥያቄውን አሰምቷል። ዳኞች ደረሰብን የሚሉትን የመብት ጥሰት ለማረሚያ ቤቱ የበላይ አካል የአመልክተው ያውቁያ እንደሆነ አራቱን ተከሳሾቹን ጠይቀው፤ ተከሳሾቹ 24 ሰአት የክፍላቸው በር ተዘግቶ እና በካቴና ታስረው ስለሚቀመጡ ለበላይ አካል ማመልከት የሚባለው ነገር የሚታሰብ አለመሆኑን አስረድተዋል። ዳኞቹ ረዘም ያለ ጊዜ ወስደው ሃላፊውን ሱፐር ኢንቴንዳንት ጣእመን፤ ተመሳሳይ አቤቱታዎችም በሌሎች መዝገቦች እየቀረቡ መሆናቸውን ጠቅሰው የተጠርጣሪዎቹን መብት መጣስ ማንንም እንደማይጠቅም እና እንዲህ አይነቱ ተግባር የሃገሪቱ የፍትህ ስርአት ላይ አሉታዊ ተፅእኖ እንደሚያመጣ ዘርዘር አድርገው አስረድተዋቸዋል፤ ተጠርጣሪዎቹ የተከሰሱበት ወንጀል በፍርድ ቤት የተያዘ ጉዳይ ስለሆነ ሌላ ቅጣት እና የመብት ጥሰት ተገቢም እንዳይደለ መክረዋል። በመጨረሻም ዳኞቹ ተከሳሾቹ በምስክር የመስማት ሂደት ተከሳሾቹን በየሚቀጣይ ቀናትም በተከታታይ የሚያገኟቸው በመሆኑ በቀረበው አቤቱታ ላይ የሚታዩ ለውጦች ካሉ እናያለን በማለት ሃላፊውን በነገው እለትም እንዲቀርቡ በማዘዝ የጠዋቱን ችሎት ዘግተዋል።
በከሰአቱ ችሎት አቃቢ ህግ ዳኞች ከተሰየሙ በኋላ ዘግይቶ በመድረሱ ዳኞች ሌላ ጊዜ እንዳያረፍድ አስጠንቅቀውታል። አቃቤ ህግ በበኩሉም ምስክሮችን ጥበቃ እንደቆየ አስረድቷል። አቃቤ ህግ በእነ ጉርሜሳ አያኖ መዝገብ 3ኛ ተከሳሽ በሆነው አቶ አዲሱ ቡላላ ላይ ሁለት የደረጃ ምስክሮች እንደቀረቡ አስረድቷል። ምስክሮቹ አቶ ታደሰ ታፈሰ እና አቶ አሸናፊ ደጀኔ እንደሚባሉ እንዲሁም ምስክሮቹ የሚመሰክሩበትን ጭብጥም አሲዟል። ጭብጡ— ጥር 17/2008 ዓም ቀን ከጠዋቱ 3:30 ላይ አዲሱ ቡላላ በፌደራል ወንጀል መመርመሪያ ማእከል ከፌስቡክ አካውንቱ ፕሪንት የተደረጉ መረጃዎችን የተከሳሽ ስለመሆናቸው የታዘቡትን በወቅቱ የታዘቡትን እንዲመሰክሩ ነው። አቃቤ ህግ የመጀመሪያውን ምስክር አቶ ታደሰ ታፈሰ የምስክር ቃላቸውን እንዲሰጡ ካስጠሯቸው በኋላ ምስክሩ ቃለ መሃላ ፈፅመው የአቃቤ ህግን ዋና ጥያቄ በመመለስ ቃላቸውን መስጠት ጀምረዋል። ምስክሩ ተነስተው ተከሳሹን አዲሱ ቡላላን በአካል እንዲያሳዩ በአቃቤ ህግበ ተጠይቀው 22ቱ ተከሳሾች የተቀመጡበት ቦታ ሄደው ሁሉንም ካዩ በኋላ አዲሱ ቡላላ ነው በማለት 8ኛ ተከሳሽ የሆነውን አቶ ጌቱ ግርማን አሳይተዋል። መሳሳታቸው በዳኞች ከተነገራቸው በኋላ ምስክሩ የተሳሳቱት ተከሳሹን ካዩት ረዘም ያለ ጊዜ ስለሆነ ነው ብለው ለማስረዳት ሞክረዋል። ጥር 17/2008 ዓም ከጠዋቱ 3:30 አካባቢ የፌደራል ወንጀል መመርመሪያ ማእከል ለስራ ከሌላ ባልደረባቸው ጋር (ባልደረባቸው በአዲሱ ቡላላ ላይ ሌላኛው ምስክር ናቸው) በሄዱበት ወቅት ቢሮ ቁጥር 31 ውስጥ አዲሱ ቡላላ ቢሮ ውስጥ የነበረውን ገመዶቹ ተነቃቅሎ የነበረ ኮምፒውተር እንደሰካካ እና እንዳበራ እንዲሁም የፌስ ቡክ አካውንቱን ስም እና የይለፍ ቃል በፈቃደኝነት አስገብቶ ከጃዋር መሃመድ ጋር መልእክት የተለዋወጠባቸውን ፅሁፎች 54 ገፅ ፕሪንት መደረጉን፤ ፕሪንት ከተደረጉ በኋላም አዲሱ ከፈረመባቸው በኃላ እሱ እና ሌላኛው ምስክር (የስራ ባልደረባቸው) መፈረማቸውን ተናግሯል። ስለ ፅሁፉ ይዘት ተጠይቀው በአብዛኛው በላቲን የተፃፈ በመሆኑ እንዳልተረዱት ነገር ግን በእንጊሊዘኛ ከተለዋወጧቸው መልእክቶች አዲሱ 38 የሚሆኑ እስረኞች በማረሚያ ቤት እንዳሉ ለጃዋር ሲነግረው ጃዋርም ለእስረኞቹ የሚሆን ብር እንደሚልክ የሚገልፁትን መልእክቶች እንደሚያስታውሱ ተናግረዋል። ፈረምኩባቸው ያሏቸውን ሰነዶችም ከሌሎች የማስረጃ ሰነዶች ውስጥ ለይተው አሳይተዋል። ምስክሩ ቃላቸውን በሚሰጡበት ወቅት “ያለበት ሁኔታ ነው ያለው” እና “እንትን” የሚሉ ቃላቶችን በተደጋጋሚ በሚጠቀሙበት ወቅት ዳኞች ምንም እንኳን የተለመዱ አባባሎች ቢሆኑም ገላጭ ባለመሆናቸው እንዳይጠቀሟቸው ቢያሳስቧቸውም፤ ምስክሩ በተለይም “ያለበት ሁኔታ ነው ያለው” የሚለውን ሃረግ የምስክርነት ቃላቸውን ሰጥተው እስኪጨርሱ ድረስ ይጠቀሙት ነበር። ምስክሩ በአቃቤ ህግ ስራቸው ምን እንደሆነ ሲጠየቁ የመንግስት ስራ እንደሚሰሩ ብቻ በመናገር ቢያልፉም የተከሳሹ ጠበቃ አቶ አመሃ የት እንደሚሰሩ እና የስራ ድርሻቸውን በጠየቋቸው ወቅት ልደታ ክፍለ ከተማ ወረዳ 6 አስተዳደር ውስጥ የስራ አስኪያጁ አማካሪ በመሆን እንደሚሰሩ ተናግረዋል። በተመሳሳይ መልኩ ከአቃቤ ህግ ለምን ጉዳይ ማእከላዊ እንደተገኙ ሲጠየቁ ለስራ ጉዳይ ብለው በደፈናው ከመለሱ በኋላ በጠበቃ አመሃ ለምን የስራ ጉዳይ እንደሆነ እንዲያብራሩ ሲጠየቁ ከፀጥታ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ችግር ፈጣሪዎች ስለነበሩ የነሱን ጉዳይ ለመጠቆም እንደሆነ ተናግረዋል።
የአዲሱ ቡላላ የፌስ ቡክ በስሙ እንዳይደለ፣ ፌስቡክህን ክፈት ተብሎ መርማሪ ሲጠይቀው ዴካ አንበሳ የሚል ስም ያለው አካውንት እንደከፈተ እና ከጃዋር መሃመድ ጋር የተለዋወጡት መልእክትም በዚሁ አካውንት እንደሆነ ነገር ግን አዲሱ ራሱ የራሴ የምጠቀምበት አካውንት ነው ሲል እንደሰማው አስረድተዋል። ጠበቃ አመሃ ዴካ አንበሳ የሚለውን ስም እንዴት ሊያስታውስ እንደቻለ ሲጠይቁት በማስታወሻ ደብተር ይዞት እንደነበረ እና ለምስክርነት ሲጠራ ማስታወሻውን አይቶ እንደመጣ ያስረዳ ሲሆን ጃዋር መሃመድን ግን በዝና ስለሚያውቀው ስሙን ለማስታወስ እንዳልተቸገረ ተናግሯል። በዝና ስትል ምን ማለትህ ነው ተብሎ ከዳኞች ለቀረበለት የማጣሪያ ጥያቄ ፤ ጃዋር ከሽብር ጋር በተያያዘ በሚዲያዎች በተደጋጋሚ ስለሚቀርብ ነው የሚል ምላሽ ሰጥቷል። በወቅቱ የጃዋር መሃመድ ፕሮፋይል ፒክቸር ከማስተር ፕላኑ ጋር ተያይዞ ሴይ ኖ የሚል የተቃውሞ የመፈክር የሚነበብበት ምስል እንደሆን፤ የአዲሱ ቡላላ ዴካ አንበሳ የሚለው አካውንት ደግሞ የሴት ምስል እንደነበረው እንደሚያስታውሱ ተናግረዋል።
በተጨማሪም ምስክሩ ተከሳሽን ከተጠቀሰው ቀን በፊትም በኋላም እንደማያቋቸው፣ ቢሮ ቁጥር 31 እሳቸው እና የስራ ባልደረባቸው ሲገቡ ተከሳሹ አዲሱ ቡላላ እና መርማሪው ብቻ እንደነበሩ፣ ቢሮ ውስጥ ከሁለት በላይ ኮምፒውተሮች፣ ጠረጴዛዎች እና አንድ ፕሪንተር እንደነበረ እንደሚያስታውስ ተናግሯል።

የመጀመሪያው ምስክር የቀረበላቸውን ጥያቄዎች መልሰው ከጨረሱ በኋላ፤ አቃቤ ህግ ቀጣዩ ምስክር የነበሩት አቶ አሸናፊ ደጀኔ ከመጀመሪያው ምስክር ጋር ተመሳሳይ ጭብጥ የሚስረዱ በመሆናቸው አያስፈልጉኝም በማለቱ ምስክሩ ቃላቸውን ሳይሰጡ ቀርተዋል።
አቃቢ ህግ ቀሪ ምስክሮችን በቀጣዩ ቀን እንዲያቀርብ፤ በተጨማሪም በአንድ ቀን ከሁለት ምስክር በላይ ማዳመጥ ስለሚቻል ከሁለት በላይ ምስክሮችን እንዲያቀርብ ዳኞች አሳስበዋል። ሆኖም አቃቤ ህግ ለቀሩት ምስክሮች ጥሪ እያስተላለፈ ቢሆንም እንደፈለገው በሚደረግላቸው ጥሪ መሰረት እየቀረቡ አለመሆናቸውን፤ በነገው እለት የሚቀርቡ ምስክሮችም በየትኛው ተከሳሽ ላይ የሚቀርቡ ምስክሮች መሆናቸውን አለማወቁን አስረድቷል።
የተከሳሽ ጠበቃ የሆኑት አቶ አመሃ ተከሳሾቹ ጠዋት ከማረሚያ ቤት መጥተው እዛው እየዋሉ ቢሆንም ከቤተሰብ የሚቀርብላቸውን ምሳ እንዳይቀበሉ መከልከላቸውን ለዳኞች ተናግረዋል። የማረሚያ ቤቱ ፓሊሶች ደረቅ ዳቦ እና ውሃ ብቻ በምሳ ሰአት እንዳቀረቡላቸው የገለፁት አቶ አመሃ፤ በጠዋት ሲመጡ ቁርስ ሳይበሉ የሚመጡ እና የጤና ችግር ያለባቸው ተከሳሾች ከመኖራቸው አንፃር ለምሳ አንድ ደረቅ ዳቦ ብቻ መፈቀዱ ተገቢ እንዳልሆነ አስረድተዋል። ከማረሚያ ቤቱ ፓሊሶች የተሰጠው ምላሽም ከቤተሰብ የሚቀርብ ምሳ እንዲ በችሎቱ በመፈቀድ አለበት የሚል ሲሆን፤ ዳኞች በበኩላቸው ከዚህ በፊት በዋለ ችሎት ምሳቸውን ከቤተሰብ ተቀብለው እንዲበሉ በወሰኑን አስታውሰው ያ ውሳኔ ተከሳሾቹ ፍርድ ቤት በሚውሉበት ቀን ሁሉ ተግባራዊ መሆን እንደነበረበት ተናግረዋል። ከዚህ በኋላም በየጊዜው ችሎቱ ምግብ ይብሉ እያለ መወሰን ሳይኖርበት ተከሳሾቹ በፍርድ ቤት በሚውሉበት ቀን ሁሉ ምሳ ከቤተሰብ ተቀብለው በችሎት እንዲበሉ ብለው ለማረሚያ ቤቱ ፓሊሶች እና ሃላፊዎች ትእዛዝ አስተላልፈዋል።
ቀሪ የአቃቢ ህግ ምስክሮችን ለመስማት ህዳር 15/2009 ተቀጥሯል።

No comments:

Post a Comment