Search This Blog

Sunday, November 13, 2016

“እሰነጥቅሃለሁ ተብያለሁ ” አቶ በቀለ ገርባ | የአቃቤ ህግ ምስክሮች አልተሰሙም፤ የቂሊንጦ ማ/ቤት ተጠርጣሪዎችን አሟልቶ አላቀረበም

Free Bekele Gerba!!!
የፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ 4ኛ ወንጀል ችሎት ዛሬ ህዳር 2/2009 ዓ.ም በዋለው ችሎት ላይ እንደተመለከተው በእነ ጉርሜሳ አያኖ የክስ መዝገብ ከተካተቱት ተጠርጣሪዎች (22 ሰዎች) መካከል 5ቱን ማ/ቤቱ አላቀረባቸውም፡፡ የቂሊንጦ ማ/ቤት አስተዳደር ህዳር 2/2009 ዓ.ም ለፍርድ ቤቱ በጻፈው ደብዳቤ እንደገለጸው ‹4ቱ ተጠርጣሪዎች በቂሊንጦ የደረሰውን የእሳት ቃጠሎ አደጋ ተከትሎ ሸዋሮቢት ማ/ቤት ተወስደው ስላልተመለሱ› ማቅረብ አልቻለም፡፡ ማ/ቤቱ ሸዋሮቢት እንደሚገኙ ያመለከታቸው ተጠርጣሪዎች ገላና ነጋሪ፣ ገመቹ ሻንቆ፣ ደረጀ መርጋ እና ቶምሳ አብዲሳ ናቸው፡፡
ሆኖም ግን ማ/ቤቱ በስም ጠቅሶ ሸዋሮቢት ስለሆኑ ማቅረብ አለመቻሉን ከጠቀሰው ሌላ አንድ ተጠርጣሪ ችሎት አለመገኘቱን በማጣራት ፍ/ቤቱ ተጠርጣሪውን ለምን እንዳላቀረበ የማ/ቤቱን ተወካይ ጠይቋል፡፡ ሆኖም የዕለቱ ጉዳይ አስፈጻሚ ም/ሰርጀንት ዘውዱ ወልደማርያም ተጠርጣሪው በእርግጥ የት እንደሚገኝ እንደማያውቁ ተናግረዋል፡፡ ይህ የት እንዳለ ያልታወቀው ተጠርጣሪ ጭምሳ አብዲሳ ይባላል፡፡
በዛሬው የችሎት ውሎ ተጠርጣሪዎች ብቻ ሳይሆኑ ጠበቆችም ተሟልተው አለመቅረባቸው ታውቋል፡፡ የብዙዎቹ ተጠርጣሪዎች ጠበቃ የሆኑት አቶ ወንድሙ ኢብሳ አልቀረቡም፡፡ ተከሳሾችም ጠበቃቸው ከቀጠሮ በፊት ደንበኞቻቸውን ለማነጋገር ወደቂሊንጦ ሄደው ማግኘት እንደማይችሉ ተነገሯቸው መመለሳቸውን ከማወቃቸው ውጭ በዛሬው ችሎት ለምን እንዳልቀረቡ እንደማያውቁ ለችሎቱ ተናግረዋል፡፡ በችሎት የቀረቡት ሌሎች ጠበቆችም ቢሆን ቂሊንጦ ማ/ቤት ደንበኞቻቸውን በነጻነት ስለጉዳያቸው ለማነጋገር እንዳይችሉ እንቅፋት እየፈጠረባቸው መሆኑን አመልክተዋል፡፡
ችሎቱ ዛሬ የተሰየመው የአቃቤ ህግ ምስክሮችን ለመስማት መሆኑን በመጥቀስ አቃቤ ህግ ከአጠቃላይ 42 ምስክሮቹ መካከል አምስቱ መቅረባቸውን በመግለጽ ምስክሮቹ ቀርበው እንዲሰሙለት ጠይቋል፡፡ ሆኖም ግን ተከሳሾቹ ሁሉም ተሟልተው ባልተገኙበት ሁኔታ ምስክር ሊሰማ እንደማይገባ ጠቅሰው ተቃውመዋል፡፡ ተከሳሾቹ በክሱ ላይ በጋራ የቀረበባቸው ፍሬ ነገር ስላለ በተናጠል ምስክሮች ቢደመጡ መብታችንን ይነካል በሚል በጠበቆቻቸው አማካኝነት አስረድተዋል፡፡
በሌላ በኩል አቶ በቀለ ገርባ አሁን ጉዳያቸውን እየየ የሚገኘው ችሎት በክስ መቃወሚያቸው ላይ ጉዳያቸው በፌደራል ፍ/ቤት ሳይሆን በኦሮሚያ ክልል ፍ/ቤቶች ሊታይ ይገባል በሚል ያነሱትን ህገ-መንግስታዊ የመብት ጥያቄ በጣሰ መልኩ ሐምሌ 25/2008 ዓ.ም መቃወሚያቸውን ውድቅ ማድረጉን በማስታወስ፣ በፍ/ቤቱ ገለልተኝነት ላይ ጥያቄ ስላላቸው ችሎት ቀርበው ክርክር ለማድረግ እንደማይፈልጉ ቀደም ብለውም ገልተጸው እንደነበር ጠቅሰው በዛሬው ችሎት ላይም ፖሊስ በጉልበት እየደበደበ እንዳቀረባቸው አስረድተዋል፡፡
አቶ በቀለ ሌሎችንም ተከሳሾች በመወከል እንዳስረዱት ከዚህም በኋላ ችሎት የሚቀርቡ ከሆነ ተገደው እየቀረቡ እንዳሉ ችሎቱ እንዲያውቅላቸው ጠይቀዋል፡፡ ፍ/ቤቱ ውድቅ ያደረገባቸውንና በክስ መቃወሚያ የጠቀሱትን ይህንኑ የህገ-መንግስት ጉዳይ ከጠበቆቻቸው ጋር ተመካክረው ወደ ፌደሬሽን ም/ቤት የመውሰድ ሀሳብ እንዳላቸውም ጠቅሰዋል፡፡
Politician Mr Bekele Gerba in court
ፖሊስ በጉልበት መኪና ውስጥ ካስገባን በኋላ ‹‹እሰነጥቅሃለሁ›› የሚል ዛቻ እንደደረሰባቸው፣ ይህን የተናገረውን ፖሊስ ችሎት ፊት ጠቁመው በማሳየት ጭምር ገልጸዋል፡፡ ሆኖም ግን ይህን ዛቻ ያደረሰውን ፖሊስ ችሎቱ አንድም ጥያቄ ሳያቀርብለት አልፎታል፡፡
በመጨረሻም ፍ/ቤቱ በዛሬው ውሎ ያልቀረቡ ተከሳሾችን ማ/ቤት እንዲያቀርብ፣ 7ኛ ተከሳሽ ጭምሳ አብዲሳን ማ/ቤት ለምን እንዳላቀረባቸው ምክንያት እንዲያስረዳ እንዲሁም የኦሮምኛና ስዋህሊ ቋንቋዎች አስተርጓሚዎች እንዲመደቡ ትዕዛዝ በመስጠት ተከሳሾቹ ተሟልተው ሲቀርቡ የአቃቤ ህግ ምስክሮችን ለመስማት ለህዳር 6/2009 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡ ፍ/ቤት ማንኛውም ተከሳሽ በቀጠሮው ዕለት የፍ/ቤቱን ትዕዛዝ አክብሮ መገኘት እንዳለበትም ማሳሰቢያ ሰጥቷል፡፡
በዛሬው የችሎት ውሎ የኦሮምኛ ቋንቋ አስተርጓሚ ችሎቱ ባለማቅረቡ ከተከሳሾች መካከል አቶ በቀለ ገርባ በአጋዥነት ሲያስተረጉሙ ውለዋል፡፡
የዛሬውን ችሎት ከተከሳሽ ቤተሰቦች በተጨማሪ የዲፕሎማቲክ ኮሚኒቲ ተወካዮችና ጋዜጠኞች ተከታትለውታል፡፡
ምንጭ Ethiopa Human Rights Project

No comments:

Post a Comment