Search This Blog

Monday, June 13, 2022

በእርግጥ አፄአዊ የአገዛዝ ሥርዓትን (Imperial orderን) ማፍረስ አይቻልምን? ማፍረስስ አይገባምን? ማፍረስስ በዓለምአቀፉ ማህበረሰብና ሕግ የተከለከለ ነውን?

 በእርግጥ አፄአዊ የአገዛዝ ሥርዓትን (Imperial orderን) ማፍረስ አይቻልምን? ማፍረስስ አይገባምን? ማፍረስስ በዓለምአቀፉ ማህበረሰብና ሕግ የተከለከለ ነውን?

ሕዝባችን የግፍ ጦርነትና እልቂት እየተፈጸመበት መሆኑን እያዩ: የአብይን የዘር ማጥፋት ጦርነት ለማውገዝ አፋቸው የተሸበበ የወሬ ቋቶች: ከዚህም አልፈው የአብይን አገዛዝ ካልደገፍን መንግሥት ይወድቅና ኦሮሞ ችግር ውስጥ ይገባል የሚሉ የእልፍኝ አገልጋዮች: ዓይናቸውን በጨው ታጥበው: ኢምፓየርን የምናፈርስበትና የግፍ ክምርን ንደን ህዝቡ እድሉን የሚወስንበትን ሁኔታ የምናመቻችበት ስሌት የላችሁም ይላሉ::
ስለ ስሌት ካወራንማ ኢምፓየርን የመጠገኛ ስሌት እንኳን የሌላቸው እነሱ ናቸው:: ዴሞክራሲያዊ ማድረግ ይቻላል የሚሉበትን(ዴሞክራሲያዊ ሁኖ የሚያውቅ ኢምፓየር ምሳሌ መጥቀስ ባይችሉም) እንኳን: ስልትና ስሌት ባለው መንገድ ቀምረው አያውቁም:: መጠገኛ ስሌት ሲያጡ የማስፈራሪቾ (fear-mongering) ፕሮፓጋንዳ እየነዙ: ህዝቡ እየፈጀውካለው ጦርነት እንኳን እራሱን እንዳይከላከል የሚያደነዝዙት ድንዙዛን እነሱ ናቸው:: ለአብይ አህመድ (እና ለኢምፓየሩ አገረ-መንግሥት) የዘመኑ ፈረስ በመሆን የመከራን እድሜ ማራዘም (በዚህ አጋጣሚም ተጠቅሞ የሕዝብን ሃብት መዝረፍና ያልተገባ ወረት ማካበት) ኢምፓየርን የመጠገኛ ስልትና ስሌታቸው መሆኑ ነው::
ሊነገራቸው የሚገባው እውነት የሚከተለው ነው::
የኢምፓየራዊ ቅኝ አገዛዝ ሥርዓቱን (imperial-colonial order) የምንቃወመው ኃይሎች እኛ: እንኳን ኢምፓየር የምናንኮታኩትበትና ህዝብን ለውሳኔ የምናበቃበት ቀርቶ: በዴሞክራሲያዊ ጎዳና መርተን ኢምፓየሩን ሙሉ በሙሉ በመቀየር (radically transform በማድረግ) የምንቤዥበት የተሻለ ስሌት አለን:: ሞክረንም ነበር:: እድል ለመስጠት ብለን:: አንድም ኢምፓየርን መቤዠት በፍፁም የማይቻል ከመሆኑ የተነሳ: አልያም በኢምፓየሩ ባለቤት ነን ባዮች እብሪት (እና የዘላለም የአፄ ዘበኛበሆኑ—the perpetual body guards በሆኑ)--አደግዳጊዎቸቸው ተባባሪነት ምክንያት ወደ ጥፋት ገደል በመውረድ አከሸፉት እንጂ::
የዛሬዎቹ ተለዋጭ አፄያውያን ደግሞ: ያለ ምንም ፕሮግራም (ወይም በቤተመንግስት ዘበኛው ኦህ_dead ፕሮግራም) ወደ "ኢምፓየራዊ ዲሞክራሲ" እንሸጋገራለን ሊሉን ይሞክራሉ::
ወደ ማስፈራሪያቸው እንመለስ::
የዓለማቀፉ ሥርዓት: ኢምፓየር እንዲፈርስና አዲስ አገር እንዲመሠረት አይፈልግም ይላሉ:: ይሄ ትልቅ ውሸት ነው:: የዓለምአቀፉ ማህበረሰቡ ሕግጋት ሁሉ ( UN Charter, UDHR, ICCPR, ICESCR, the 1960 UN Declaration on decolonisation, the 1970 UNGA Resolution, and more recently the declaration on indigenous peoples) ኢምፓየርና ቅኝግዛትን ይኮንናሉ: ለማፍረስና ለማስቀረትም ዝርዝር ድንጋጌ ያስቀምጣሉ::
ከዚህ አልፈው:በሌሎች አለምአቀፍ ስምምነቶችና ህጎች የዘር መድሎን: አፓርታይዳዊ አገዛዝን: የዘር ማጥፋትን: ወዘተ ይኮናሉ: የሚወገድበትንና የምንከላከልበትን ዝርዝር ድንጋጌዎች ያስቀምጣሉ:: በፍርድ ሂደትም በተደጋጋሚ አዳዲስ አገሮች የሚመሰረቱበትን አግባብ ሲያስቀምጡ ተስተውለዋል:: ( ምሳሌ: የሄግ ፍርድቤት በኮሶቮ ላይ የወሰነው ውሳኔ:: የተመድ በደቡብ ሱዳን ላይ ያስማማው CPAም ተመሳሳይ ውጤት ነበረው::) ስለዚህ ዓለምአቀፉ ሥርዓት ከኢምፓየር መለየትን (መገንጠልን) አይደግፍምና ኦሮሞና ሌሎች ግፉአን ህዝቦች አብይና ጃዋርን እየደገፉ ወደ ጥፋታቸው ይጏዙ ማለት ወይ አለማወቅ ነው: ወይም አውቆ ማሳሳት ነው::
የወቅቱ አፄያውያን: አዲስ አገር ሲመሰረት ቀሪው መንግስት (the rump state) ለአዲሱ መንግሥት ፈቃድ ወይም እውቅና ካልሰጠ: አገር መሆን አይቻልም ይላሉ:: ሌላ ትልቅ ውሸት::
እውነቱ:- አገር የመመሥረት መብት (the right to statehood) እና እንደ አገር እውቅና የማግኘት (the right to recognition) መብት ይለያያሉ:: አሮጌው አገር ስንብቱን ከደገፈው (እንደ Czech እና Slovak ወይም እንደ ኤርትራና ኢትዮጵያ ወይም እንደ ሁለቱ ሱዳኖች) ዓለማቀፋዊ እውቅና ለመስጠት ቀለል እንዲልለት ያደርጋል::
አሮጌው መንግሥት አዲሱን እውቅና ከነሳው የአዲሱን አገርነት አያስቀረውም:: ከሌሎች ጋር የሁለትዮሽ (bilateral) የመገናዘብና የመስራት መብቱ የተጠበቀ ነው:: ኦሮሞ አገር ከሆነ እውቅና ያጣል ብሎ ማስፈራራት--ለዚህም ሶማሊላንድን እንደምሳሌ ማቅረብ--ተራ ማጭበርበር ነው:: አገርነትና እውቅና (Statehood and recognition) ሁለት የተለያዩ ሂደቶች ናቸውና::
አሮጌው አገር ለኦሮሞ እውቅና አይሰጠውም ብሎ መከራከርም: የኢትዮያን ሕገ-መንግሥትን አለማወቅን ያሳያል:: በሕጋዊ ሕዝበ-ውሳኔ የተፈጸመ መለየትን በማድረግ: "ንብረት በመከፋፈልና" (liquidation of assets) የአዲሱን አገር ሉዓላዊነት በማወቅ ለተበበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ማሳወቅ የኢትዮጵያ መንግስሥት ሕገ-መንግሥታዊ ግዴታ ነው:: ( አንቀጽ 39(4))
የአፍሪካ አንድነት ድርጅት (ብ1963/4) በአዲሶቹ ነፃ አገሮች መካከል የድንበር ግጭት እንዳይነሳ በማሰብ የቅኝ ግዛት የነበረው ድንበር እንዳለ ይቆያል ቢልም: Saharawi, Namibia, Eritrea, South Sudan, አገር እንዳይሆኑና እውቅና እንዳያገኙ እንቅፋት አልሆነም:: Somalilandን አገርነቷን አልከለከላትም:: (የዓለምአቀፉ ማህበረሰብ ትልቋን ሶማሊያ ለማረጋጋትና መልሶ ለማቋቋም እያደረገ ያለውን ጥረት ላለማናጋት ሲባል እውቅናን አግዶ (suspend አድርጎ) እየደከመ ስለሆነ ከዚህ ጥረት ጋር ለመናበብ ብሎ ዝም አለ እንጂ እውቅና ስላልተገባ ወይም ስላልፈለገ አይደለም::
ኢትዮጵያ የአካባቢው የሰላም መልህቅ (anchor) ነችና አዲስ አገር እንዲፈጠር ምዕራባውያን አይፈልጉም የምትል ማደናገሪያም ትጠቀሳለች:: ኢትዮጵያ የአካባቢው ሰላም ዋና አናጊ: የአካባቢው አገሮች ሁሉ በጋጠወጥነት የሚተራመሱባት የትርምስ ሜዳ መሆኗን ያየ (ውስጡ እየኖረ ያለ) ሰው: የሰላምና መረጋጋት መልህቅ ነች ሲል የምፀቱ ወሰን አልባነትን ያሳያል::
እንኳን ዛሬ በዓመት 15 ጊዜ በተመድ የጸጥታ ምክር ቤት ምትከሰስ የዓለም ሸክም ሆና ቀርቶ: አንፃራዊ አፄአዊ ሰላም (imperial peace) በነበራት ወቅትም ቢሆን "የመልህቅነቷ" መሠረቱ ኦሮሚያ እንደ ሆነ ዓለም ሁሉ ያውቀዋል:: ለአካባቢው ሰላምና መረጋጋት በዘላቂነት ዋስትና የሚሰጠው የቅራኔዎችና የተቃርኖዎች ማጨቂያ የሆነው ቡቱቶው የኢትዮጵያ ኢምፓየር ሳይሆን የኦሮሚያና የሌሎች ግፉአን ህዝቦች ነፃ መንግሥታትና በእነርሱ መካከል የሚፈጠር ፍትሃዊ አጋርነት ብቻ ነው::
የባለ ጊዜ አፄአዊያን ማስፈራሪያ ስሌት የሌለው በፍርሃት ስሜት ላይ የተመረኮዘ መቀባጠር መሆኑን ከላይ የገለፅነው ያስረዳል:: ስልትም ስሌትም የላቸውም:: ይሄን በይቅርታ ልናልፈው እንችላለን:: የማናልፈው ግን የዚህ የቅጥፈት ትንተናና መቀባጠር መነሻና መድረሻው: የኦሮሞ ሕዝብ: ከአፄአዊ አገዛዝ ለመላቀቅ የሚያደርገውን ትግል ለማንኳሰስ: የትግል ግቡ የማይደረስበት ነው በማለት ትግሉን ለማደብዘዝ: ታጋዮቹም ከመፈክርና ከስሜት ያለፈ ስልትና ስሌት የሌላቸው አስመስሎ ማቅረቡንነው::

No comments:

Post a Comment