Search This Blog

Monday, April 14, 2014

የዴሞክራሲን ሰብል-በጅብ እርሻ ‹‹ነፃነትን ተንከባከቧት እናም እውነት እራሷን ትጠብቃለች››

የጅብ እርሻ
‹‹የጅብ እርሻ›› ምን ማለት ይሆን? በእርግጥ ቃሉን የሰማሁት ድንገት ነው፡
፡ ገጠመኜን ላካፍላችሁ፡፡ እንደ ወትሮዬ ሁሉ በአንዱ ቀን ወደ 6 ኪሎ ለመጓዝ ፒያሳ ከሚገኘው የጥንት የጠዋቱ ሲኒማ ኢትዮጵያ በር ላይ ወደ ቅድስት ማርያም የሚሄድ ታክሲ ላይ ተሳፈርኩ፡
፡ አንድ በእድሜያቸው ጠና ያሉ ሽማግሌ ሰው ከጎኔ ባለው ባዶ መቀመጫ ላይ ተቀመጡ፡፡ የሽማግሌው አካላዊ ቁመና ረጅም እና ግዙፍ ነው፡፡ ወታደራዊ ቁመና እንዳላቸው መመልከት ይቻላል፡፡ እንደዋዛም ጨዋታ ጀመርን፣ በመሀሉም እንዲህ አሉኝ ‹‹አብዛኛውን ጊዜ ታክሲ ውስጥ አምስት እና አስር ሳንቲም ሲያስቀሩብኝ መልስ ስጡኝ ብዬ አልጠይቅም፡፡ ከክብሬ በታች መስሎ ስለሚሰማኝ ነው፡፡ የዘመኑ ወጣት ግን ለትንሽ ሳንቲም ሲል ለድብድብ ሁሉ ሲጋበዝ አየዋለሁ፡፡›› ባሉት ነገር መስማማቴን በፈገግታ ገልጬላቸው ጨዋታችንን ቀጠልን፣ እግረ መንገዳቸውንም የክብር ዘበኛ አባል እንደነበሩ በኩራት ነገሩኝ፡፡ አስከተሉናም ‹‹መንግስቱ ነዋይን ያኔ በግርግሩ ጊዜ ሳናውቅ አሳሰርን፡፡ ምን ያደርጋል ‹‹የጅብ እርሻ›› የሚል ቃል ተናገሩ፡፡ ሆኖም በየመሀሉ ቃሉን ደጋገሙት ‹‹የጅብ እርሻ››፣ ‹‹የጅብ እርሻ…›› ይህን ቃል ሰምቼው ስለማላውቅ ምን ማለት እንደሆነ ለማወቅ ጓጓሁ፡፡ ሽማግሌው እኔ ከምወርድበት ሳልደርስ ቀድመው ወረዱ፡፡ ምንም እንኳ ወደምሄድበት ቦታ ባልደርስም ከሳቸው ጋር ጥቂት የመጨዋወቱ እድል እንዲያመልጠኝ ስላልፈለኩ ተከትዬአቸው ወረድኩ፡፡ እናም በጭውውታችን መሀል ‹‹ሰሙ ወይ ይህች የጅብ እርሻ የምትለው ቃል ምንድን ነች?›› ብዬ ጠየኳቸው፡፡ እርሳቸውም ፈገግ አሉና ሰማህ ወይ ‹‹ጅብ አያርስም፣ ካረሰ ግን እስኪያድግ አይጠብቅም፡፡ ገና በቡቃያው ይበላዋል›› ሲሉ የጅብ እርሻ ማለት ምን ማለት እንደሆነ አስረዱኝ፡፡
We need Democracy and justice in our country!!!! Ashenafi
እኔም በአንድ በኩል የኢህአዴግን አካሄድ፣ በሌላ በኩል በተቃዋሚ ፓርቲዎች መካከል የሚካሄደውን ሁኔታ ሊያስረዳልኝ/ ሊገልፅልኝ የሚችል ሀሳባዊ ተምሳሌት (metaphor) በማግኘቴ በጣም ደስ ብሎኝ ተሰነባበትን፡፡
በዚህ የሃያ አመት የስልጣን ዘመኑ ኢህአዴግ አልፎ አልፎ ብሩህ የሆነ ጅማሮዎች ወይንም የዴሞክራሲ ተክሎች ነበሩት፡፡ ሆኖም ብዙዎቹ ፕሮግራሞች ገቢራዊ ሳይሆኑ በእንጭጩ ተበልተዋል፡፡ ትልቅ ደረጃ ይደርሳሉ የተባሉ እና ውጤት ያስመዘገቡ ተቃዋሚ ኃይሎችም ቢሆኑ ከውስጥ በተነሳ ሽኩቻ ተበልተዋል፡፡
የዚህ ፅሁፍ አላማ በፖለቲካ ነፃነት፣ በህግ እና በፍትህ መካከል ያለውን ግንኙነት በትንሹ ከዳሰስን በኋላ የተጀመሩት ራዕዮች እንዴት ግባቸውን ሳይመቱ እንደተቀጩ ለማሳየት ነው፡፡
ፖለቲካ በይዘቱ በሶስት ማህበራዊ መዋዕቅሮች መካከል የሚደረግ የትግል ውጤት ነው፡፡ ይኸውም በግለሰብ፣ በቡድን እና በመንግስታት መካከል ስልጣንን ለማግኘት ሲባል የሚደረግ ፍልሚያ ነው፡፡ በሌላ በኩል ትግሉ በመብት እና በጭቆና፣ በነፃነት እና በኃይል፣ በነፃነት እና እኩልነት፣ እንዲሁም በሀሳብ እና በጉልበት መካከል ያለ ተቃርኖ ስለሚሆን ሽኩቻው ሁልጊዜም ለግል ጥቅም ብቻ ሳይሆን የሀገርንም ጥቅም ታሳቢ አድርገው በተነሱ ተፋላሚዎች መካከል የሚካሄድ ሂደት መሆኑን መረዳት ይኖርብናል፡፡
የማንኛውም ፖለቲካ ስርዓት ሙሉ በሙሉ ዴሞክራሲን እውን ለማድረግ ስለማይችል የፖለቲካ ኃልዮት (Theory) በይዘቱ ላለበት ስርዓት ሂሳዊ እና ተቺ እንዲሆን ይገደዳል፡፡ በአንፃሩም አቃፊ እና ደጋፊ የሆነ የፖለቲካ ንድፈ ሀሳብ (Theory) ፖለቲካዊ ብቻ ይሆንና ኃልዮት መሆኑ ይከስማል፡፡ ይሄ ነጥብ በተለይ በኢትዮጵያ ሁኔታ ተገቢ ስፍራ አለው ብዬ ስለማምን በዚህ መጣጥፍ ላይ የማሰፍረው ሃሳብ ሂስዊና ተቺ መሆኑን ከወዲሁ ማሳወቅ እፈልጋለሁ፡፡

ነፃነት
ነፃነትን በሚመለከት አብይ የሆነውን ሀሳብ በአንድ እና ሁለት ቃላት ብናስቀምጥ፤ ነፃነት ማለት ማናቸውም ገደብ የለሽ ክዋኔ (Absence of restraints) ሲኖር ማለት ነው፡፡ ሆኖም ግን ይሄ ነፃነት ፍፁማዊ ሳይሆን በተወሰነ መልኩ የአንፃራዊነት መልክ አለው፡፡
በአንድ ማህበረሰብ ውስጥ መብትን በሚመለከት ጐልቶ የሚታየው ጫና የሚመነጨው ከመንግስት ነው፡፡ ቢሆንም መንግስት እንደ ፖለቲካ ኃይል የዜጎችን መብት በተወሰነ መልኩ ሊገታው ይችላል እንጂ ጨርሶ ሊደመስሰው አይችልም፡፡ የመንግስት ጫናም ሆነ ጣልቃ ገብነት ህግን ተንተርሶ ወይንም ህጉ የሚጠይቀውን መስፈርት አሟልቶ ሲገኝ ብቻ እንጂ እንደዚሁ በዘፈቀደ መብትን ሊፈታተን አይችልም፡፡
በዴሞክራሲያዊ ስርዓት ውስጥ ያሉ ማህበረሰቦች ምንጊዜም ቢሆን የሚከተሉትን አራት የ‹‹ነፃነቶች›› አውዶች ተጋሪዎች ናቸው፡
፡ እነዚህም
ሀ. የፖለቲካ ነፃነት
ለ.ህጋዊ ነፃነት
ሐ.ግለሰባዊ ነፃነት
መ. ተቋማዊ ነፃነት ናቸው፡፡
ከላይ ለመጥቀስ እንደተሞከረው የፖለቲካዊ እና ህጋዊ ነፃነት ሁኔታን ለመረዳት በቅርቡ ወዳለፍነው ሁለት የፖለቲካ ስርዓቶች መለስ ብለን ማለትም ከዘውዳዊ አገዛዝ እና ከሶሻሊስት ስርዓቱ ጋር ትንሽ ንፅፅር እናድርግ፡፡
ዘውዳዊ አገዛዝ እና ህግ
እንደ እውቁ የእንግሊዝ የ17ኛው ዘመን ፈላስፋ ጆን ሎክ አስተምህሮት የሰው ልጅ ‹‹ሲቪል ማህበረሰብ›› ከማቋቋሙ በፊት ‹‹ተፈጥሮአዊ ማህበረሰብ›› ውስጥ ይኖር ነበር፡፡ ሆኖም ግን በተፈጥሮ የተገኘው የማህበረሰብ አደረጃጀት ሰው አመቺ ሆኖ ስላላገኘው ወደ ሲቪል ማህበረሰብ ተሸጋግሯል፡፡ ሎክ ለዚህም ሽግግር አብይ የሆነው ምክንያት የሚለው ህግን እና ዳኝነትን በሚመለከት ዙሪያ ነው፡፡ እንደ እርሱ አቀራረብ ፍትህ እንዲገኝ ከተፈለገ በሰዎችመካከል ያለን ጭቅጭቅ ነፃ በሆነ ዳኛ መበየን አለበት ብሎ ስለሚያምን ሲቪል ማህበረሰብ ሲቋቋም ገለልተኛ የሆነ የዳኝነት እርከን አብሮ መቋቋም እንዳለበት አሳስቧል፡፡
ከእርሱ አስተምህሮት ስንነሳ የዘውዳዊ አገዛዝ ስርዓት ከተፈጥሮአዊ አደረጃጀት የተሻገርነውን የግለሰቦች በራስ ጉዳይ ዳኝ ከመሆን ያልተላቀቀ ስለሚሆን ሲቪል ማህበረሰብ የተቋቋመበትን ዋነኛ ሀሳብ የሚፃረር ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ በመሆኑም ይሄንን ቅራኔ ለመቅረፍ በሎክ ሀሳብ ዘውዳዊ አገዛዙ ወደ ህገ መንግስታዊ የዘውድ አገዛዝ ወይንም ህገ-መንግስታዊ የስልጣን ክፍፍል አደረጃጀት መዋቅር መሸጋገር ይገባዋል፡፡
ከዚህ አስተምህሮት አንድ ወሳኝ የሆነ መርህ እናገኛለን፡፡ ይኸውም ‹‹ማንም ግለሰብ፣ ቡድን፣ መንግስት በራሱ ጉዳይ ላይ እራሱ ዳኛ መሆን አይችልም››፡፡ ይሄ ብሂል በአውሮፓውያኑ ብቻም ሳይሆን በኛም ሀገር ያለ የህግ አመለካከት ነው፡፡ ወደ የዘውዳዊ ስርዓት ስንመለስ ከዚህ መርህ አኳያ ዋናው ችግር ንጉሠ ነገሥቱ በራሱ ጉዳይ ላይ እራሱ ዳኛ መሆኑ ነው፡፡
እንግዲህ ከዚህ ስንነሳ የቀድሞው ዘውዳዊው ስርዓት የራስን ጉዳይ በራስ የመወሰን የህግ አካሄድ አሁን ካለንበት የፍትህ ስርዓት ጋር ስናነፃፅር በዚህ ጥያቄ ዙሪያ የአሁኑ የፍትህ ሥርዓት ይህንን ሽግግር ተሻግሮታል ወይ ብለን መጠየቁ ተገቢ ይሆናል፡፡ እኔ እንደምረዳው የተጠናከረ የፍትህ አካል በሌለበት ሁኔታ መንግስት በራሱ ጉዳይ የራሱ ዳኛ መሆኑ አይቀሬ ነው፡፡
የሶሻሊስት ስርዓት እና ህግ
ሶሻሊስት ስርዓት ከግለሰብ ህጋዊ መብት ይልቅ ወደ ማህበረሰብ ጥቅል መብት ስለማያደላ ብዙሃኑን እስከጠቀመ ድረስ እነ መብት፣ ነፃነት የመሳሰሉት ወደ ጐን ይገፈተራሉ፡፡ በሶሻሊስት ስርዓት ለሰው ልጅ እጅግ አስፈላጊ ናቸው ከሚባሉት እሴቶች መካከል ‹‹እኩልነትን›› ብቻ በዋነኝነት በማቀንቀን ግለሰቡ ላይ የፖለቲካ እና ህጋዊ ጥሰት ያራምዳል፡፡
በህግ አኳያ ስናየው ዋናው የሶሻሊስት ድክመት ወይም ግድፈት ከ‹‹ሀ›› አንስቶ ለ‹‹ለ›› ያለ ‹‹ሀ›› ፍቃድ መስጠት ትክክል አይደለም የሚለውን ህጋዊ መርህ መጣሱ ነው፡፡
አሁን በቅርቡ በመሬት ሊዝ ላይ ያለውን ጭቅጭቅ እንደምሳሌ ብንወስድ የኢህአዴግ ሹመኞች ሊዙ ለምን እንደሚያስፈልግ ከሚያቀርቡት ክርክር መካከል አንደኛው መሬቱን ወስደን የጋራ መኖሪያ ቤት ለሰፊው እና ለጭቁኑ ህዝብ እንሰራለን የሚለው ነው፡፡ ይህንን የሚቃወሙትም ጥቂት ተጠቃሚዎች ብቻ (ኪራይ ሰብሳቢዎች) ናቸው ሲሉ ይደመጣሉ፡፡
ይሄ አካሄድ ባንድ ቴሌቪዥን ክርክር ላይ የኢዴፓው ተወካይ አቶ ሞሼ ሰሙ አዲሱ የሊዝ አዋጅ መንግስትን ወደ መሬት ማከፋፈል እየወሰደው እንደሆነ ይጠቁማል ሲሉ የገለፁት ሀሳብ ያለበትን ሁኔታ በደንብ ይገልፀዋል የሚል እምነት አለኝ፡፡
ከላይ ከተጠቀሱት ሁለት ንድፈ ሀሳቦች በመነሳት የኢህአዴግ የህግ ስርዓት ከዘውዳዊ አገዛዝ እና ከሶሻሊስት ስርዓት የወረሳቸው ወይንም ያልተሻገራቸው ሁለት የህግ ግድፈቶች አሉ የሚል እምነት አለኝ፡፡ ይኸውም በራሱ ጉዳይ ራሱ ዳኛ መሆን እና ከአንዱ አንስቶ ለአንደኛው ተበድሏል ወይም ተጨቁኗል በማለት ያለፍቃድ ማከፋፈል የሚሉት ናቸው፡፡ ሲጠቃለል ኢህአዴግ ካለፈው የዘውዳዊ ስርዓት እና የሶሻሊስት ስርዓት ያልተላቀቃቸው ግድፈቶች አሉበት ማለት እንችላለን፡፡
ኢህአዴግ እና የአንድ ወጥነት ፍልስፍና (Monism)
ሞኒዝም በጥቅሉ ሲታይ በማህበረሰብ ውስጥ የሚከሰቱ ጉዳዮች ወደ ጥያቄ እና መልስ እርከን በማውረድ ምንጊዜም አንድ መልክ የያዘ ጥያቄና አንድ መልክ የያዘ መልስ አለ ብሎ ያምናል፡፡ በዚህ ርዕስ ዙሪያ ትልቅ ድርሳን የፃፉት የኦክስፎርዱ ፕሮፌሰር የነበሩት ሰር አይዛያ በርሊን (Sir Isaiah Berlin) ናቸው፡፡ እንደሳቸውም አቀራረብ የአንድ ወጥነት ፍልስፍና (ሞኒዝም) የሚከተሉትን ባህሪያት የያዘ ነው፡፡ የመጀመሪያው ልክ እንደ ተፈጥሮ ሳይንስ ችግሮቹን ጥያቄ የሚል ስያሜ በመስጠት ፍፁማዊ መልስ አላቸው ብሎ ያምናል፡፡ ሁለተኛው ለነዚህም ጥያቄዎች የሚሰጠው መልስ ብቸኛ እና ማህበረሰቡ በግልጽ የሚያያቸው ናቸው ብሎ ያምናል፡፡ ሶስተኛ በሚቀርቡት መልሶች መካከል ምንጊዜም ቅራኔ ሊኖር አይችልም የሚል እምነት አለው፡፡
እንደ ፕ/ር በርሊን አገላለፅ የሞኒዝም ፍልስፍና መሰረቱ ከዘመኑ አብርሆት ወይንም ብርሃነ ህሊና (Enlightenment) ከሚባለው የመነጨ ሲሆን በተለይ በከፍተኛ ደረጃ ተቀብለው ያስተጋቡት የ20ኛው ክ/ዘመን ሶሻሊስቶቹ ናቸው፡

በመሆኑም የዚህ አንድ ወጥነት ፍልስፍና ሁለት አበይት የሆኑ ችግሮች አሉት፡፡ አንደኛው ከላይ እንዳልነው ለአንድ ጥያቄ አንድ መልስ አለው ብሎ ስለሚቀበል ሌላ አይነት አመለካከት፣ አቀራረብ ወይንም የመፍትሄ ሀሳብን አያስተናግዱም፡፡
ለምሳሌ የቤት እጥረት ካልክ ኮንደሚኒየም፣ መሬት ካልክ ሊዝ፣ የብሔር እኩልነት ካልክ ፌደራሊዝም፣ ክህሎት ካልክ ስልጠና ወዘተ፡፡ በተጨማሪም እነኚህ አንድ ወጥ መልሶች እርስ በርሳቸው ወይንም ከሌላ እሴት ጋራ ግጭት ሊኖራቸው ይችላል የሚል እምነት የላቸውም፡፡ በመሆኑም በነፃነት እና በእኩልነት፣ በስልጠና እና በትምህርት፣ በቁጥር እና በጥራት ወዘተ መካከል ያለውን ቅራኔ አይመለከቱም፡፡ ምንጊዜም ፖለቲካውን እንደ ደረቅ የተፈጥሮ ሳይንስ አንድ ጥያቄ ጠይቆ እዛው እርግጥ ያለ መልስ የሚገኝበት ሳይሆን በውይይት እና በምይይጥ ተያይዞ የሚዘልቅ ሂደት ነው፡፡ ካቀረበው መፍትሄ ውጭ ሌላ አማራጭ ለማስተናገድ ስለማይሞክር ሞኒዝም በተፈጥሮ ኢ-ዴሞክራሲያዊ አካሄድን ያዘለ ነው እንላለን፡፡ በሌላ በኩል ሁለተኛው የሞኒዝም ችግር ስናየው በአንድ ማህበረሰብ ውስጥ የተለያዩ በጐ እሴቶች ቢኖሩም መንግስት ግን ሁሉንም በጠቅላላ ቋጠሮ ውስጥ ከቶ በተመሳሳይ መልኩ አንድ ወጥ በሆነ ፖለቲካዊ አተያይ እንዲመራ እና መፍትሄውም ለሁሉም አንድ ወጥ የሆነ መልስ ብቻ እንዳላቸው አድርጐ የማቅረብ አባዜ ነው፡፡
የፍትህ አካላት፣ የትምህርት ተቋማት፣ የመብት ተከራካሪ ቡድኖች በራሳቸው ያለማንም ጣልቃ ገብነት ለማህበረሰቡ የሚሰጡት ፋይዳ ያለው አገልግሎት ብቻውን ተቀዳሚ አላማ ቢሆንም ለሚፈለገው ልማት በተዘዋዋሪ የሚያበረክቱት አስተዋፅኦ በዚህ ረገድ ነፃ ከሆኑ ከፍተኛ ነው የሚሆነው፡፡ ነገር ግን እነዚህ ነፃ ተቋማት በአንድነት ተጨፍልቀው ስራቸውን ሁሉ ወጥ ወደ ሆነው ማህበረሰባዊ ጥያቄ (ልማት ተብሎ ለተሰየመው) ለመመለስ ብቻ ከሄድን የታለመላቸውን ተልዕኮ ሊወጡ አይችሉም፡፡
የፍትህ እና የትምህርትን ጉዳይ እንደምሳሌነት ብንወስድ የፍትህ ተቋም በራሱ ፍትሃዊ ግብ እና በጐ እሴት ያለው እንደሆነ መሆኑ ይቀርና ተቋሙና ዳኞቹ የልማት ተልዕኮ ማቀፍ እንዳለባቸው ሲደረጉ በዋነኝነት የተመሰረቱበትን አላማ ይጥሳሉ የሚል አመለካከት አለኝ፡፡ ትምህርትም ቢሆን በራሱ ትልቅ ጉዳይ መሆኑ ይቀርና ግቡ የሚመዘነው በሚያመርተው እና የገበያውን ፍላጐት ለማርካት በሚለው መመዘኛ ከሆነ ችግር ያመጣል፡፡
ለማጠቃለል፡፡ አሁን ያለውን የኢትዮጵያ የህግ፣ የፖለቲካ እና የነፃነት ድባብ ላጤነ ሰው በከፊል የሚከተሉት ሶስት ድምዳሜዎች ላይ መድረሱ አይቀሬ ነው፡፡
1. ማንም ሰው በህግ ተጠያቂ ሲሆን የተቋቋመው ፍርድ ቤት ጥፋተኛ ሆኖ እስካላገኘው ድረስ በዛች የእስራት ዘመን ወይም ከውጭ ሆኖ ሲከራከር የመጨረሻ የፍርድ ቤቱ ቃል እስከሚደርስ ድረስ ሰውየው ንፁህ ነው (Presumption of Innocence) የሚል ግምት ለተከሳሹ ይሰጣል፡፡ ይሄ ግምት አንዳንድ የመንግስቱ ሹመኞች እንደሚከራከሩት መንግስትን አይጨምርም፡፡ የፍርዱ ሂደት እስከሚያልቅ የዜጐችን መብት ለመጠበቅ እንጂ በመንግስት የቀረበውን ውንጀላ ልክ ነው ለማለት አይደለም፡፡
2. የገዢውን ፓርቲ የአሰራር ዘይቤ በምናይበት ጊዜ በአብዛኛው ዴሞክራቲክ ገፅታ ለማንፀባረቅ የሚከውኗቸው ድርጊቶች ልማዳዊ (Rituals) ናቸው፡፡ እንደምሳሌም ብንወስድ ከወረዳ እስከ ዞን የሚካሄዱ ስብሰባዎች የዴሞክራቲክ መልክ ቢይዙም እውነተኛ የሆነ (Authentic) ውይይቶች ሲካሄዱ አይታይም፡፡ እንዲሁም በየስብስባዎቹ ድባብ በግልፅ ማየት የሚቻለው ሰብሳቢው ገዢ፣ ተሰባሳቢው ተገዢ ሆነው ‹‹ሰዎቹን››፣ ‹‹ማህበረሰቡን››፣ ‹‹ባለድርሻ አካላቱን›› አወያየን የሚለው ፈሊጥ ለታይታነት እና ከማስመሰል ያለፈ ሆኖ አናገኘውም፡፡
3. የገዢው ፓርቲ በመንግስት እና በሲቪል ማህበረሰብ መሀል ምንም አይነት ልዩነት አለ ብሎ ስለማያምን ከሃይማኖታዊ ተቋም እስከ አለማዊ የሆኑ ስብስቦችን የማካተት እና የመዋጥ (የጅብ እርሻ) አባዜ በእጅጉ ተፀናውቶታል፡፡

No comments:

Post a Comment