Search This Blog

Sunday, June 8, 2014

በሀሮሚያ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ላይ በቦምብ ጉዳት ያደረሱ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ዋሉ

በኦሮሚያ ክልል ሀሮሚያ ዩኒቨርስቲ በያዝነው ግንቦት ወር በቴሌቪዥን የእግር ኳስ ጨዋታ ይከታተሉ በነበሩ ተማሪዎች ላይ የእጅ ቦንብ ወርውረው በሰው ህይወትና አካል ላይ ጉዳት ያደረሱ አራት ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር ማዋሉን የፀረ ሽብር ግብረ ሀይል አስታወቀ፡፡
ከተጠርጣሪዎቹ መሀከል አንዱ በፖሊስ ጥበቃ ስር እያለ ህይወቱን በገዛ እጁ ማጥፋቱን ግብረ ሀይሉ አክሎ ገልጿል፡፡
የብሄራዊ የመረጃና ደህንነት አገልግሎት ከፌዴራል ፖሊስ የጋራ የፀረ ሽብር ግብረ ሀይል ጋር ዛሬ በሰጠው መግለጫ ተጠርጣሪዎቹ አበበ ኡርጌሳ፣ኑረዲን ሀሰን፣ኒሞና ጫሊ እና መገርሳ ወርቁ የተባሉ የሀሮሚያ ዩኒቨርስቲ በተለያዩ ፋካልቲዎች ውስጥ የሚማሩ ተማሪዎች መሆናቸውን አስታውቋል፡፡
የጋራ የፀረ ሽብር ግብረ ሀይሉ ከኦሮሚያ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ጋር በመተባበር ባደረገው ክትትል በተያዙት አራት ተጠርጣሪዎች ላይ እስካሁን የተደረገው ምርመራ ተጠርጣሪዎቹ አደጋውን ባደረሱበት እለት ከቀኑ 9 ሰዓት ላይ በዩኒቨርስቲው ቅጥር ግቢ በተለምዶ ወለጋ ላውንጂ ተብሎ በሚጠራው ክበብ ጀርባ መሰብሰባቸውን መግለጫው አመልክቷል፡፡
መግለጫው በማያያዝም ተጠርጣሪዎቹ የቦምብ ጥቃት ለመፈፀም ማሰባቸውን፣ የእጅ ቦንብ መዘጋጀቱንና ከመሀላቸው አበበ ዑርጌሳ ጥቃቱን እንዲፈፅም መመረጡን በመግለፅ ፍቃደኝነቱ ካረጋገጡ በኋላ ኑረዲን ሀሰን የተባለው ቦንቡን በጃኬቱ ጠቅልሎ ለአበበ ዑርጌሳ ማስረከቡን አመልክቷል፡፡
የቦንብ አወራወር ቴክኒኩን ደግሞ ኒሞና ጫሊ ለአበበ ያሳየው መሆኑን መግለጫው ያመለክታል፡፡
እነዚህ ተጠርጣሪዎች በፈፀሙት ጥቃት አብዲሳ አደም ኢስማኤል የተባለውና የጀንደር ጥናቶች የአንደኛ ዓመት ተማሪ የነበረው ወጣት በደረሰበት ከባድ ጉዳት ሆስፒታል ከገባ በኋላ ህይወቱ አልፏል፡፡ ከ18 በላይ የሚሆኑ ሌሎች ተማሪዎች ደግሞ በፍንዳታው ከባድና ቀላል የአካል ጉዳት የደረሰባቸው መሆኑን ያሳወቀው የግብረሀይሉ መግለጫ በተጠርጣሪዎቹ ድብደባም ወደ 50 የሚጠጉ ተማሪዎች ጉዳት እንደደረሰባቸው አክሎ ገልጿል፡፡
እንደመግለጫው ከሆነ አበበ ኡርጌሳ ቦንቡን ከወረወረ በኋላ ይዞት በነበረው የፌሮ ብረት በአካባቢው የነበሩ ተማሪዎችን ደብድቦ ጉዳት አድርሷል፡፡ በአጥር ዘሎ ካመለጠ በኋላ ከተሸሸገበት ደቡብ ምእራብ ሽዋ ዞንም በተደረገው ክትትልና የህዝብ ትብብር በቁጥጥር ስር ውሏል፡፡ ቦንቡ ከተወረወረ በኋላ ቀሪዎቹም ተጠርጣሪዎች ካደራጇቸው ሌሎች ተማሪዎች ጋር በመሆን ከቦንቡ ጥቃት የተረፉ ተማሪዎችን በፌሮና በድንጋይ ደብድበዋል፡፡
ሁኔታዎች ተረጋግተዋል በሚል ግምት ወደ ሀሮማያ ዩንቨርሲቲ የተመለሱና በተለያዩ ቦታዎች ተሰውረው የቆዩት ኒሞላ ጫሊና ኑረዲን ሀሰን የተባሉ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን መግለጫው አትቷል፡፡
በፖሊስ ጥበቃ ስር እያለ ራሱን በገዛ እጁ ያጠፋው አንዱ ተጠረጣሪ በድሬዳዋና በአዲስ አበባው ሚኒሊክ ሆስፒታል አስከሬኑ ላይ የተደረጉ ምርመራዎችም የሞቱ መንስኤ ራስን አንቆ መግደል መሆኑን ማረጋገጣቸውን መግለጫው አክሎ ገልጿል፡፡ 

No comments:

Post a Comment