Search This Blog

Monday, October 27, 2014

ወያኔያዊ ዲሞክራሲ!

ወያኔያዊ ዲሞክራሲ!

በአሸናፊ ንጋቱ

ኢትዮጵያ ውስጥ ዴሞክራሲ የሚለውን ቃል ለመጀመሪያ ጊዜ ጥቅም ላይ የዋለበትን ጊዜ ይህ ነው ብሎ ለመናገር
የጠለቀ ጥናት ይጠይቃል፡፡ ነገር ግን የሁለተኛውን የዓለም ጦርነት ተከትሎ በወጡት ዓለማቀፍ ህጎች እና መርሆች
በመንተራስ በፀደቀው የ1955ቱ ሕገ መንግስት ላይ ዴሞክራሲያዊ መብቶች በሚል ስያሜ የዜጎች መብቶች ተቀምጠው
እናገኛለን፡፡ ያም ቢሆን የንጉሱ ስርዓት ራሱን ዴሞክራሲያዊ ብሎ ጠርቶ አያውቅም - ደግ አደረገ፤ ፈላጭ ቆራጭ
ነበርና፡፡

የንጉሱ ስርዓት ማብቂያ ላይ ብቅ ብቅ ማለት የጀመሩት ‹የመጀመሪያዎቹ› የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች ራሳቸውን
ዴሞክራሲያዊ ብለው ከመጥራት ይልቅ ሕብረተሰባዊ፣ አብዮታዊ፣ ወ.ዘ.ተ የሚሉ ቃላትን ተመራጭ ያደርጉ ነበር፡፡
ለዚህም ጥሩ ማሳያ የሚሆኑን የንጉሱን ስርዓት መገርሰስ ተከትሎ ብልጭ ብላ በነበረችው ‹የነፃነት ጮራ› በመጠቀም
እስከ ቀይ ሽብር ማብቂያ ድረስ ለምልመው ከነበሩት ፓርቲዎች ውስጥ የዋነኛዎቹን ስያሜ ብንመለከት፤ የመላው
ኢትዮጵያ ሶሻሊስት ንቅናቄ (መኢሶን)፣ አብዮታዊ ሰደድ፣ የወዛደር ሊግ (ወዝሊግ)፣ የኢትዮጵያ ጭቁኖች አብዮታዊ
ትግል (ኢጭአት) እና ማርክሳዊ ሌኒናዊ ሪቮሊሽናዊ ድርጅትን (ማሌሪድ)፤ እንዲሁም እነዚህ አምስት ድርጅቶች በጋራ
የመሰረቱትን የኢትዮጵያ ማርክሳዊ ሌኒናዊ ድርጅቶች ህብረት (ኢማሌዲህ) በአንድ ወገን ስናገኝ፤ በሌላ በኩል ደግሞ
የኢትዮጵያ ህዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲን (ኢህአፓ) እናገኛለን፡፡

ከነዚህ ዋነኛ ፓርቲዎች ውስጥ አንዱም ዴሞክራሲን የስም ማሸብረቂያ ሲያደርጋት አይታይም፤ አልደፈረምም፡፡ ደርግ
በአፈሙዝ በዙሪያው ያሉትን ፓርቲዎች አንድ ባንድ ካስወገደ በኋላ የወዛደሩን ፓርቲ የኢትዮጵያ ሰራተኞች ፓርቲ
ኮሚሽን (ኢሰፓኮ) በኋላ የኢትዮጵያ ሰራተኞች ፓርቲን (ኢሰፓ) መሰረትኩ አለ፤ እስከዚህ ጊዜ ድረስም ዴሞክራሲን
ተዳፍሮ ለስም መጠሪያነት አላዋለም ነበር፡፡ ነገር ግን ወታደራዊው መንግስት በዙሪያው ነፍጥ ያነገቡ ሀይላት እየገፉ
ሲመጡበት እና የምስራቁ ርዕዮተ ዓለም ሲዳከም ተመልክቶ ‹በአዎጅ ሀገር አስተዳድራለሁ› የሚለውን ቀረርቶ በማቆም፤
ለሕዝቡ ‹ዴሞክራሲያዊ ሕገ መንግስት› እነሆ አልኩ ሲል፤ በዛውም የሀገሪቱን ብሄራዊ መጠሪያ ዴሞክራሲ በተባለችው
ምትሃተኛ ቃል አስጊጧት ነበር - ‹የኢትዮጵያ ሕዝባዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ›፡፡

የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢህአዴግ) ግንባር ከጅምሩ ራሱን ዴሞክራሲያዊ ብሎ በመጥራት
የፖለቲካውን ገበያ የተቀላቀለ ሲሆን፤ እርሱን ከመሰረቱት አራት ፓርቲዎች ውስጥ ከሕዝባዊ ወያነ ሃርነት ትግራይ
(ህወሃት) በቀር ሶስቱ ብሄረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ብአዴን)፣ የኦሮሞ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ኦህዴድ)፣
የደቡብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ደኢህዴን) ያችን ‹ወርቃማ ቃል› መለያቸው አድርገዋታል፡፡ ይህ ብቻ
አይደለም በኢህአዴግ አጋርነት ቀሪዎቹን አምስት ክልሎች ከሚያስተዳድሩ ፓርቲዎች ውስጥ ከሀረሪ ብሔራዊ ሊግ
(ሀብሊ) በቀር አፋርን፣ ሶማሌን፣ ጋምቤላን እና ቤንሻንጉል ጉምዝን የሚያስተዳድሩት አጋር ፓርቲዎች ስያሜያቸውን
በምትሃተኛዋ ዴሞክራሲ ያደመቁ ሁነው እናገኛቸዋልን፡፡

ተቃዋሚ ፓርቲዎቻችንም ‹ዴሞክራሲ› ለተባለው ቃል ያላቸው ፍቅር የበዛ ነው፡፡ ዴሞክራሲን በስያሜነት ያልተጠቀመ
የተቃዋሚ ፓርቲ የህዝብን ይሁንታ አያገኝም የተባለ ያክል፤ የተቃዋሚው ሰፈር በዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ፣ የዴሞክራሲ
ግንባር፣ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ፣ ዴሞክራሲያዊ ህብረት ወ.ዘ.ተ በሚሉ የዴሞክራሲ ቅጽል የተዋቡ ናቸው፡፡

ይሄን እይታችንን ወደ ሀገሪቱ መጠሪያነት ስንወስደው ደግሞ፤ የሀገራችን ብሄራዊ መጠሪያ ከዴሞክራሲ ጋር የተፋቀረ
ሆኖ እናገኝዋለን፡፡ ወታደራዊው መንግስት አስራ ሶስት ዓመታትን ዘግይቶ ባወጣው ሕገ መንግስቱ ንቆ ትቶት የነበረውን
ዴሞክራሲ ለስርዓቱ መጠሪያነት ‹የኢትዮጵያ ሕዝባዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ› በማለት አውሎታል፡፡ ወታደራዊውን
መንግስት የተካው ወያኔ በበኩሉ የወታደራዊውን መንግስት ሕገ መንግስት ቀይሮ ባወጣው አዲስ ሕገ መንግስት
‹የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክን› እንደመጠሪያነት ተጠቅሞ በአፍሪካ ራሳቸውን ‹ዴሞክራሲያዊ
ሪፐብሊክ› ብለው ከሚጠሩት ከኮንጎ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ እና ከአልጀሪያ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ጋር
በሶስተኝነት ተሰልፏል፡፡ እንግዲህ የሀገሪቱ መጠሪያ ዴሞክራሲያዊ ከተባለ ሩብ ምዕተ ዓመት አስቆጥራለች ማለት ነው።

እንግዲህ ያንድ ወጣት እድሜ ያስቆጠረው የዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ ብሄራዊ መጠሪያ እውን መሬት ላይ ያለችውን
ኢትዮጵያን ይወክላል ወይ? ትንሹም ትልቁም ‹ዴሞክራሲ› የተሰኝችውን ቃል እየመዘዘ ስሙ ላይ ሲለጥፍ፤ እውን ራሱን
ለዴሞክራሲ ፅንሰ ሀሳብ አስገዝቶ ነውን? ወይስ እንዲሁ ማታለያ ነች? ነው ጥያቄው፡፡

እኛም ሀገር ዴሞክራሲ ዴሞክራሲን በፓርቲ ፕሮግራም አድማቂነት፤ ዴሞክራሲን በሕዝብ ግንኙነት መሪ ቃልነት
ይጠቀማሉ ፤ ሕዝቡም እንደመናፍስቱ ወደነሱ ይቀርባል፤ በዙሪያቸውም ይሰበሰባል፤ ያኔ አይኑን ያውሩታል በሕዝቡ
ስም ይነግዳሉ፡፡ ይህም ማለት ፖለቲከኞቻችን ዴሞክራሲን እንደ ማር ገምቦ ይገለገሉባታል እንደማለት ነው፡፡ ህዝቡ
ማሩን ፍለጋ በማሩ ዙሪያ ይኮለኮላል፤ ማሩን ግን አያገኝም፡፡

የዘመናዊ ሕገ መንግስታት ፈር ቀዳጅ የሆነው የአሜሪካ ሕገ መንግስት አንድም ቦታ ዴሞክራሲ ወይም ዴሞክራሲያዊ
የሚሉ ቃላትን አይጠቀምም፡፡ በተነፃፃሪ ባለፉት 25 ዓመታት ያየናት ኢትዮጵያ ከሕገ መንግስታቶቿ እስከ ፓርቲ
ፕሮግራሞች ድረስ ዴሚክራሲን ያልተጠቀመችበት ቦታ ማግኝት ከባድ ነው፡፡ ይህ ሲባል ግን ኢትዮጵያ አብዝታ
ዴሞክራሲ ዴሞክራሲ ስላለች አሜሪካ ደግሞ በሕገ መንግስቷ አንድም ቦታ አላስተናገደችውምና፤ ኢትዮጵያ የተሻለች ዴሞክራሲ ናት ማለት በፍፁም አይደለም፡፡ ይልቁንም የህዝቡን ፈቃድ የሚያደርግ እንጅ፤ ዴሞክራሲ፣ ዴሞክራሲ
የሚል ሁሉ ዴሞክራሲያዊ አይደለም፡፡ ለዚህም ላለፉት ከሁለት አስርት አመታት በላይ ሀገራችንን እና ህዝቧን በጭቆና
በአምባገነንነት እየገዛ ያለውን የወያኔ መንግስት ትልቅ ማሳያ ሆኖ እናገኝዋለን።

በዲሞክራሲ ጥላ በመሽሽግ የውጭውን አለም ይሁንታ ለመጐናጸፍ የሚተጋው ወያኔ አስተዳድረዋለሁ የሚለውን ህዝብ
ጥያቄ ለመመለስ ሲታትር አይስተዋልም ይልቊን ድምጻችን ይሰማ በማለት ሆ ብሎ የወጣውን ነፃነት ናፋቂ ትውልድ
በያደባባዩ ሲገድል ተመልክተናል ለዚህም በ1997 ምርጫ ማግስት የደረሰው ህዝባዊ ጭፍጨፋም ሆነ ከዚያ በኋላ
የተነሱ ህዝባዊ ጥያቄዎች ምላሻቸው የጠመንጃ አፈሙዝ እንደነበር የቅርብ ግዜ እውነታዎች ናቸው።


ወያኔ ብቻውን ለመወዳደር እየተራወጠ ባለበት የ2007 ምርጫ በተለያየ የመንግስት የሥራ ኃላፊነት ላይ ተቀምጠው
ያሉ ካድሬዎችና ደህንነቶች ሠራተኞችንና ነዋሪዎችን በየቀበሌው እንዲሁም በተለያዩ አዳራሾች እየሰበሰቡ ኢህአዴግን
መምረጥ ግዴታ እንደሆነ ከዛቻና ከማስፈሪያ ጋር መመሪያ እየሠጡ መሆናቸው ይታወቃል። የገዢው ፓርቲ
ካድሬዎችና ደህንነቶች በተለ ያዩ ወረዳዎችና ቀበሌዎች ነዋ ሪዎች እንዲሰበሰቡ ካስደረጉ በኋላ ስብሰባው የተጠራበትን
አጀንዳ በመተው “ኢህአዴግን መምረጥ ግዴታ ነው፤ ኢህአዴግን አለመምረጥ ፀረ ህዝብነት ነው፡፡” በማለት ህዝብን
በማሸበር ላይ ይገኛሉ።

ወያኔ እና ምርጫ የማይተማመኑ ሁለት ባልንጀራሞችን ያስታውሰኛል ይህን ያልኩበት ምክንያት *የማይተማመን
ባልንጀራ በየወንዙ ይማማላል* እንደሚባለው ወያኔም ምርጫ ከመድረሱ አስቀድሞ የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎችንም
ሆነ የነጻነት ታጋይ ግለሰቦችን/Activist/ ማተራመስ ይጀምራል። ለዚህም እንደማሳያነት የምንመለከተው ከቅርብ
ግዜያት ወዲህ በዞን9 ጦማርያን እንዲሁም በተለያዪ የፖለቲካ ፓርቲ ውስጥ ንቊ ተሳትፎ የነበራችውን ግለሰቦች በሀሰት
የክስ መዝገብ በማደራጀት ለእስርና ለእንግልት እንዲዳረጕ በማድረግ የፖለቲካውን ሂደት ለብቻቸው ለመቆናጠጥ
ሲታትሩ እናስተውላለን። ለመሆኑ ወያኔ ስልጣን ላይ የቆየው ህዝባችን መርጦት ነው እንዴ? የዚህን ምላሽ ለአምባቢው
ትቼዋለሁ። በእኔ በኵል ይህንን የአምባገነኑን መንግስት (ወያኔ) ለማስወገድ በአንድነት እንነሳ እላለሁ።



ድል ለጭቁኑ ህዝብ!!!





አስተያየትዎን በ andethiopia16@gmail.com ይላኲልኝ




ኢትዮሚድያ - Ethiomedia.com
October 13, 2014

source, http://www.ethiomedia.com/15store/weyaniawi_democracy.pdf

No comments:

Post a Comment