Search This Blog

Tuesday, October 28, 2014

የዛሬይቱ የሕወሃት/ኢሕአዴግ ኢትዮጵያ ይችን ትመስላለች !!!

አንድ ጊዜ እንዲህ ሆነ። ኦሃዮ ዉስጥ ባለ አንድ ዩኒቨርሲቲ ዉስጥ ነው። የተወሰንን ከዉጭ አገር የመጣን እግር ኳስ ለመጫወት በዩኒቨርሲቲዉ ወዳሉ ሜዳዎች አመራን። አንዱ ቦታ በጣም አረንጓዴ ነው። እንክብካቤ የተደረገለት ሃሪፍ ሜዳ። በዚያ መጫወት ጀመርን።
ብዙም አልቆየም አንድ ሰው መጣ። «እዚህ መጫወት አትችሉም ? » አለን። «ለምን ? » ብለን ጠየቅን። «የዪኒቨርሲቲው የእግር ኳስ ቡድን የሚለማመድበት ነው » የሚል መልስ ተሰጠን። « የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች ነን፣ ማንኛውም በጊቢው ያለው ፋሲሊቲ መጠቀም እንችላለን። እዚህ ነው የምንጫወተው» ብለን ክችች አልን። ሰዉዬ ሄደና ፖሊስ ጠራ። እንደገና ክርክሩ ከፖሊሱ ጋር ቀጠለ። «ለመማር ገንዘብ እንክፈላለን። የጊቢው ፋሲሊቲን በሙሉ እንጠቀማለን። እዚህ መጠቀም አይቻልም የሚል ሕግ ካለ ወረቀት አሳየን» ብለን ፖሊሱን ተከራከርን። ፖሊሱ በቀኙ ዱላ፣ በግራው ሽጉጥ ታጥቋል። በአክብሮት አናገረን። «ትክክል ናችሁ። አሁን ግን ቦታዉን ልቀቁና ፣ ነገ የዩኒቨርሲቲዉን አስተዳዳሪ ታናግራላችሁ» አለን።
ይሄን ታሪክ ያለምክንያት አይደለም ያነሳሁት። በአገራችን ኢትዮጵያ ካለው ጋር ለማመሳሰል ብዬ ነው። የዉጭ አገር ዜጎች ሆነን፣ በባእድ አገር ይሄን አይነት መብትና ክብር ስናገኝ፣ በአገራችን ግን እንደ ዉሻ እየተደበደብን፣ እየታሰረንና እየተገደልን መሆናችንን ሳሰበው ዉስጤ በጣም ይደማል።
መስከረም 22 ቀን እንዲህ ሆነ። ወጣት ፖለቲከኛው ሃብታሙ አያሌው ከማእከላዊ ወደ አራዳ ፍርድ ቤት መሄድ ነበረበት። ፖሊሶች እጁ ላይ ካቴና አስረዉ፣ በሕዝብ ፊት እንደ ዉሻ እየጎተቱት ነበር የሚወስዱት። «በወቅቱ መብቴና ክብሬ ተደፈሯል» ብሎ ለዳኛው ሃብታሙ አቤቱታ አቀረበ። ዳኛው «ለምንድን ነው እንደዚህ የምታደርጉት ? » ብሎ ፖሊሶቹን ጠየቀ። ፖሊሶቹ «ጉዳት እንዳይደርስበት ለመጠበቅ ነው» የሚል መልስ ሰጡ። ሁለተኛ እንደዚያ እንዳያደርጉ ፍርድ ቤት ቢያዛቸውም፣ እንደገና በካቴና እንደ ዉሻ እየጎተቱት ወሰዱት።
እዚህ ላይ እንግዲህ አንድ ነገር አንርሳ። ሃብታሙ ገና ክስ አልተመሰረተበትም። ፖሊስ መረጃ በእጁ ምንም ስለሌለ ፣ ምን ብሎ እንደሚከሰው ስለማያውቅ፣ መረጃዎችን ፈጠሮ እስኪያመጣ፣ ጊዜ ይሰጠኝ እያለ በመጠየቁ ነው ይኽው ለአራት ወራት ታስሮ እየተሰቃየ ያለው።
በካቴና እየተጎተተ መሄድ ብቻ አይደለም። ለአንድ ሳምንት መጸዳጃ ቤት እንዳይጠቀም ተከልክሎ ፌስታል ነበር የሚጠቀመው። ለሶስት ሳምንታት በጨለማ ቤት ዉስጥ ብቻውን ተቀምጦ ቶርቸር እየተደረገ ነው። እየተደበደበ ነው። ለማረሚያ ቤቱ ሃላፊ አቤት ቢል መልስ አላገኘም።
ይሄ ሁሉ ግፍ ለምን ? ሰዎቹ ባህሪያቸው እንደዚህ ነው። እንደ ሰው ሳይሆን እንደ እንስሳ ነው የሚያስቡት። ዶር መራራ ጉዲና እንዳሉት ከጫካ መጡ እንጂ ጫካ ከነርሱ አልወጣም። የሚቃወሟቸውን በሐሳብ ከማሸነፍ ይልቅ በጉልበት መጨፍለቅ ልማዳቸው ነው።
ሃብታሙንም ሆን ብለው ሞራሉንና መንፈሱን ሰባብረው በሽተኛ አድርገው ከጨዋታ ዉጭ ሊያደርጉት ስለፈለጉ ቶርቸር እያደረጉት፣ ኢሰብአዊ ጭካኔ እየፈጸሙበት ነው። «ፖለቲካውን የምትተው ከሆነ ትለቀቃለህ። አለበለዚያ ግን እዚሁ ትሞታታለህ» ነው እያሉት ያለው።
ብርቱክን ሚደቅሳ ላይ ይሄንኑ ነበር ያደረጉት። ለስድስት ወራት ጨለማ ቤት ዉስጥ አስቀምጠዋት ነበር። ሬፕ ባደረጉና በነፍሰ ገዳዮች ላይ እንኳን የማይደርስ የአካልና የስነ-ልቦና ቶርቸር ነበር የፈጸሙባት። መሰባበሯን ሲያወቁና ፖለቲካ እንደማትቀጥል ሲያረጋግጡ ለቀቋት። እርሷም ወደ ዉጭ ወጣች። እነርሱ እንደፈለጉትና እንደወደዱት ፖለቲካዉን ተወች። ተሳካላቸው።
ጀነራሎችና የአገዛዙ ባለስልጣናት፣ እንዲሁም ከነርሱ ጋር ያበሩና የስርዓቱ ተጠቃሚ የሆኑ ቱጃሮች በሰረቱ ፎቆች አዲስ አበባ ላይ ላዩን ብታምረም፣ በዉስጥ ግን ይህ አይነቱ ጭካኔ የሚፈጸምባት፣ የበሰበሰች ከተማ እየሆነች ነው። አዲስ አበባ ብቻ ሳይሆን በመላው ኢትዮጵያ እንደዚሁ።
እንግዲህ የዛሬይቱ የሕወሃት/ኢሕአዴግ ኢትዮጵያ ይችን ትመስላለች !!! ዜጎች እንደ ዉሻ የሚቆጠሩባት !!!!! ዜጎች የሚሰቃዩባት !!!!
ታዲያ መፍትሄው ምንድን ነው ? ዜጎች ዝም ባሉ ቁጥር ግፉ ይጨመራል እንጂ አይቀንስም። ይሄ ሁሉ ግፍ እየሆነ ዝምታን መምረጥ፣ የግፍ ተባባሪ መሆን ነው። በአገራችን ቶርቸር ሲደረግ፣ ዜጎችን ላይ መንግስታዊ ዉንብድናና ሽብር ሲፈጸም ሰምቶ እንዳልሰማ መሆን ፣ «ጎሽ ማሰራችሁን፣ መደብደባችሁን ፣ ማሰቃየታችሁን ቀጥሉበት፣ ግፉበት » እንደማለት ነው። ዝምታ መፍትሄ ሊሆን አይችልም። ብዙዎቻችን በአገራችን የሚደረገዉን ግፍ ስናይ ፣
ዉስጣችን ይደብናል። እንናደዳለን። ሆኖም መናደድና መቆጨት መፍትሄ ሊሆን አይችልም።
መፍትሄው አንድ እና አንድ ብቻ ነው። እርሱም እያንዳንዱ ዜጋ ለመብቱና ለነጻነቱ መነሳት ! ሁሉም የሚሊዮኖች ንቅናቄ አካል ከሆነ፣ ሁሉም በየክልሉ በየመንደሩ የግፍ አገዛዝን ከተቃወመ፣ ሁሉም የሌላዉን ይቀር፣ የራሱን፣ የቤተሰቡን ነጻነት ካረጋገጠ ፣ ያኔ ለውጥ ይመጣል።

No comments:

Post a Comment