Search This Blog

Thursday, November 6, 2014

ህዳር 9: የጸረ-ጭቆና ኣመጽ ዕለትን በተመለከተ ከኦነግ የተሰጠ መግለጫ

ለኦሮሞ ህዝብ የነጻነት ትግል የበለጠ ህዝባዊ ድጋፍ ለማስገኘትና ለጭቆና ስርዓት ፍጻሜ ለማበጀት የኦሮሞ ነጻነት ግንባር በ2005ዓም “በጨቋኝ የባዕዳን ስርዓት መገዛት ይብቃን!” ብሎ በጠላት ላይ እንዲያምጽ ለመላው የኦሮሞ ህዝብ ጥሪ ኣስተላለፈ። የኦሮሞ ህዝብም ከነጻነት ታጋይ መሪ ድርጅቱ፡ ኦነግ፡ የተላለፈለትን ጥሪ በደስታ ተቀብሎ በመላው ኦሮሚያ ውስጥ የጸረ-ጭቆና ኣመጽ በማካሄድ ዘወትር ሲዘከር የሚኖር ኣኩሪ እርምጃ ወሰደ።
በ2005ዓም የተቀጣጠለው ኣመጽ በተለያየ መልክና ደረጃ ሲካሄድ ዛሬ መድረሱም በተጨባጭና በገሃድ እየታየ ነው። በቀጣይነት እየተካሄደ ያለውን ይኸው የ2005ቱ የጸረ-ጭቆና ኣመጽም ከወርሃ ሚያዚያ 2011ዓም ጀምሮ በቆራጥ የቄሮ ኣባላት የኦሮሞ ወጣቶች በኣዲስና የተደራጀ መልክ ይዞ ይበልጥ በመፋፋም መላውን ኦሮሚያን ኣዳርሶ እንደቀጠለ ነው። በቄሮ ቢሊሱማ የኦሮሞ ወጣቶች ተቀጣትሎ በሰፊው የኦሮሞ ህዝብ ተሳትፎና ድጋፍ እየተካሄደ ያለው ኣመጽ ጠላትን ያንቀጠቀጠና የኦሮሞ ህዝብ የነጻነት ትግልን ደግሞ ወደ ግቡ ያቃረበ መሆኑ በ2014ዓም ሲካሄድ የነበረውና እየተካሄደያለው የጸረ-ጭቆና ኣመጽ በሚገባ ኣረጋግጧል።
በኦሮሞ ወጣቶች ግንባር-ቀደም ተሳትፎ እየተካሄደ ያለው የኦሮሞ ህዝብ ኣመጽ በሃገር-ቤትና በውጪ ሃገራት ካለው የኦሮሞ ተወላጅ ከፍተኛ ድጋፍና ትብብር ማግኘት መቻሉ በኦሮሞ ህዝብ ላይና በኦሮሚያ ወስጥ እየተፈጸመ ያለውን ደባና እኩይ ተግባራትን ለዓለም ይፋ ማድረግ ኣስችሏል። እነዚህ ድሎች በቀላሉ ያልተገኙ ስለመሆናቸው ደግሞ ከማንም የተሰወረ ኣይደለም። የኦሮሞ ህዝብ ነጻነትን የሚፈልግ መሆኑን በግልጽ ለማሳየት ከባድና ውድ መስዋዕትነት ከፍሏል። ህይወቱ፡ ኣካሉንና ንብረቱን እንዲሁም በገንዘብ የማይተመኑ ሌሎች መስዋዕትነቶችን እየከፈለ ይገኛል። ከሁሉም በላይ በኢትዮጵያ ኢምፓዬር ውስጥ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ የቄሮ ቢሊሱማ ኣባላት የኦሮሞ ወጣቶች ለሃገር ባለቤትነት መብታቸው መከበር ሲያካሄዱት የነበረውና እያካሄዱት ያለው ፍልሚያ ጨቋኙን የወያኔ ስርዓት እየለበለበ፡ የኦሮሞ ህዝብ ነጻነት የማይቀር መሆኑን በግል ኣስመስክሯል። የኦሮሞ ህዝብ ነጻነት መረጋጋጥ የማይቀር መሆኑን መተኪያ የሌላትን ህይወታቸውን በመሰዋት ያረጋገጡትን የኦሮሞ ወጣቶች፡ ተማሪዎችና ብሄርተኞችን በክብር መዘከር ደግሞ የሁሉም የኦሮሞ ዜጋ የዜግነት ግዴታ ነው።
የዘንድሮውን ህዳር 9: የጸረ-ጭቆና ኣመጽ ዕለት በኦሮሚያ ውስጥና የኦሮሞ ዜጎች በሚገኙባቸው የውጪ ሃገራት ሁሉ በደመቀ ሁኔታ ህይወታቸውን የሰዉትን ውድና ቆርጥ የኦሮሞ ልጆች ከማሞገስና መዘከር በተጨማሪ መስዋዕትነት የከፈሉበትን የነጻነት ትግል ከግቡ ለማድረስ ቃላችንን ማደስ ይኖርብናል። በዚህም ለፍትሓዊና ክቡር ዓላማ ልጆቻቸውን ያጡትን እናቶች እንባ ለማበስ ይበልጥ ለመታገል በቆራጥነት መነሳት ይጠበቅብናል። ለህዝባቸው ነጻነት ሲሉ በጸረ-ጭቆና ኣመጹ ውስጥ ህይወታቸውን የሰዉትን የኦሮሞ ወጣቶች፡ ተማሪዎች ብሄርተኞችን መዘከር የያንዳንዱ ኦሮሞ ዜጋ ግዴታ መሆኑን በመገንዘብ ይህንን ዕለት በያለንበት ሁሉ እንዘክር። የተሰዉ ጀግኖቻችንን ስናስታውስ የጨቋኙ ስርዓት ወህኒ ቤቶች ውስጥ እየተሰቃዩ ያሉትን ዜጎቻችንንም መርሳት የለብንም። በተቻለ መንገድ ሁሉ ከጎናቸው መቆም ሁሉም የኦሮሞ ዜጋ በተጨማሪ ሊተገብረው የሚገባ ወገናዊ ግዴታ ነው። ጨቋኙ የወያኔ መንግስት ለኦሮሞ ህዝብ ርህራሄ የሌለውና ኦሮሞን ከምድረ-ገጽ በማጥፋት እንደጨቆነ ለመኖር ኣቅዶ እየሰራ ያለ መሆኑ ያለፉት 23ዓመታት የወይኔ ኣገዛዝ በማያጠራጥር ሁኔታ ኣሳይተዋል።
ስርዓቱ የኦሮሞ ህዝብን ለማጥፋት ከመስራት የማይቆጠብ መሆኑን የኦሮሞ ዜጎችን ያለምንም ርህራሄ ከኣያት-ቅድመ ኣያት መሬታቸው በማፈናቀል ለራሱ መውሰድና ለሸሪኮቹ ማከፋፈል፡ ኦሮሞ በኢኮኖሚ ጠንካራ መሰረት እንዳይኖረው የተለያዩ ደባዎችን በመፈጸም ማደህየት፡ የኦሮሞ ልጆችን ከማሃይምነት ጨለማ ውስጥ ለማስቀረት ከየትምህርት ቤትች በጅምላ ማባረር፡ በእስርቤቶች ውስጥ ማሰቃየትና እየፈጸመ ያለው ጭካኔ የተመላበት ግድያ ለዚህ ማርረጃ ይሆናሉ።
በሌላ በኩል የኦሮሞ ህዝብን በተለያየ በልኩ ሊቀርቡትና ሊወዳጁት የሚሹ ባዕዳን ሁሉ ነጻነቱና የዲሞክራሲ መብቱ ተከብሮ እንደኦሮሞ በሃገሩ ላይ ኣዛዥ ሆኖ መኖሩን የማይፈልጉ መሆናቸውን የጸረ-ጭቆና ኣመጹ በሚገባ ኣረጋግጧል። የኦሮሞ ዜጎች የነገ ሃገር ተረካቤ የወገን ኣለኝታ ወጣቶች ሳይቀሩ በጠራራ ጸሃይ በጥይት ሲደበደቡ፡ በኣስር ሺዎች እስር ቤት ሲታጎሩ፡ ህጋዊ ኣግባብ የረዥም ዓመታ የእስር ብይን ሲተላለፍባቸ ለኦሮሞ ዜጎች ኣለመረሳቸውና በዝምታ ማለፋቸው እነዚን ባዕዳን ኣካላት ምን እንደሚፈልጉ ያሳያል።
ትላንት፡ ዛሬም ሆነ ለወደፊቱ የኦሮሞ ህዝብ የነጻነት ትግል በባዕዳን ኣካላት ትብብርና ድጋፍ ሳይሆን በራስ በመመኮዝ ዓላማ በመካሄድ ፍጻሜውን የሚያገኝ መሆኑ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር የጸና እምነት ነው። ስለሆነም የኦሮሞ ህዝብ በተለይም ደግሞ የታጠቀውን የጠላይ ሃይል ባዶ እጆቹን በጀግንነት እየተጋፈጠ ያለው ኣዲሱ ትውልድ ነጻነቱን የሚያገናጽፈው ትግሉ ብቻ መሆኑን በጥልቀት በመገንዘብ ኣመጹን ኣፋፍሞ ከፍጻሜው ኣንዲያደርስ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር በዚህ ኣጋጣሚ መልዕክቱን ያስተላልፋል።
በሃገር ቤትና ውጪ ሃገራት ያለው የኦሮሞ ህዝብም እንደኣሁኑ ኣንድነቱን ኣጠናክሮ የጋራ ክንዱንም በማጠናከር የጸረ-ጭቆና ኣመጹን በማፋፋሙ ውስጥ ድርሻውን እንዲያሳድግ ኦነግ በክብር ያሳስባል። ጠንካራ ሃይል ሆነን የጭቆናን ቀንበር ኣሽቀንጥረን ለመጣል እንድነታችንን እናጠናክር።
የወይኔ መንግስት በኣሁኑ ወቅት ኣገዛዙን ለማስቀጠል ስልጣን ላይ የሚያሰነብተውን የይስሙላ ምርጫ ለማካሄድ በዝግጅት ላይ ይገኛል። የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ለሰኔ ወር ቀጠሮ የተያዘለት ምርጫ ካሁን ቀደም ከተካሄዱት ምርጫዎች የተለየ ይሆናል የሚል እምነት የለውም። የምርጫውን መድረክ የሚያዘጋጀው፡ የሚመራውና የሚመረጠውን ሰው የሚያዘጋጀው ወያኔና ወያኔ ብቻ ነው። ከዚህ ደግሞ የኦሮሞ ህዝብ ኣንዳች ፋይዳ ኣግኝቶ ኣያውቅም፡ የሚያገኘው ጥቅምም ኣይኖርም። ስለሆነም የኦሮሞ ህዝብ ዘወትር በሚነዛው የጠላት ፕሮፓጋንዳ ሳይታለል በማይመለከተው ምርጫ ላይ ጊዜውን ማባከኑን ትቶ የኣልገዛም-ባይነት ኣመጹን ኣጠናክሮ እንዲቀጥል ኦነግ መልዕክቱን ያስተላልፋል። ለጠላት ሰርግ ኣጫፋሪ መሆን እዚህ ላይ ማብቃት ይኖርበታል።

በመጨረሻም ከጸረ-ጭቆና ኣመጹና የኦሮሞ ህዝብ የነጻነት ትግል የተቀሰሙ ልምዶችን እንዲሁም የተገኙ ጥንካሬውንና ድሎችን እያስጠበቁ፡ ነጻነትን የሚያገናጽፈንን ሁሉን ኣቀፍ ትግል ለማፋፋም በኣንድነትና በተባበረ ክንድ እንታገል! የነጻነት ታጋዮቻችንና ውድ የኦሮሞ ልጆች ህይወታቸውን የሰዉለትን ክቡር ዓላማ ከግቡ ለማድረስ ወከባችንን ኣስረን በቆራጥነት እንንቀሳቀስ!
በጸረ-ጭቆና ኣመጹና በነጻነት ትግሉ የተሰዉ ታጋዮች፡ ብሄርተኞችና ውድ የኦሮሞ ልጆችን እየዘከርን፡ የኦሮሞ ጀግኖች የተሰዉለትን ዓላማ ከግቡ ማድረስ ያለብን ግዴታና ሃላፊነት መሆኑን ተገንዝበን ለትግሉ ፍጻሜ ለማበጀት እንነሳ!
ድል ለኦሮሞ ህዝብ!
የኦሮሞ ነጻነት ግንባር
ህዳር 2014ዓም

No comments:

Post a Comment