Search This Blog

Thursday, November 20, 2014

ስለ ወያኔ ጭካኔ ነውረኝነትና አውሬነት

ሰሞኑን ስለ ሞት ፍርድ ሲወራ የክንፈ ገ/መድህን ገዳይ ሻለቃ ጸሃዬ አሟሟት የኢሕአዴግን አውሬነትTemesgen Desalegn የጻፈውን እነሆ
"...በነገራችን ላይ መረሳት የሌለበት ቁም-ነገር የጥፋት ስራው ተጠያቂ ህወሓት እንጂ ‹‹እወክለዋለው›› የሚለው የትግራይ ህዝብ አለመሆኑ ነው፡፡ አማራ-በብአዴን፣ ኦሮሞ-በኦህዴድ እንደማይገለፀው ሁሉ፣ የትግራይ ህዝብም በህወሓት ይገለፃል የሚል የጨዋታ ህግ የለም፡፡ እነዚህ ሰዎች ለስልጣናቸው እስከጠቀመ ድረስ የማይፈፅሙት ህገ-ወጥ ድርጊት አለመኖሩ ላይ መስማማት የሚኖርብን ይመስለኛል፤ የማይፈፅሙት ጭካኔም የለም፡፡ ይህንን የሚያሳይ አንድ ነገር ልንገራችሁ፡፡ ታሪኩ የቀድሞ የደህንነት ሹም የነበረው ክንፈ ገ/መድህንን በጥይት ደብድቦ ስለገደለው ሻለቃ ፀሀዬን የሚመለከት ነው፡፡ እንደሚታወቀው ሟችም ገዳይም ትግርኛ ተናጋሪዎች ቢሆኑም፣ ሻለቃው ወንጀሉን ከፈፀመ በኋላ ለብዙ ችግር ተዳርጎ ነበር፣ ያውም ከነቤተሰቡ፡፡ መጀመሪያ ባለቤቱን ከምትሰራበት ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት አባረሯት፡፡ እግር በእግርም እየተከታተሉ በኪራይ ከምትኖርበት ቤት አፈናቀሏት (በጊዜው እስክንድር ነጋ የገንዘብ ድጋፍ ያደርግላት ነበር) ሻለቃውም ለስድስት ዓመት ያህል በጨለማ ቤት ውስጥ በመታሰሩ የአይን ብርሃኑ በከፍተኛ ደረጃ ተጎዳ፡፡ ፍርድ ቤት ሲቀርብ እንዴት ለመራመድ ይቸገር እንደነበረ አስተውለናል፡፡ እኔ እያልኩ ያለሁት ያጠፋ ሰው በህግ አይጠየቅ አይደለም፤ ከህግ ውጪ ስለምን የበቀል ሰለባ ይሆናል ነው? ሰዎቹ ከየትኛውም ብሄር ተወለዱ በጠላትነት ከመዘገቧችሁ ለጭካኔያቸው ወደር የለውም፡፡ 
የሆነው ሆኖ ስርዓቱ ገደብ ላጣው ጭካኔው ‹‹ብሄር›› የተሰኘ አጥር የለውም ያስባለኝ በሻለቃው ህይወት መጨረሻ የተፈፀመው ድርጊት ነውና እሱን ልንገራችሁ፡፡
ዕለቱ የኦርቶዶክስ ክርስትና እምነት ተከታዮች ‹‹ፍልሰታ›› እያሉ የሚጠሩት የአስራ ስድስት ቀን ፆም ዋዜማ ነው-ሐምሌ 30ቀን፡፡
ሻለቃው ይህች ቀን የመጨረሻዋ መሆኗን ሊያውቅ የሚችልበት አገጣሚ አልነበረምና ጥብቅ ሀይማኖተኛ በመሆኑ ለፆሙ የመንፍስና የቁስ ዝግጅቱን አጠናቆ በደስታ እየጠበቀ ነው፡፡ የሆነው ግን በተቃራኒው ነበር፡፡ 


በፃሃፊ ብዕር ልተርክላችሁ፡፡
…ወቅቱ ክረምት ቢሆንም ፀሀይ ህቡዕ የገባች እስኪመስል ድረስ ዝናብን አግደው የያዙ የሰማይ መስኮቶች ከንጋት ጀምረው ላንቃቸውን ከፍተው ምድሪቱን እያረሰረሷት ነው፡፡ ቀኑ ተገባዶ አስር ሰዓት ላይ ደርሷል፡፡ አብዛኛው እስረኛ በየክፍሉ ከቷል፡፡ ጥቂቶቹ ደግሞ ውሽንፍሩን ተከትሎ ያረበበውን ቅዝቃዜ ይከላከልልናል በሚል ካፍቴሪያ ውስጥ ቁጭ ብለው ሻይና ቡና ደጋግመው ያዛሉ፡፡
አንዲት የደህንነት መኪና ሾፌሩን ጨምሮ አራት ሰዎች አሳፍራ ወደማረሚያ ቤቱ አስተዳደር መግባቷን ማንም አላስተዋለም፡፡ መኪናዋ የኃላፊውን ቢሮ ታካ ስትቆም የቡድኑ መሪ ቀልጠፍ ብሎ ወርዶ በቀጥታ ከፊቱ ወደአለው ቢሮ በመግባት፣ ከማረሚያ ቤቱ ኃላፊ ጋር ለጥቂት ደቂቃዎች ቆይታ ከአደረገ በኋላ በወህኒ ቤቱ ውስጥ ያልተለመደ ትዕዛዝ ተላለፈ፤ ሁሉም እስረኛ ወደ ክፍሉ እንዲገባ የሚል፡፡
እስረኞቹ በሙሉ ወደ ክፍላቸው መግባታቸው ከተረጋገጠ በኋላ የሞት ፍርድ ተፈርዶበት ቀኑን እየጠበቀ የነበረው ሻለቃ ፀሀዬ ከክፍሉ ወጥቶ ከደህንነት ቢሮ ወደመጣችው መኪና ውስጥ እንዲገባ ተደረገ፡፡ መኪናዋም በመጣችበት ፍጥነት የመልስ ጉዞ አደረገች፡፡ ይህ ሁሉ ነገር ተካሄዶ ያለቀው በአስራ አምስት ደቂቃ ውስጥ ነበር፡፡
...ጎዳናው ላይ አልፎ አልፎ እየተንገዳገደ ከሚያዘግም ሰካራም እና ከሚያላዝኑ የመንገድ ዳር ውሾች በቀር አንዳች እንቅስቃሴ አይታይም፤ ጭር ብሏል፡፡ የክረምቱ ቅዝቃዜ በድቅድቅ ጨለማ ቁጥጥር ስር ከዋለው ሌሊት ጋር ተቀላቅሎ በእጅጉ ያስፈራል፡፡ የሻለቃው ባለቤት ወ/ሮ አምሳለ የመኖሪያ ቤቷ በር ሲንኳኳ ከሶስት ልጆቿ ጋር በእንቅልፍ ዓለም ውስጥ ነበረች፡፡ ማንኳኳቱ ሳይቋረጥ ለደቂቃዎች በመቀጠሉ ድንገት ካሰጠማት እንቅልፍ አባነናት፡፡ እናም በሩን ከፈተች፡፡ ከዚህ ቀደም አይታቸው የማታውቃቸው ሁለት ሰዎች ቆመዋል፡፡ ደነገጠች፡፡ 
‹‹ምንድን ነው? ምን ፈልጋችሁ ነው?›› አከታትላ ጠየቀች፡፡ 
‹‹ፖሊሶች ነን፣ ሻለቃ ፀሀዬ በጣም ስለታመመ አምሳለን ጥሩልኝ ስላለን ነው የመጣነው›› ሲል መለሰ አንደኛው ሰውዬ፡፡
‹‹ቀን ስንቅ ስወስድለት ደህና አልነበረ እንዴ? አሁን ምን ተፈጠረ?›› 

‹‹ድንገት ነው የታመመው፤ ልታዪው የምትፈልጊ ከሆነ ቶሎ እንሂድ?›› አለና አጣደፋት በሌሊት ከሰው ደጅ ቆሞ መመላለሱ ያልተመቸው ሁለተኛው ሰው፡፡ ወ/ሮ አምሳለም ስጋት እንደሞላት ሰዎቹን አሳፍራ በመጣችው መኪና ውስጥ ገብች፡፡ ሆኖም መኪናዋ ወደመጣችበት መመለሰ ስትጀምር መንገዱ ወደቃሊቲ የሚወስደው እንዳልሆነ ተረዳች፡፡ ከሃያ ደቂቃ ጉዞ በኋላም መኪናዋ አንድ ግቢ ውስጥ ገብታ ቆመች፡፡ ሁሉም ወረዱ፡፡ 
‹‹የታለ ባለቤቴ?›› አምሳለ ጠየቀች፣
‹‹ያው! እዛ ክፍል ውስጥ ግቢ፣ እየጠበቀሽ ነው›› አላት አንደኛው ሰው፣ በሩ ወደተከፈተ ክፍል በእጁ እያመለከተ፡፡
እንደተባለችው ገርበብ የተደረገውን በር ሙሉ በሙሉ ከፍታ ገባች፡፡ …ክፍሉ ወለል መሀል ላይ ሻለቃው በጥይት ተበሳስቶ በጀርባው ተዘርሯል፡፡ …ያልጠበቀችውን ክስተት የተመለከተችው የሻለቃው ባለቤት እንደሎጥ ሚስት የጨው አምድ ሆነች፡፡ …የዚህን ያህል ነው የህወሓት ጭካኔ፡፡ ከመስመሩ ካፈነገጣችሁ ትግሬ ሆናችሁ አማራ ጉዳዩ አይደለም፡፡ እናም ማቆሚያ ላጣው የአማርኛ ቋንቋ ተናጋሪዎች መፈናቀልም ብቸኛው ተጠያቂ ህወሓት እንጂ ‹‹ወከልኩት›› የሚለው ህዝብ በፍፁም ሊሆን አይችልም፡፡ ይህ አመለካከት የተሳሳተ ከመሆኑም በላይ የማይታረም አደጋ ያስከትላል፡፡ የስርዓቱ ደጋፊዎችም ሆናችሁ ልሂቃኖች፣ በአሰልቺ ዜማ ጠዋትና ማታ ‹‹አባይ፣ አባይ…›› የምትሉ አርቲስቶች ከምንም በፊት ስለንፁሀን እምባ መገደብ ልትናገሩ ይገባል፡፡ አገዛዙ የዱርዬ ባህሪውን ይገድብ ዘንድ ስትዘምሩ መስማት እንፈልጋለን፡፡"
‪#‎FreeAllPoliticalPrisoners‬

No comments:

Post a Comment