Search This Blog

Thursday, February 27, 2014

በባህር ዳር ከተማ የታየው ህዝባዊ ተቃውሞ በሌሎች የሀገራችን ክፍሎችም ተጠናክሮ ይቀጥላል!

(አንድነት) የተሰጠ መግለጫ!!!

ከጊዜ ወደ ጊዜ አምባገነናዊ የአፈና መዋቅሩን በማጠናከር ለመድብለ ፓርቲ የፖለቲካ ሥርዓት በር መዝጋቱን አጠናክሮ ለብቻው አውራ ፓርቲ ለመሆን እየታተረ ያለው የኢህአዴግ መንግሥት ደርግ በውድቀቱ ዋዜማ ወደ ተላበሰው ባህሪ እየተሸጋገረ እንደሆነ ተስተውሏል፡፡
የዚሁን ድርጅታዊ ባህሪ ውርስ በዋነኛነት ከሚያስፈጽሙት የግምባሩ አባል ድርጅቶች አንዱ የሆነው ብአዴን ኢህአዴግ በአማራው ህዝብ ላይ እየፈፀመው ያለው የንቀት እና የማጥላላት ዘመቻም አብይ ተደርገው ሊወሰዱ ከሚችሉ የግንባሩ አፍራሽ ተግባራት በዋነኝነት ሊጠቀስ የሚችል ነው፡፡
የአማራ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር እና የብአዴን ጽ/ቤት ኃላፊ የሆኑት አቶ አለምነው መኮንን የክልሉን ህዝብ የናቀ እና ያዋረደ አስነዋሪ ንግግር ካደረጉ በኋላ ከጥፋታቸው ከመታረም ይልቅ በክልሉ ቴሌቭዥን ያንኑ አምባገነናዊ ባህሪያቸውን እንደያዙ የግሌ ብቻ ሳይሆን የድርጅቴ አቋም ነው ሲሉ መመለሳቸውም መላውን የሀገሪቷን ህዝብ ያስቆጣ ተግባር ነው፡፡

ይህንን አስነዋሪ ተግባር የፈጸመውን ብአዴንን ከ70 እስከ 80 ሺህ የሚደርሱ የባህር ዳር ከተማና የአካባቢው ነዋሪዎች ከፓርቲያችን ጎን በመሰለፍ እሁድ የካቲት 16 ቀን 2ዐዐ6 ዓ.ም የባህር ዳርን ጎዳና እና አደባባዮች በህዝባዊ ማዕበል ሲያስጨንቁ መዋላቸውም ሰላማዊ ትግሉ የደረሰበትን ሁኔታ በግልፅ የሚያስገነዝብ ነው ማለት ይቻላል፡፡ የኢህአዴግ መንግሥት በአንፃሩ ዛሬም ከስህተቱ ለመማር ያልተዘጋጀ በመሆኑ ይህን የሰፊ ህዝብ ቁጣ በማጣጣል አፋኝ እና ተሳደቢ መሪዎቹን ከጉያው ላለመነጠል እየሞከረ እንደሆነም አስተውለናል፡፡ ፓርቲያችን አንድነት ለዴሞክራሲ እና ለፍትህ ፓርቲ አንድነት የባህር ዳር እና አካባቢው ነዋሪዎች ላደረጉት ህዝባዊ ትገል ከፍተኛ ክብር እና አድናቆት አለው፡፡ ይህንን ህዝባዊ መሠረታችንን ወደ ላቀ ደረጃ በማሸጋገር በሁሉም የሀገራችን ክልሎች ተቃውሞው ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ልናረጋግጥ እንወዳለን፡፡
የብሔረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ብአዴን) ይህንን የህዝብ ጥያቄ አለመቀበሉን እየገፋበት በመሆኑም በባህርዳር የታየው ህዝባዊ ተቃውሞ ቤሎች የሀገራችን ክልሎች ተጠናክሮ የሚቀጥል ሲሆን አቶ አለምነው መኮንን በፍርድ አደባባይ ለማቆም በአጭር ጊዜ ውስጥ ክስ መስርተን ለህዝብ ይፋ እንደምናደርግ እናረጋግጣለን፡፡
በመጨረሻም በዚህ ፈታኝ የትግል ምዕራፍ ፡-
1ኛ. መላው የኢትዮጵያ ህዝብ
2ኛ. በውጭ ሀገር የምትኖሩ ኢትዮጵያውያን፤ የፓርቲያችን አባላት እና ደጋፊዎች ከጎናችን በመሆን ትግላችንን እንድትደግፉ ጥሪ እናቀርባለን !!!!
በባህርዳር የታየው ህዛባዊ መነቃቃትና የትግል ስሜት በሌሎች የሀገራችን ክፍሎች ይደገማል !!!
ድል የህዝብ ነው !!!

No comments:

Post a Comment