Search This Blog

Sunday, February 2, 2014

እቅድ - ትራንስፎርሜችን - ራእይ = ኢሕአዴጋዊ መንጠራራት አቅዶ የሚያብድ ሥውር አደገኛ ሕሊና፣ ቁምነገር አልባ ነው!

የሰላም ትልቁ ጠላት ከአቅም በላይ መመኘት ነው፡፡

የሥራ መንፈስ ከብዙሃኑ የልብ ፍቅርና የአገር መውደድ ስሜት ጋር በፅኑ መቆራኘት አለበት፡፡ ላገር አሳቢ እየመሰለ ውስጥ ውስጡን እንደሚቦጠቡጥ ሹም ባለበት ቦታ ዕቅድ ሲታቀድ ቢውል ፍሬ-ቢስ ነው የሚሆነው። ነባር ነባር በላተኛ አባርረን ትኩስ ትኩስ፣ ልጅ-እግር በላተኛ ካመጣን፤ የበላተኞች መተካካት እንጂ የአዲስ ደም - ቅያሪ አይሆንልንም፡፡ እጃችንን ዘርግተን የማንደርስበትን ነገር ለመጨበጥ መሞከር፤ በር ከፍተን ለዘራፊ እንደመተው ነው፡፡ የሰላም ትልቁ ጠላት ከአቅም በላይ መመኘት ነው፡፡ አሊያም የክቡር እምክቡራን ዕብደት ነው። “ከአቅም በላይ መኖር የዕድገት ፀር ነው” ይሉ ነበር ያለፈው ሥርዓት ነገረ-ሠሪዎች! ኮከብ እነካለሁ ብሎ ሠምበሌጥ ላይ መወድቅ ይከተላል፡፡ ለራስ ጥቅም ሲሉ የአገር ዕቅድ አወጣሁ ማለት መዘዙ ብዙ ነው፡፡ ድህነት ባጠጠበት፣ ችጋር በተንሠራፋበት አገር እንደ ህንድ እጉልላቱ አናት ላይ ጥቂት ባለ ፀጋ ሰዎች ብቻ ተቀምጠው፣ የበለፀገች ኢትዮጵያን መመኘት ከንቱ መገበዝ ነው፡፡


በአየር ላይ ህንጻ መገባት እንደማይቻለው ሁሉ ማቀድና በባዶ ሜዳ መመኘት እጅግ የተራራቁ ጉዳዮች ናቸው፡፡ ማቀድ፤ በዝርዝር ያቀድኩትን ለመፈፀም ምን ምን አደርጋለሁ ማለትን፣ ያንንም ማስፈፀሚያ ፋይዳ ያለው ቁሳቁስንና አጋዥ የሰው ኃይልን፤ እንዴት እቀዳጀዋለሁ ማለትን፤ በመጨረሻም ቀን በቀን ሥራ ላይ ማዋልን ይጠይቃል፡፡ በዚህ ማህል ባይሳካስ ብሎ ማውጠንጠንን፣ ሁለተኛ ዘዴ መዘየድን እቅድ 2 እንዲሉ የግድ ማሰብን ይሻል፡፡ ካልሆነና አማራጭ ሁሉ ከተሟጠጠም በጊዜ ሀሳብን ለውጦ ወደ ሌላ ዕቅድ መሸጋገር ነው፡፡ ከዚህ ቀላልና ግልፅ መንገድ ውጪ በጉልበት ልሥራህ ቢሉት ሀብትንም ማባከን፣ የሰው ኃይልንም በአጓጉል መንገድ ሜዳ ማፍሰስ ነው፡፡ እግርህን በአልጋህ ልክ ዘርጋ፤ እንደማለት ነው፡፡ ይህን በአገር ደረጃ መንዝሮ ማየት ነው እንግዲህ አገርን ለማሳደግ መጣጣር፡፡ ከምንጨብጠው በላይ መጀመሪያ እጃችን ረዥም መሆኑን ማረጋገጥ ያስፈልጋል;;


“ይህንንማ ማን ያጣዋል ይሄንን ማንም ያውቀዋል፡፡ ዝቅተኝነት’ኮ፣ የለጋ ምኞት መሰላል ነው ጠዋቱን ሥልጣን የጠማው:- ደረጃውን ሲያያዘው፣ ሽቅብ ሽቅብ ያንጋጥጣል ጫፉ ላይ ሲደርስ ግና፣ ጀርባውን ለመስጠት ይሻል ጧት የበላበትን ወጪት፣ ማታ ሰባሪ ይሆናል ቀና ብሎ ወደ ሰማይ፣ ደመናውን ብቻ ያያል እላይ ያወጣውን ታች ሰው፣ ቁልቁል ረግጦ ይሳደባል” ይላል የሺክስፒሩ ብሩተስ፡፡ ዞሮ ዞሮ ዕቅድ እንደ አቃጁ፣ ዕቅዱ እንደ ከዋኙ ነው፡፡ የሸር ዕቅድም፣ የአውቆ-አበድ ዕቅድም አለና ጠንቅቆ ማየት ይገባል፡፡ ታዋቂው ፀሀፌ-ተውኔት ፀጋዬ ገብረ መድህን በሚኒልክ ተውኔት፣ በኢልግ አፍ፣ እንዲህ ይላል፡- “ኮንቲ ኦሊኒ ግን ጭምት፣ ቀዝቃዛ፣ ነገር ለማሻከር ሆን ብሎ በዕቅድ የሚቆጣ፣ ሆን ብሎ በዕቅድ እንዳስፈላጊው ሁኔታ የሚያብድ፣ አንድ ነፃ መንግሥት ያለኔ ፈቃድ ለምን ሰንደቅ ዓላማ ተከለ ብሎ በነገረ-ቀደም አቅዶ እሚጮህ፤ … አቅዶ የሚያብድ ሥውር አደገኛ ሕሊና፣ ቁም - ነገር - አልባ ሰው ነው!” ከዚህ ይሰውረን፡፡ ዕቅዶች ይከወናሉ፡፡ ፓርቲዎች ይለመልማሉ፡፡ አገር ታድጋለች፡፡ የዕለት ጉርሥ የዓመት ልብስ ይኖረናል ማለት ያባት ነው፡፡ ሆኖም ያ እስኪሳካ ድህነት አንድያውን እንዳያደቀን ሁሉን በወግና በቅጡ ማስተካከል፣ መቆጣጠር፣ መተግበር ያስፈልጋል፡፡ 

No comments:

Post a Comment